ቃለ ምልልስ | ፌንግ-ሊንግ ያንግ
አንዲት የማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች?
ፌንግ-ሊንግ ያንግ በታይፔ፣ ታይዋን በሚገኘው ማዕከላዊ የምርምር አካዳሚ ረዳት ተመራማሪ ነች። የምርምር ውጤቶቿ በሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ታምን ነበር። በኋላ ግን አስተሳሰቧን ለውጣለች። ንቁ! መጽሔት ስለምታጠናው የሳይንስ ዘርፍና ስለ እምነቷ አነጋግሯታል።
እስቲ ስለ አስተዳደግሽ ንገሪን።
ወላጆቼ በጣም ድሆች ሲሆኑ እናቴ ማንበብ እንኳ አልተማረችም። በታይፔ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በተደጋጋሚ በጎርፍ የሚጠቃ አካባቢ አሳማ እናረባና አትክልት እናለማ ነበር። ወላጆቼ ጠንክሮ መሥራትና ሌሎችን መርዳት ያለውን ትልቅ ጥቅም አስተምረውኛል።
ቤተሰቦችሽ ሃይማኖተኛ ነበሩ?
ቤተሰቤ የታኦይዝም ሃይማኖት ተከታይ ነበር። “ለሰማይ አምላክ” መሥዋዕት እናቀርብ ነበር፤ ይሁንና ስለ እሱ ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። ‘ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ሰዎች ይህን ያህል ራስ ወዳድ የሚሆኑት ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ስለ ታኦይዝምና ስለ ቡድሂዝም የሚገልጹ መጻሕፍትን እንዲሁም የምሥራቅና የምዕራብ አገሮችን ታሪክ አነበብኩ። ከዚህም በላይ ወደ አንድ ወይም ሁለት ቤተ ክርስቲያን ሄጄ የሚሉትን ሰምቻለሁ። ነገር ግን ለጥያቄዎቼ መልስ ማግኘት አልቻልኩም።
ሳይንስ ያጠናሽው ለምንድን ነው?
ሒሳብ እወድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የተለያዩ ነገሮች አወቃቀር በፊዚክስና በኬሚስትሪ ሕጎች የሚገዛበት መንገድ በጣም ያስደንቀኝ ነበር። እጅግ ግዙፍ ከሆነው ጽንፈ ዓለም አንስቶ እስከ ረቂቅ ተሕዋስያን ድረስ ሁሉም ነገር የተዋቀረበት መንገድ በሕግ የሚገዛ ነው። እኔም እነዚህን ሕጎች የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ።
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ትክክል ነው ብለሽ ታምኚ የነበረው ለምንድን ነው?
ይህን ንድፈ ሐሳብ የሚያስተባብል ነገር ተምሬ አላውቅም። ከመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ስማር የኖርኩት የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ የሥነ ሕይወት ሳይንስ ተመራማሪ በመሆኔ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ መቀበል ይጠበቅብኝ ነበር።
የሥነ ሕይወት ሳይንስ ተመራማሪ በመሆኔ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ መቀበል ይጠበቅብኝ ነበር
መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቢ ያነሳሳሽ ምንድን ነው?
በ1996 የድህረ ምረቃ ትምህርቴን ለመከታተል በጀርመን መኖር ጀመርኩ። በሚቀጥለው ዓመት ሲሞን ከምትባል ሴት ጋር ተገናኘሁ። እሷም የይሖዋ ምሥክር ስትሆን መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቼ የሚሰጠውን መልስ አሳየችኝ። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ይገልጻል ስትለኝ የማወቅ ፍላጎቴ ተነሳሳ። በየቀኑ ማለዳ በአሥር ተኩል ተነስቼ ለአንድ ሰዓት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ። ከዚያም በእግር እየሄድኩ ባነበብኩት ነገር ላይ አሰላስላለሁ። በቀጣዩ ዓመት ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤ ጨረስኩ። የትንቢቶቹ ትክክለኛነት በጣም አስደነቀኝ። በጊዜ ሂደት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ እንደሆነ በእርግጠኝነት አመንኩ።
ስለ ሕይወት አመጣጥ የነበረሽ አመለካከት ምን ነበር?
