አገሮችና ሕዝቦች
ሞንጎሊያን እንጎብኝ
ጀንጊስ ካን በ12ኛው መቶ ዘመን የኖረ ደፋር ተዋጊ ሲሆን ለታላቁ የሞንጎሊያውያን ግዛት መሠረት ጥሏል። ይህ ግዛት መጀመሪያ ላይ ከነበረው ስፋት ጋር ሲወዳደር የዛሬዋ ሞንጎሊያ በጣም ትንሽ አገር ናት፤ ሩሲያና ቻይና ብቻ የሚያዋስኗት ሞንጎሊያ ምንም የባሕር በር የሌላት ስትሆን ሰዎች ተበታትነው ከሚኖሩባቸው የዓለማችን አገሮች አንዷ ናት።
የሞንጎሊያ መልክዓ ምድር ወንዞችን፣ ጅረቶችን፣ ረጃጅም ተራሮችን፣ በሣር የተሸፈኑ ለጥ ያሉ ሜዳዎችንና ወጣ ገባ የሆኑ ቦታዎችን የያዘ ነው። በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው የሚገኙ የዳይኖሶር ቅሪተ አካላት የተገኙበት ጎቢ በረሃ በስተ ደቡብ በኩል ይገኛል። ከባሕር ጠለል በላይ 1,580 ሜትር ገደማ ላይ የምትገኘውን ሞንጎሊያን የአገሬው ሕዝብ “የሰማያዊ ሰማይ አገር” ብሎ ይጠራታል። ሞንጎሊያ በዓመት ውስጥ ከ250 የሚበልጡ ፀሐያማ ቀናት ስላሏት ይህን ስያሜ ማግኘቷ ተገቢ ነው!
በሞንጎሊያ ውስጥ እጅግ ተቃራኒ የሆነ የአየር ንብረት አለ። በበጋ ወቅት ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሲሆን ክረምት ላይ ደግሞ ከዜሮ በታች እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ ሊያሽቆለቁል ይችላል። በሞንጎሊያ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ
የሚሆኑት ዘላኖች ናቸው። ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን የሚጀምሩት ፍየሎቻቸውን፣ ላሞቻቸውን፣ ግመሎቻቸውንና ፈረሶቻቸውን በማለብ ነው። ሞንጎሊያውያን አብዛኛውን ጊዜ የሚመገቡት የወተት ተዋጽኦና ሥጋ ሲሆን በተለይ የበግ ሥጋ በጣም ይወዳሉ።ሞንጎሊያውያን እንግዳ ተቀባይ ናቸው። ጌር ብለው የሚጠሯቸውን በቀላሉ ከቦታ ቦታ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ድንኳን መሰል መኖሪያዎቻቸውን በር ምንጊዜም ክፍቱን ይተዉታል፤ ይህን የሚያደርጉት ማንኛውም መንገደኛ ገብቶ አረፍ እንዲልና ያስቀመጡለትን ምግብ እንዲበላ ሲሉ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ለእንግዶች ጨው የተጨመረበት ሻይ በወተት ይቀርብላቸዋል።
በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሞንጎሊያውያን የቡዲዝም እምነት ተከታዮች ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ ሃይማኖት የለሽ የሆኑ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የሻማኒዝም፣ የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች አሉ። በአሁኑ ጊዜ ሞንጎሊያ ውስጥ ከ770 ለሚበልጡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩ ከ350 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።