በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጠባቂው ጋር ተባብሮ ማገልገል

ከጠባቂው ጋር ተባብሮ ማገልገል

ከጠባቂው ጋር ተባብሮ ማገልገል

“ጌታ ሆይ፣ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክዬአለሁ።”​—ኢሳይያስ 21:​8

1. ይሖዋ ራሱ የየትኞቹ ታላላቅ ተስፋዎች ምሥክር ነው?

 ይሖዋ አቻ የሌለው የዓላማ አምላክ ነው። ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራው ዓመፀኛ መልአክ፣ አምላክ ስሙን ለማስቀደስና ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚያስተዳድር ክብራማ መንግሥት ለማቋቋም ያለውን ታላቅ ዓላማ ለማክሸፍ የሚያስችል አንዳች አቅም የለውም። (ማቴዎስ 6:​9, 10) በዚህ አገዛዝ ሥር የሰው ልጅ እውነተኛ በረከት ያገኛል። አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” ደስተኛ የሆኑና አንድነት ያላቸው የሰው ልጆች ሰላምና ብልጽግና አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 25:​8፤ 65:​17-25) ይሖዋ ለእነዚህ ታላላቅ ተስፋዎች ራሱ ምሥክር ነው!

2. ይሖዋ የእርሱ ምሥክር እንዲሆኑ ያደረጋቸው ሰዎች እነማን ናቸው?

2 ይሁን እንጂ ታላቁ ፈጣሪ ሰብዓዊ ምሥክሮችም አሉት። በቅድመ ክርስትና ዘመን ከአቤል አንስቶ የጽናትን ሩጫ የሮጡና ብዙውን ጊዜም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱ ‘እንደ ደመና ያሉ ብዙ ምሥክሮች’ ነበሩ። የእነዚህ ምሥክሮች ድንቅ ምሳሌ ዛሬ ላሉት ታማኝ ክርስቲያኖች ማበረታቻ ይሆናል። ደፋር ምሥክር በመሆን በኩል ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። (ዕብራውያን 11:1–12:​2) ለምሳሌ ያህል በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት የሰጠውን የመጨረሻ ምሥክርነት አስታውስ። ኢየሱስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:​37) ከ33 እዘአ አንስቶ እስከዚህ እስከ 2000 እዘአ ድረስ ቀናተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለው ‘ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ’ በድፍረት በመናገር መመሥከራቸውን ቀጥለዋል።​—⁠ሥራ 2:​11

ባቢሎናዊ ቡድኖች

3. ሰይጣን ስለ ይሖዋ እና ስለ ፈቃዱ የሚሰጠውን ምሥክርነት የተቃወመው እንዴት ነው?

3 ባለፉት ሺህ ዓመታት ታላቁ ባላጋራ ሰይጣን ዲያብሎስ የአምላክ ምሥክሮች የሚያሰሙትን ምሥክርነት መና ለማስቀረት ያልሸረበው ተንኮል አልነበረም። ይህ ‘ታላቅ ዘንዶና የቀደመው እባብ’ ‘የሐሰት አባት’ እንደመሆኑ መጠን ‘ዓለሙን በሙሉ ሲያስት’ ኖሯል። በተለይ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ‘የአምላክን ትእዛዝ በሚጠብቁት ላይ’ የማያባራ ውጊያ ከፍቷል።​—⁠ዮሐንስ 8:​44፤ ራእይ 12:​9, 17

4. ታላቂቱ ባቢሎን ሕልውና ለማግኘት የበቃችው እንዴት ነው?

4 ከዛሬ 4, 000 ዓመታት በፊት በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በኋላ ሰይጣን ናምሩድ የተባለ ‘ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ’ አስነሳ። (ዘፍጥረት 10:​9, 10 NW ) የናምሩድ ታላቋ ከተማ ባቢሎን (ባቤል) የአጋንንታዊ ሃይማኖቶች መናኸሪያ ሆነች። ይሖዋ የባቤልን ሕንፃ የሚገነቡትን ሰዎች ቋንቋ በደበላለቀበት ጊዜ ሰዎቹ የሐሰት ሃይማኖታቸውን እንደያዙ በምድር ሁሉ ላይ ተበተኑ። በዚህ መንገድ ባቢሎን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ ለተጠራችው የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ግዛት መነሻ ሆናለች። የራእይ መጽሐፍ ይህ ጥንታዊ የሃይማኖት መዋቅር ጥፋት እንደሚጠብቀውም ይተነብያል።​—⁠ራእይ 17:​5፤ 18:​21

የምሥክሮች ብሔር

5. ይሖዋ ለእርሱ ምሥክር እንዲሆን ያደራጀው ብሔር የትኛው ነበር? ይሁን እንጂ በምርኮ እንዲወሰድ የፈቀደውስ ለምንድን ነው?

