በኢየሱስ ላይ ሞት የፈረደበት ሊቀ ካህን
በኢየሱስ ላይ ሞት የፈረደበት ሊቀ ካህን
በኅዳር ወር 1990 ከጥንታዊው የኢየሩሳሌም ከተማ በስተ ደቡብ በኩል አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ መንገድና መናፈሻ እየሠሩ ያሉ ሰዎች አንድ አስደናቂ ነገር አገኙ። አንድ ትራክተር በአጋጣሚ የአንድን ጥንታዊ የመቃብር ዋሻ ጣሪያ ደረመሰ። ይህ ሰፊ አካባቢ ከአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ የመቃብር ቦታ ሆኖ አገልግሏል። በእርግጥም አርኪኦሎጂስቶች በመቃብሩ ውስጥ ያገኙት ነገር ትኩረት የሚስብ ነው።
በዋሻው ውስጥ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ሬሳቸው በመቃብር ቆይቶ ሥጋቸው ከበሰበሰ በኋላ ዓጽማቸው ወጥቶ የተቀመጠባቸው 12 የሬሳ ሣጥኖች አሉ። ከእነዚህ መካከል ዮሴፍ ባር ቀያፋ (የቀያፋ ልጅ ዮሴፍ) የሚል ስም የተቀረጸበት አንድ በጥሩ ሁኔታ የተሠራ እንዲሁም እስካሁን ከተገኙት ሁሉ የሚበልጥ የሬሳ ሣጥን ይገኛል።
ይህ መቃብር በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሞት እንዲበየንበት ያደረገውን የፍርድ ሂደት የመራው ሊቀ ካህን የተቀበረበት ሊሆን እንደሚችል ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ይህን ሊቀ ካህን “ዮሴፍ የሚባለው ቀያፋ” ሲል ጠርቶታል። ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአጭሩ ቀያፋ ተብሎ ተጠርቷል። ታዲያ ስለ እርሱ ማወቅ ለምን አስፈለገን? ኢየሱስን ለማስገደል ያነሳሳውስ ምንድን ነው?
ቤተሰቡና የቀድሞ ሕይወቱ
ቀያፋ ያገባው የሌላኛውን ሊቀ ካህን ማለትም የሐናን ሴት ልጅ ነበር። (ዮሐንስ 18:13) በጋብቻ ለመጣመር ያቀዱት ምናልባት ከሠርጉ ቀን ከዓመታት በፊት ሊሆን ይችላል፤ ይህም ሁለቱ ቤተሰቦች ወዳጅነታቸው የሰመረ እንደሚሆን እርግጠኛ እስኪሆኑ ድረስ ቆይተዋል ማለት ነው። በሌላ አባባል የካህናት ዘር ስለመሆናቸው የዘር ግንዳቸውን በደንብ ተጠናንተዋል። ሁለቱም ቤተሰቦች ሀብታምና የገዢው መደብ ክፍል የነበሩ ሲሆን ምናልባትም ሀብት ያካበቱት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካላቸው ርስት ሊሆን ይችላል። ሐና የወደፊት አማቹ የፖለቲካ አጋሩ እንደሚሆን በእርግጠኝነት ማወቅ እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። ሐናም ሆነ ቀያፋ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው የሰዱቃውያን ወገን ሳይሆኑ አይቀሩም።—የሐዋርያት ሥራ 5:17
ታዋቂ የሆነ የካህናት ቤተሰብ አባል እንደመሆኑ መጠን ቀያፋ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ከነማብራሪያቸው እንደሚማር የታወቀ ነው። በቤተ መቅደስ ማገልገል የጀመረው በ20 ዓመቱ ሲሆን ሊቀ ካህን የሆነው ግን መቼ እንደሆነ አይታወቅም።
ሊቀ ካህናት እና የካህናት አለቆች
መጀመሪያ ላይ ሊቀ ካህንነት በትውልድ የሚተላለፍ እንዲሁም የዕድሜ ልክ ሹመት ነበር። ይሁን እንጂ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሃስሞናውያን ይህን ቦታ በኃይል ያዙ። a ታላቁ ሄሮድስ ሊቀ ካህናትን በመሾምና በመሻር ከሥልጣኑ በስተ ጀርባ ያለው እርሱ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። በይሁዳ የተሾሙ ሌሎች ሮማውያን ገዥዎችም ተመሳሳይ አሠራር ተከትለዋል።
ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ “የካህናት አለቆች” ብሎ የሚጠራው ቡድን እንዲቋቋም ምክንያት ሆኗል። (ማቴዎስ 26:3, 4) ይህ ቡድን ከቀያፋ በተጨማሪ ልክ እንደ ሐና ከሊቀ ካህንነታቸው የወረዱ ነገር ግን አሁንም በዚሁ ስም የሚጠሩ የቀድሞ ሊቀ ካህናትን ያካተተ ነው። በተጨማሪም ቡድኑ በወቅቱ ያሉትንና የቀድሞዎቹን የካህናት ቤተሰቦች ያጠቃልላል።