ስለዚህ ጉዳይ በጥሞና ማሰብ በጀመርኩበት በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የሞለኪውል ባዮሎጂ ባለሙያዎች በሕያዋን ነገሮች ውስጥ የሚታየው ኬሚካላዊ ሂደት ከዚያ በፊት ማንም ሰው አስቦት በማያውቀው መጠን እጅግ የተወሳሰበ እንደሆነ መገንዘብ ጀምረው ነበር። እርግጥ ሳይንቲስቶች ሕያው በሆኑ ሕዋሳት ውስጥ ያሉት ፕሮቲኖች በኬሚካላዊ ይዘታቸው እጅግ የተወሳሰቡ እንደሆኑ ካወቁ ረጅም ዘመን አልፏል። አሁን ግን በርካታ ፕሮቲኖች እንዴት አንድ ላይ ተቀናብረው ተንቀሳቃሽ ክፍሎች ያሉት አስደናቂ ማሽን እንደሚያስገኙ እየተረዱ መጥተዋል። አንድ የሞለኪውል ማሽን ከ50 በሚበልጡ ፕሮቲኖች የተገነባ ሊሆን ይችላል። በጣም ያልተወሳሰበ የሚባለው ሕዋስ እንኳ ኃይል ለማመንጨት፣ መረጃ ለማባዛትና ከሕዋሱ የሚወጡትንና ወደ ሕዋሱ የሚገቡትን ነገሮች ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ማሽኖች ያስፈልጉታል።
ታዲያ ምን ድምዳሜ ላይ ደረስሽ?
‘እነዚህ የፕሮቲን ማሽኖች እንዲህ ባለ አስደናቂ ንድፍ የተሠሩት እንዴት ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር። በእነዚያ ዓመታት የሕዋሳት ኬሚካላዊ አወቃቀር ከሚገመተው በላይ የተወሳሰበ መሆኑ በርካታ ሳይንቲስቶችን ተመሳሳይ ጥያቄ እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ሕይወት ባላቸው ሕዋሳት ውስጥ የሚገኙት የሞለኪውል ማሽኖች እጅግ የተወሳሰቡ በመሆናቸው በአጋጣሚ ሊገኙ አይችሉም የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ የያዘ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር። እኔም በሐሳቡ ተስማማሁ። ሕይወት የተገኘው በፍጥረት መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።
‘እነዚህ የፕሮቲን ማሽኖች እንዲህ ባለ አስደናቂ ንድፍ የተሠሩት እንዴት ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር
የይሖዋ ምሥክር የሆንሽው ለምንድን ነው?
ሲሞን የጤና ችግር ቢኖርባትም እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በየሳምንቱ 56 ኪሎ ሜትር ተጉዛ መምጣቷ በጣም ነካኝ። በጀርመን ናዚዎች ዘመን አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ገለልተኝነታቸው ምክንያት በማጎሪያ ካምፖች ታስረው እንደነበረ አወቅኩ። ድፍረታቸው በጣም አስደነቀኝ። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንደነሱ የመሆን ፍላጎት አሳደረብኝ።
በአምላክ ማመንሽ ጠቅሞሻል?
የሥራ ባልደረቦቼ ከቀድሞው ይበልጥ ደስተኛ እንደሆንኩ ይናገራሉ። ያደግኩት በድህነት በመሆኑ የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ነበር፤ ከዚህ የተነሳ ስላደግኩበት አካባቢም ሆነ ስለ ወላጆቼ ተናግሬ አላውቅም። አሁን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት ትምህርት አምላክ ሰዎችን በኑሮ ደረጃቸው እንደማያበላልጥ አውቄያለሁ። እንዲያውም ኢየሱስ ያደገው ምናልባት ከእኔ ቤተሰቦች ባልተናነሰ ድህነት ይኖር በነበረ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አሁን ወላጆቼን እንከባከባለሁ፤ ደግሞም እነሱን ለወዳጆቼ ማስተዋወቅ ያስደስተኛል።