5 ከናምሩድ ዘመን በኋላ 500 ዓመታት ገደማ ቆይቶ ይሖዋ የታመነ የነበረውን የአብርሃምን ዝርያዎች የእስራኤል ብሔር ብሎ በማደራጀት በምድር ላይ ምሥክሮቹ ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጓል። (ኢሳይያስ 43:​10, 12) የዚያ ብሔር አባላት የነበሩ ብዙ ግለሰቦች ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የእስራኤል ብሔር በአጎራባቾቹ ብሔራት የሐሰት እምነት በመበከሉ የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ መሆናቸው ቀረና ወደ ሐሰት አምልኮ ዘወር በማለት ለይሖዋ ጀርባቸውን ሰጡ። በዚህ ምክንያት በንጉሥ ናቡከደነፆር የሚመራው የባቢሎን ሠራዊት በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደስዋን በመደምሰስ ብዙዎቹን አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን አጋዛቸው።

6. በትንቢት የተነገረለት ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ያወጀው ምሥራች ምንድን ነው? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነበር?

6 ይህ ለሐሰት ሃይማኖት እንዴት ያለ ታላቅ ድል ነበር! ይሁን እንጂ የባቢሎን የበላይነት ብዙም አልቆየ። ከ200 ዓመታት በፊት ግን ይሖዋ “ሂድ ጉበኛም አቁም፣ የሚያየውንም ይናገር” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። ይህ ጉበኛ መናገር ያለበት መልእክት ምን ነበር? “ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ” የሚል ነው። (ኢሳይያስ 21:​6, 9) ደግሞም በ539 ከዘአበ ትንቢታዊው ቃል በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። ኃያሏ ባቢሎን በመውደቋ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ወዲያው ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ በቅቷል።

7. (ሀ) አይሁዳውያን ከይሖዋ ተግሳጽ ምን ተምረዋል? (ለ) ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን በምን ዓይነት ወጥመድ ወድቀዋል? ውጤቱስ ምን ነበር?

7 ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ከጣዖት አምልኮና ከመናፍስታዊ ሃይማኖቶች መራቅ እንዳለባቸው በቂ ትምህርት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ደግሞ በሌሎች ወጥመዶች ውስጥ ወደቁ። ለአንዳንዶቹ የግሪካውያን ፍልስፍና ወጥመድ ሆኖባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከአምላክ ቃል ይልቅ ሰብዓዊ ወጎችን አስበልጠዋል። የተቀሩት ደግሞ ልባቸው በብሔራዊ ስሜት ተወስዷል። (ማርቆስ 7:​13፤ ሥራ 5:​37) ኢየሱስ ሲወለድ ብሔሩ ዳግም ከንጹሕ አምልኮ ፈቀቅ ብሎ ነበር። ኢየሱስ ለሚያውጀው ምሥራች ምላሽ የሰጡ ግለሰብ አይሁዶች የነበሩ ቢሆንም ብሔሩ በጥቅሉ እርሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። (ዮሐንስ 1:​9-12፤ ሥራ 2:​36) እስራኤል የአምላክ ምሥክር መሆኗ ያከተመ ሲሆን በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም ከነቤተ መቅደስዋ በድጋሚ ጠፍታለች። በዚህ ጊዜ ይህን እርምጃ የወሰደው የሮማ ሠራዊት ነበር።​—⁠ማቴዎስ 21:​43

8. የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ማገልገል የጀመረው የትኛው ቡድን ነበር? ጳውሎስ ለዚህ ቡድን የሰጠው ማስጠንቀቂያ ወቅታዊ የነበረው ለምንድን ነው?