ሮማውያን በይሁዳ የሚካሄዱትን ዕለታዊ ጉዳዮች የማስፈጸሙን ሥራ የካህናት አለቆችን ጨምሮ ለአይሁድ የገዢ መደቦች ሰጧቸው። ይህም የሮም መንግሥት ወደ ይሁዳ ብዙ ወታደሮች ሳይልክ አካባቢውን ለመቆጣጠርና ግብር ለመሰብሰብ አስችሎታል። ሮም አይሁዳውያን ባለ ሥልጣናት ሥርዓት እንዲያስከብሩና ጥቅሟን እንዲያስጠብቁላት ትፈልግ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ለሮም ቅኝ ግዛት ጥላቻ ስለነበራቸው የሮም ገዥዎች አይወዷቸውም ነበር። ነገር ግን የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ሲሉ ተባብረው መሥራታቸው ለሁለቱም የሚበጅ ነበር።
በቀያፋ ዘመን ሊቀ ካህኑ የአይሁድ የፖለቲካ መሪም ነበር። የሶርያ ገዥ የነበረው ቄሬኔዎስ በ6 ወይም በ7 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለሐና ይህንን ሹመት ሰጥቶት ነበር። የረቢዎች አፈ ታሪክ እንደሚያሳየው ስግብግብነት፣ ወገናዊነት፣ ዓመጽና ጭቆና የአይሁዳውያን የገዥ መደብ ቤተሰቦች መለያ ምልክት ነበር። አንዲት ጸሐፊ፣ ሊቀ ካህኑ ሐና ‘አማቹ በቤተ መቅደሱ የሥልጣን ተዋረድ ፈጣን እድገት እንዲያደርግ ይፈልግ ነበር። ደግሞም የቀያፋ ሥልጣን እያደገ በሄደ መጠን ለሐና የሚኖረው ጠቀሜታ በዚያው መጠን ይጨምራል’ በማለት ጽፈዋል።
የይሁዳ ገዥ የነበረው ቫሌርዩስ ግራቱስ ሐናን በ15 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ከሥልጣኑ አስወገደው። ከዚያም ሌሎች ሦስት ሰዎች [አንደኛው የሐና ልጅ ነው] በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከታትለው ሥልጣን ያዙ። ቀያፋ ሊቀ ካህናት የሆነው በ18 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ነበር። በ26 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የይሁዳ ገዥ ተደርጎ የተሾመው ጳንጥዮስ ጲላጦስ ለአሥር ዓመት በቆየው የግዛት ዘመኑ ቀያፋን በሥልጣን ላይ እንዲቆይ አድርጎታል። ኢየሱስ ያገለግል በነበረበትም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ የስብከት ሥራቸውን በጀመሩበት ወቅት ቀያፋ በሥልጣን ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ቀያፋ ክርስቲያኖች ለሚሰብኩት መልእክት ጥላቻ ነበረው።
ለኢየሱስና ለሮም መንግሥት የነበረው ፍራቻ
ቀያፋ ኢየሱስን ዓመጽ ቀስቃሽ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ለሰንበት የሚሰጡትን ማብራሪያ አስመልክቶ በጥያቄ ያፋጠጣቸው ከመሆኑም ሌላ ነጋዴዎችንና ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተ መቅደሱ በማባረር ቤተ መቅደሱን “የወንበዴዎች ዋሻ” እንዳደረጉት ተናግሯል። (ሉቃስ 19:45, 46) አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚካሄደውን ንግድ የተቆጣጠሩት የሐና ቤተሰቦች ናቸው ብለው ያምናሉ። ምናልባትም ቀያፋ ኢየሱስን ዝም ማሰኘት የፈለገበት ሌላው ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። የካህናት አለቆች ኢየሱስን ይዘው እንዲያመጡት ወታደሮች ቢልኩም እነርሱ ግን በንግግሩ ከመደነቃቸው የተነሳ ባዶ እጃቸውን ተመለሱ።—ዮሐንስ 2:13-17፤ 5:1-16፤ 7:14-49
አይሁዳውያን ገዥዎች ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው ሲሰሙ ምን እንደተከሰተ ተመልከት። የዮሐንስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- “የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ ‘ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ሥፍራችንንና ዮሐንስ 11:47, 48) የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን የሚመለከተው ለሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ሆነ ለሕዝቡ ሰላም አስጊ እንደሆነ አድርጎ ሲሆን ጲላጦስ ደግሞ አንድ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂ የሚያደርገው እነርሱን ነው። ሮማውያኑ የዓመጽ ንቅናቄ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩት ብዙኃኑን ያሳተፈ ማንኛውም እንቅስቃሴ በአይሁዳውያን ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። ሳንሄድሪን ደግሞ የእነርሱን ጣልቃ ገብነት በምንም መንገድ አይፈልግም።
