“በወቅቱ በጣም ያስፈልገኝ የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ”
“በወቅቱ በጣም ያስፈልገኝ የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ”
የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከ120 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንፈስ ጭንቀት ይሰቃያሉ። በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉ ሲሆን ከ10 እስከ 20 ሚልዮን የሚሆኑ ደግሞ ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ። በመንፈስ ጭንቀት የሚሰቃዩ ሰዎችን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? በሕክምና ስቃዩን ማስታገስ የሚቻል ሲሆን ከጎናቸው ሆኖ ማበረታታትና ማጽናናትም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ቀጥሎ የቀረበው ከፈረንሳይ የተላከ ደብዳቤ እንደሚያሳየው በመንፈስ ጭንቀት የሚሰቃዩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁዋቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በማንበብ ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት ችለዋል።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕይወት መቀጠሌ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ይሰማኝ ነበር። እንድሞት አምላክን የለመንኩት ሲሆን በውስጤ በድን እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። መመሪያ እንዲሰጠኝ ይሖዋን አጥብቄ ከመማጸኔም በተጨማሪ የ2002 የይሖዋ ምሥክሮችን የዓመት መጽሐፍ ለማንበብ ወሰንኩና በሦስት ቀናት ውስጥ አንብቤ ጨረስኩት። መጽሐፉን ማንበቤ ትልቅ ማበረታቻ የሰጠኝ ሲሆን እምነቴን አጠናክሮልኛል።”
“በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ምርምር አደረግሁ። እነዚህን መጽሔቶች ላለፉት 15 ዓመታት ያለማቋረጥ ሳነብ የነበረ ቢሆንም እንዲህ የመሰለ መንፈስን የሚያነቃቃና የሚያጽናና ትምህርት አገኝባቸዋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። መጽሔቶቹ ዛሬ በቀላሉ ማግኘት የማይቻለውን ፍቅራዊ ማበረታቻ የሚሰጡ በመሆናቸው በወቅቱ በጣም ያስፈልገኝ የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ።”
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 34:18) “ልባቸው” ወይም “መንፈሳቸው የተሰበረ” ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መጽናኛና የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ብሩህ ተስፋ ማግኘት እንደሚችሉ አያጠራጥርም። የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ጭንቀቶች ያሉባቸው ሰዎች አምላክ ካጻፈው የመጽናኛ ምንጭ ጥቅም እንዲያገኙ ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ያሰራጫሉ።