8 ይህ በእንዲህ እንዳለ ክርስቲያኖችን ያቀፈ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተወልዶ ስለ ነበር ይህ የክርስቲያኖች ቡድን በአሕዛብ መካከል የአምላክ ምሥክር ሆኖ ማገልገል ጀመረ። (ገላትያ 6:​16) ሰይጣን አፍታም ሳይቆይ ይህን አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ለመበረዝ ማሴር ጀመረ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በጉባኤዎቹ ውስጥ ኑፋቄያዊ ተጽዕኖዎች መታየት ጀምረዋል። (ራእይ 2:​6, 14, 20) ጳውሎስ የሰጠው የሚከተለው ማስጠንቀቂያ ወቅታዊ ነበር:- “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”​—⁠ቆላስይስ 2:​8

9. ሐዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው ለሕዝበ ክርስትና ብቅ ማለት በር የከፈተው ነገር ምንድን ነው?

9 ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎችን ያቀፈው ሃይማኖት የኋላ ኋላ በግሪካውያን ፍልስፍና፣ በባቢሎናውያን ሃይማኖታዊ ሐሳቦች እንዲሁም ቆየት ብሎ እንደ አዝጋሚ ለውጥና የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት በመሰለው ሰብዓዊ “ጥበብ” ተበርዟል። ይህም ጳውሎስ አስቀድሞ እንደተናገረው ነው። “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኵላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ” ብሎ ነበር። (ሥራ 20:⁠29, 30) ሕዝበ ክርስትና ሕልውና ያገኘችው ከዚህ የክህደት እንቅስቃሴ በመነሳት ነው።

10. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ለሚከናወነው የተበረዘ አምልኮ እጁን የሰጠው ሁሉም ሰው እንዳልነበረ የሚያሳየው የትኛው ማስረጃ ነው?

10 ከልባቸው ለንጹህ አምልኮ ያደሩ ሰዎች ‘ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት መጋደል ነበረባቸው።’ (ይሁዳ 3) ስለ ንጹሕ አምልኮና ስለ ይሖዋ የሚሰጠው ምሥክርነት ጨርሶ ከምድር ገጽ ይጠፋል ማለት ነውን? በፍጹም። ዓመፀኛው ሰይጣንና የእርሱ ሥራ በሙሉ የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ለሚካሄደው የክህደት አምልኮ እጁን የሰጠው ሁሉም ሰው እንዳልነበር ግልጽ ሆኗል። በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ፒትስበርግ ፔንሲልቫኒያ ውስጥ የተደራጀው ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ዛሬ ላለው የአምላክ ምሥክሮች ቡድን አስኳል ሆኗል። እነዚህ ክርስቲያኖች ዛሬ ያለው የዚህ ዓለም ሥርዓት ፍጻሜ እንደቀረበ አሳውቀዋል። ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መሠረት የዚህ ዓለም “መደምደሚያ” አንደኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት በ1914 ጀምሯል። (ማቴዎስ 24:​3, 7 NW ) ሰይጣንና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ ያንን ዓመት ተከትሎ ከሰማይ መባረራቸውን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ አለ። በችግር የተሞላው 20ኛው መቶ ዘመን ሰይጣን የሚያደርገው ሩጫና ክርስቶስ በሰማይ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚያረጋግጡት ምልክቶች አስገራሚ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ቁልጭ ብሎ የታየበት ዘመን ነው።​—⁠ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21፤ ራእይ 12:​10, 12

11. ሰይጣን ምን ሙከራ አድርጎ ነበር? ይሁን እንጂ ሙከራው ያልተሳካለት ለምንድን ነው?

11 ሰይጣን በሰኔ 1918 በብዙ አገሮች ውስጥ ይሰብኩ የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጠራርጎ ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ሞክሯል። የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በመባል የሚታወቀውን ሕጋዊ ኮርፖሬሽናቸውንም ለማጥፋት ሞክሯል። በማኅበሩ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚሠሩ በመጀመሪያ መቶ ዘመን በኢየሱስ ላይ እንደደረሰው በመንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተዋል በሚል የሐሰት ክስ ተወንጅለው ታስረው ነበር። (ሉቃስ 23:​2) ይሁን እንጂ እነዚህ ኃላፊዎች በ1919 ተፈትተው አገልግሎታቸውን መቀጠል ችለዋል። በኋላም ከቀረበባቸው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነዋል።

በጥበቃ ላይ ያለ “ጉበኛ ”

12. ዛሬ ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ክፍል ወይም “ጉበኛ” ማን ነው? ምን ዓይነት አመለካከትስ ነበራቸው?