ሕዝባችንን ይወስዱብናል።’ ” (ቀያፋ፣ ኢየሱስ የተለያዩ ተአምራት መሥራቱን ባይክድም በእርሱ ላይ እምነት ከማዳበር ይልቅ ሥልጣኑንና ክብሩን የማስጠበቅ ፍላጎት ነበረው። ታዲያ የአልዓዛርን ከሞት መነሳት እንዴት ሊቀበል ይችላል? ቀያፋ ሰዱቃዊ እንደመሆኑ መጠን በትንሣኤ አያምንም ነበር!—የሐዋርያት ሥራ 23:8
ቀያፋ አብረውት ለነበሩት ገዥዎች እንዲህ ሲል የተናገረው ነገር ክፉ መሆኑን በግልጽ ያሳያል:- “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።” ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ።”—ዮሐንስ 11:49-53
ቀያፋ የእነዚህን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም ያልተረዳ ቢሆንም ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን ትንቢት መናገሩ ነበር። b የኢየሱስ መሞት ጠቃሚ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ለአይሁዳውያን ብቻ አይደለም። የእርሱ ቤዛዊ መሥዋዕት የሰውን ዘር በሙሉ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለማላቀቅ የሚያስችለውን መንገድ ይከፍታል።
የግድያ ሴራ
የአይሁድ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በቀያፋ ቤት ተሰብስበው ኢየሱስን እንዴት እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ተማከሩ። የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፈለው በመወሰን ረገድ የሊቀ ካህኑ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም። (ማቴዎስ 26:3, 4, 14, 15) ሆኖም የቀያፋ ክፋት አንድ ሰው በማስገደል ብቻ የሚያቆም አልነበረም። “የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤ ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ [በ]ኢየሱስ . . . ያምኑበት ስለ ነበር ነው።”—ዮሐንስ 12:10, 11
ማልኮስ የተባለው የቀያፋ አገልጋይ ኢየሱስን እንዲይዙ ከተላኩት ሰዎች መካከል ነበር። ታስሮ የመጣው ኢየሱስ በመጀመሪያ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ለምርመራ ተወሰደ። በምሽት ለፍርድ መቀመጥ ሕገ ወጥ ድርጊት ቢሆንም ቀያፋ የአይሁድ ሽማግሌዎችን አስቀድሞ ሰብስቧቸው ነበር።—ማቴዎስ 26:57፤ ዮሐንስ 18:10, 13, 19-24
የሐሰት ምሥክሮቹ በኢየሱስ ላይ በሰጡት የምሥክርነት ቃል መስማማት አለመቻላቸው ለቀያፋ እንቅፋት አልሆነበትም። ሊቀ ካህኑ በሴራው የተባበሩት ሰዎች መሲሕ ነኝ ለሚል ለማንኛውም ሰው ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ያውቃል። ስለዚህም ይህ ማዕረግ ይገባኛል ይል እንደሆነ ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስም ከሳሾቹን “በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ” እንደሚያዩት ነገራቸው። ለጽድቅ የቆመ በመምሰል “ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፣ ‘በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል?’ ” በማለት ተናገረ። የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ኢየሱስ ሞት ይገባዋል በማለት ተስማሙ።—ማቴዎስ 26:64-66
