በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዩናይትድ ስቴትስ

ከእግረኞች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት መኪና የሚበዛባቸውን ጎዳናዎች በሚያቋርጡበት ጊዜ ሙዚቃ በማዳመጥ፣ ስልክ በማነጋገርና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን በማከናወን ትኩረታቸው እንደሚከፋፈል አንድ ጥናት ጠቁሟል። ከሁሉም ይበልጥ አደገኛ የሆነው ትኩረት የሚከፋፍል ነገር የጽሑፍ መልእክት መጻፍ ሆኖ ተገኝቷል። የጽሑፍ መልእክት የሚላላኩ ሰዎች አንድን የመኪና መንገድ ለማቋረጥ የሚፈጅባቸው ጊዜ ትኩረታቸው ካልተሰረቀባቸው እግረኞች 18 በመቶ በልጦ ሲገኝ የመብራት ምልክቶችን ያለማክበር፣ ተገቢ ባልሆነ ቦታ የማቋረጥ ወይም ግራና ቀኝ ሳያዩ የማቋረጥ አጋጣሚያቸው 3.9 እጥፍ ሆኖ ተገኝቷል።

ናይጄርያ

በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከናይጄርያ ወደ አውሮፓ የሚወሰዱ ሴቶች በጁጁ የጥንቆላ ቦታዎች ምሥጢር ያለማውጣት የመሐላ ሥርዓት እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ። እነዚህ ሴቶች መሐላችንን ካልጠበቅን ከመንፈሳዊው ዓለም ቅጣት ይደርስብናል የሚል ሥር የሰደደ ፍርሃት ያለባቸው ሲሆን ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ደግሞ ሴቶቹ ጸጥ ለጥ ብለው እንዲገዙላቸውና የወሲብ ባርነት ግዳጃቸውን በታዛዥነት እንዲፈጽሙ ለማድረግ ይህን እንደ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል።

ስፔን

ለረጅም ጊዜ ሥራ አጥ ሆነው ከቆዩ ሰዎች መካከል ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውንና የሙያ ልምዳቸውን ከማመልከቻ ቅጻቸው ላይ ያወጡታል። ይህን የሚያደርጉት ብቃታቸው ከተፈላጊው መሥፈርት በልጦ እንዳይገኝ በመስጋት ነው።

ዓለም

በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ከኋላ ቀር ምድጃዎች የሚወጣው ጭስ ለሞት መንስኤ ከሆኑ ነገሮች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ በእነዚህ አገሮች በየዓመቱ አራት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በጭስ ምክንያት በሚመጣ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የተነሳ ይሞታሉ። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ከእንጨት ወይም ከከሰል ምድጃዎች የሚወጡት መርዛማ ኬሚካሎች በገዳይነታቸው በሲጋራ ጭስ ውስጥ ከሚገኙት ኬሚካሎች አይተናነሱም።