12 ይሖዋ ‘የፍጻሜው ዘመን’ በጀመረበት ጊዜ ከዓላማው አፈጻጸም ጋር ግንኙነት ያላቸውን ክስተቶች በሚመለከት ለሕዝቡ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ጠባቂ አቁሟል። (ዳንኤል 12:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1) እስከዛሬ ድረስ ይህ የጠባቂ ክፍል ማለትም የአምላክ እስራኤል የተባሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢሳይያስ ስለ ጠባቂው ከተናገረው ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል:- “በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ። ያየውም:- ጌታ ሆይ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፣ ሌሊቱንም በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ . . . ብሎ [“እንደ አንበሳ፣” NW ] ጮኸ።” (ኢሳይያስ 21:​7-9) ሥራውን በቁም ነገር የሚመለከት ጠባቂ ማለት ይሄ ነው!

13. (ሀ) ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ያወጀው መልእክት ምንድን ነው? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃለች ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

13 ይህ ጠባቂ ያየው ነገር ምን ነበር? ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ማለትም የምሥክሮቹ ቡድን “ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ!” ሲል በድጋሚ አውጆአል። (ኢሳይያስ 21:​9) በዚህ ጊዜ አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ከመንበረ ሥልጣንዋ የተወገደችው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ናት። (ኤርምያስ 50:​1-3፤ ራእይ 14:​8) ይህ ምንም አያስገርምም! ታላቁ ጦርነት የተባለለት ይህ ውጊያ የተጀመረው በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ ሲሆን በሁለቱም ወገን የነበሩት ቀሳውስት ለጋ ወጣቶች በጦርነት እሳት ውስጥ እንዲማገዱ በመቀስቀስ እሳቱ ይበልጥ እንዲፋፋም አድርገዋል። እንዴት ያለ አሳፋሪ ተግባር ነው! በ1919 በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ከነበሩበት እንቅስቃሴ አልባ ሁኔታ ተነሥተው እስከ ዛሬም ድረስ የቀጠለውን ምድር አቀፍ የምሥክርነት ዘመቻ ሲያጧጡፉ ታላቂቱ ባቢሎን ልትገታቸው አልቻለችም። (ማቴዎስ 24:​14) በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የእስራኤላውያኑ ነፃ መውጣት የባቢሎንን ውድቀት የሚያሳይ እንደነበር ሁሉ ይህም የታላቂቱን ባቢሎን ውድቀት የሚያበስር ነበር።

14. ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ክፍል በዋነኝነት የተጠቀመበት መጽሔት የትኛው ነው? ይሖዋስ ይህንን ሥራ የባረከው እንዴት ነው?

14 የጠባቂው ክፍል በቅንዓትና ትክክለኛ የሆነውን የማድረግ ጠንካራ ፍላጎት በመያዝ ተግባሩን ሲያከናውን ቆይቷል። በሐምሌ 1879 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በወቅቱ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ይባል የነበረውን ይህን መጽሔት ማሳተም ጀመሩ። ከ1879 እስከ ታኅሣሥ 15, 1938 ድረስ ያሉት እትሞች በሙሉ በመጀመሪያው ገጻቸው ላይ “ጉበኛ ሆይ፣ ሌሊቱ ምን ያህል ነው?​—⁠ኢሳይያስ 21:​11” የሚሉትን ቃላት ይዘው ይወጡ ነበር። aመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላለፉት 120 ዓመታት የዓለምን ሁኔታዎችና የሚያስተላልፉትን ትንቢታዊ መልእክት በታማኝነት ሲከታተል ቆይቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13) የአምላክ ጠባቂ ክፍልና ጓደኞቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” የይሖዋ ሉዓላዊነት በክርስቶስ መንግሥት አማካኝነት የሚረጋገጥበት ጊዜ እንደቀረበ ለሰው ዘር በስፋት ለማወጅ በዚህ መጽሔት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። (ዮሐንስ 10:​16) ይሖዋ ይህን ምሥክርነት ባርኮታልን? መጠበቂያ ግንብ መጀመሪያ በ1879 ከታተመበት 6, 000 ቅጂ ተነሥቶ ዛሬ ከ22, 000, 000 በሚበልጡ ቅጂዎች በ132 ቋንቋዎች የሚታተም ዓለም አቀፍ ስርጭት ያለው መጽሔት ለመሆን በቅቷል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል 121 ቋንቋዎች እኩል ታትመው የሚወጡ ናቸው። በምድር ላይ ካሉት ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ በበለጠ ስፋት የተሠራጨው የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ የሚያደርገው ይህ መጽሔት መሆኑ ምንኛ የተገባ ነው!