የሞት ቅጣቱን ሮማውያን ሊያጸድቁት ይገባል። በሮማውያንና በአይሁዶች መካከል አደራዳሪ ሆኖ ጉዳዩን ለጲላጦስ ያቀረበው ቀያፋ ሳይሆን አይቀርም። ጲላጦስ ኢየሱስን በነፃ ሊያሰናብተው ባሰበ ወቅት “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ከጮኹት የካህናት አለቆች መካከል ቀያፋ ሊኖር ይችላል። (ዮሐንስ 19:4-6) ቀያፋ ኢየሱስን ከሚፈታላቸው ይልቅ አንድ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላቸው ሕዝቡን ሳይገፋፋና “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” በማለት በግብዝነት ከተናገሩት የካህናት አለቆች ጋር ሳይተባበር አይቀርም።—ዮሐንስ 19:15፤ ማርቆስ 15:7-11
ቀያፋ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የሚያሳዩትን መረጃዎች ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። ጴጥሮስንና ዮሐንስን ከዚያም እስጢፋኖስን ተቃውሟል። እንዲሁም በደማስቆ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን እንዲያስር ለሳኦል ሥልጣን ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:11-13፤ የሐዋርያት ሥራ 4:1-17፤ 6:8 እስከ 7:60፤ 9:1, 2) ይሁንና የሶርያ ገዥ የነበረው ቪቴሊየስ በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ቀያፋን ከሥልጣን አወረደው።
የአይሁዳውያን ጽሑፎች ስለ ቀያፋ ቤተሰቦች ክፋት ይገልጻሉ። ለምሳሌ የባቢሎናውያን ታልሙድ ላይ “ወዮልኝ በሃና ቤተሰብ እጅ ላይ የወደቅሁ ቀን፤ ወዮልኝ በኔ ላይ እየተንሾካሾኩ ወይም እያደቡ ነውና” የሚል የምሬት አገላለጽ ተጽፎ ይገኛል። ይህ እሮሮ “የማያፈናፍኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ በምሥጢር የሚያደርጉትን ስብሰባ” እንደሚያመለክት ይታሰባል።
ከቀያፋ ሕይወት ምን ትምህርት እናገኛለን?
አንድ ምሁር የካህናት አለቆቹ “ኃይለኛ፣ መሠሪና ዘዴኛ እንዲሁም ትዕቢተኛ” እንደነበሩ ገልጸዋል። ቀያፋ መሲሑን እንዳይቀበል እንቅፋት የሆነበት ትዕቢት ነው። ስለዚህ ዛሬም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አለመቀበላቸው ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። አንዳንዶች አጥብቀው የሚያምኑባቸውን እምነቶች ትተው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ብዙም ፍላጎት የላቸውም። ሌሎች ደግሞ የምሥራቹ ሰባኪ መሆን ክብራቸውን የሚነካባቸው ይመስላቸዋል። እንዲሁም የክርስትና የአቋም ደረጃዎች ታማኝ ያልሆኑትንና ስግብግቦችን እንዲሸሹ ያደርጓቸዋል።
ቀያፋ ሊቀ ካህን እንደመሆኑ መጠን አይሁዳውያን መሲሑን እንዲቀበሉ መርዳት ይችል ነበር። ነገር ግን ለሥልጣን የነበረው ጥማት በኢየሱስ ላይ ሞት እንዲፈርድ አደረገው። ይህ ተቃውሞ ቀያፋ መቃብር እስከገባበት ዕለት ድረስ ዘልቆ እንደሚሆን ይገመታል። ስለ እርሱ የሚናገረው ዘገባ ስንሞት ትተነው የምንሄደው አጽማችንን ብቻ አለመሆኑን ያሳያል። እኛም በተግባራችን በአምላክ ዘንድ ጥሩ ወይም መጥፎ ስም ትተን እናልፋለን፤ ይህን ደግሞ ልንሽረው አንችልም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሃስሞናውያን ታሪክ በሰኔ 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-30 ላይ ወጥቷል።
b ይሖዋ ከዚህ ቀደም፣ ክፉ የነበረው በለዓም ስለ እስራኤላውያን ትክክለኛ ትንቢት እንዲናገር አድርጓል።—ዘኍልቍ 23:1 እስከ 24:24
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀያፋ ልጅ ዮሴፍ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ የተገኘው የሬሳ ሣጥን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የሬሳ ሣጥኑ፣ ጽሑፉ እና ከጀርባ በኩል የሚታየው ዋሻ:- Courtesy of Israel Antiquities Authority