ደረጃ በደረጃ የተወሰደ የማጥራት እርምጃ

15. ከ1914 በፊት እንኳ ሳይቀር ደረጃ በደረጃ የተወሰደው የማጥራት እርምጃ ምን ነበር?

15 የክርስቶስ ሰማያዊ ግዛት ከጀመረበት ከ1914 በፊት በነበሩት 40 ዓመታት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እንደ ሕፃናት ማጥመቅ፣ የሰው ነፍስ አለመሞት፣ መንጽሔ፣ እሳታማ ሲኦል እና ሥላሴ ከመሳሰሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ብዙ የሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች ተላቅቀው ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉንም የተሳሳቱ አመለካከቶች ለማጥራት ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጓል። ለምሳሌ ያህል በ1920ዎቹ ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መካከል ብዙዎቹ መስቀልና ዘውድ ያለው ምልክት ደረታቸው ላይ ለጥፈው ይሄዱ የነበረ ሲሆን የገና በዓልንና ሌሎችንም አረመኔያዊ በዓላት ያከብሩ ነበር። ይሁን እንጂ አምልኳቸው ንጹሕ እንዲሆን ማንኛውም የጣዖት አምልኮ ርዝራዥ መወገድ ነበረበት። ለክርስትና እምነትና ለሕይወት መንገዳችን ዋነኛ መሠረት ሊሆን የሚገባው የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ኢሳይያስ 8:​19, 20፤ ሮሜ 15:​4) በአምላክ ቃል ላይ መጨመርም ሆነ ከዚያ አንዳች ማጉደል ትክክል አይደለም።​—⁠ዘዳግም 4:​2፤ ራእይ 22:​18, 19

16, 17. (ሀ) የጠባቂው ክፍል ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ይዟቸው የቆየው የተሳሳቱ አመለካከቶች ምንድን ናቸው? (ለ) የግብጹ ‘መሠዊያና አምድ’ ትክክለኛ ማብራሪያ ምንድን ነው?

16 የዚህን መሠረታዊ ሥርዓት አስፈላጊነት የሚያጎላ አንድ ምሳሌ አለ። በ1886 ሲ ቲ ራስል የዘመናት መለኮታዊ ዕቅድ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሲያሳትም በውስጡ የሰውን ዘር ዕድሜ ከታላቁ የግብጽ ፒራሚድ ጋር የሚያዛምድ አንድ ሠንጠረዥ ነበረ። በ⁠ኢሳይያስ 19:​19, 20 ላይ የተጠቀሰው ዓምድ ይህ ለፈርኦን ኩፉ መታሰቢያ የተሠራው ፒራሚድ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፣ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል። ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምሥክር ይሆናል።” ይህ ፒራሚድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምን ግንኙነት ሊኖረው ይችላል? እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በታላቁ ፒራሚድ ውስጥ ያሉት የአንዳንዶቹ መተላለፊያዎች ርዝመት በዚያ ጊዜ በነበረው ግንዛቤ መሠረት በ⁠ማቴዎስ 24:​21 ላይ ያለውን “ታላቅ መከራ” መጀመሪያና መጨረሻ ያመለክታሉ ተብሎ ይታሰብ ነበር። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱበትን ቀንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ለማስላት ሲሉ የፒራሚዱን የተለያዩ ገጽታዎች መለካትን ሥራዬ ብለው ተያይዘውት ነበር!

17 የኅዳር 15 እና የታኅሣሥ 1, 1928 መጠበቂያ ግንቦች ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠውን ምሥክርነት ለማረጋገጥ በአንድ አረማዊ ፈርኦን የተገነባና የኮከብ ቆጠራን የመሰሉ አጋንንታዊ ምልክቶች ያሉበት የድንጋይ ሐውልት እንደማያስፈልገው ግልጽ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ የድንጋዩ መጽሐፍ ቅዱስ እየተባለ ይጠራ የነበረው ይህ ፒራሚድ ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ቆይቷል። ከዚህ ይልቅ ግን የኢሳይያስ ትንቢት መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው መረዳት ተቻለ። በ⁠ራእይ 11:​8 መሠረት “ግብጽ” የሰይጣንን ዓለም የምታመለክት ምሳሌያዊ መግለጫ ነች። ‘የእግዚአብሔር መሠዊያ’ የተባለው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም እንደ መጻተኞች ሆነው ሲኖሩ የሚያቀርቡትን ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንድናስታውስ ያደርገናል። (ሮሜ 12:​1፤ ዕብራውያን 13:​15, 16) ‘በግብጽ ዳርቻ’ አለ የተባለው ዓምድ “የእውነት ዓምድና መሠረት” የሆነውና “በግብጽ” ማለትም ቅቡዓኑ በቅርቡ ትተውት በሚሄዱት በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ምሥክር የሆነው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​15

18. (ሀ) ይሖዋ ቅን ልብ ላላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነገሮችን ግልጽ ማድረጉን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ ካገኘው ምን ማድረጉ ጥበብ ይሆናል?

18 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ ስለ ትንቢታዊው ቃሉ የሚሰጠንን ግልጽ መረዳት ጨምሮ እውነቱ ይበልጥ ቁልጭ ብሎ እንዲታየን ማድረጉን ይቀጥላል። (ምሳሌ 4:​18) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት አያልፍም ስለ ተባለው ትውልድ፣ ስለ በጎችና ፍየሎች ስለሚገልጸው ምሳሌ፣ ስለ ጥፋት ርኩሰቱና በተቀደሰው ስፍራ ስለሚቆምበት ጊዜ፣ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን፣ ስለ ክርስቶስ ተዓምራዊ መለወጥ እንዲሁም በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኘው የቤተ መቅደስ ራእይ የሚገልጹትን ትምህርቶች በጥልቀት ለመመልከት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተናል። አንዳንድ ጊዜ ማስተካከያ የተደረገባቸውን እንዲህ ያሉ ማብራሪያዎች መረዳት ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የማብራሪያዎቹ ምክንያት በጊዜው ግልጽ ይሆንልናል። አንድ ክርስቲያን በአንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ በሚገባ ግልጽ ሳይሆንለት ከቀረ እንደ ነቢዩ ሚክያስ በትሕትና “የመድኃኒቴን አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ [“እጠብቃለሁ፣” NW ]” ማለቱ እንዴት ጥሩ ይሆናል።​—⁠ሚክያስ 7:​7

19. ቅቡዓን ቀሪዎችና የእነርሱ ተባባሪ የሆኑት ሌሎች በጎች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እንደ አንበሳ ያለ ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው?

19 ጉበኛው “ጌታ ሆይ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜያለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ” ብሎ እንደ አንበሳ እንደ ጮኸ አስታውስ። (ኢሳይያስ 21:​8) ቅቡዓን ቀሪዎቹ የሐሰት ሃይማኖትን በማጋለጥና ሰዎችን ነፃ በሚያወጣው ጎዳና በመምራት በኩል የአንበሳ ዓይነት ድፍረት አሳይተዋል። (ራእይ 18:​2-5) “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደመሆናቸው መጠን መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጽሔቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን በብዙ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል። ይህም ‘በጊዜው የሚቀርብ ምግብ ነው።’ (ማቴዎስ 24:​45) ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡትን እጅግ ብዙ ሰዎች’ በመሰብሰብ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል። እነዚህም ቢሆኑ የመቤዠት ኃይል ባለው የኢየሱስ ደም የነጹና ‘ቀንና ሌሊት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ በማቅረብ የአንበሳ ልብ እንዳላቸው ያሳዩ ሰዎች ናቸው። (ራእይ 7:​9, 14, 15) በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉት ጥቂት ቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮችና ጓደኞቻቸው የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ባለፈው ዓመት ምን ፍሬ አግኝተዋል? የሚቀጥለው ርዕሳችን ይህን የሚዳስስ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከጥር 1, 1939 አንስቶ “እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ​—⁠ሕዝቅኤል 35:​15” በሚል ተቀይሯል።

ታስታውሳለህን?

ይሖዋ በየዘመናቱ ምን ምሥክሮች ነበሩት?

የታላቂቱ ባቢሎን አጀማመር እንዴት ነው?

ይሖዋ ለእርሱ ምሥክር የነበረው ብሔር ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ እና በ70 እዘአ እንድትጠፋ የፈቀደው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ያቆመው ጠባቂ ቡድንና ተባባሪዎቻቸው ምን ዓይነት መንፈስ አሳይተዋል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጌታ ሆይ፣ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜያለሁ”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ጠባቂ ቡድን ተግባሩን በቁም ነገር ያከናውናል