በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በክርስቶስ ውስጥ በሚገባ የተሰወረውን’ ውድ ሀብት ፈልጎ ማግኘት

‘በክርስቶስ ውስጥ በሚገባ የተሰወረውን’ ውድ ሀብት ፈልጎ ማግኘት

‘በክርስቶስ ውስጥ በሚገባ የተሰወረውን’ ውድ ሀብት ፈልጎ ማግኘት

“የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው።”—ቆላ. 2:3

1, 2. (ሀ) ሀዋርድ ካርተር በ1922 ምን ቅርሶች አገኙ? እነዚህ ቅርሶች በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት የት ነው? (ለ) የአምላክ ቃል ለሰው ልጆች በሙሉ ምን ግብዣ አቅርቧል?

አብዛኛውን ጊዜ አንድ የተደበቀ ሀብት ሲገኝ ጉዳዩ ትልቅ ዜና ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ እንግሊዛዊው የአርኪኦሎጂ ተመራማሪ ሀዋርድ ካርተር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በጣም አስቸጋሪ በሆነ የአየር ንብረት ትጋት በተሞላበት መንገድ ፍለጋ ሲያካሂዱ ከቆዩ በኋላ በ1922 አንድ አስደናቂ ነገር አገኙ። እኚህ ተመራማሪ ያገኙት፣ በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኘውንና በውስጡ ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የያዘውን የፈርዖን ቱታንግካመንን መቃብር ነበር።

2 ካርተር ያገኙት የተቀበረ ሀብት አስደናቂ ቢሆንም ካገኟቸው ቅርሶች አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት በሙዚየሞች ውስጥ አሊያም በአንዳንድ ግለሰቦች እጅ ነው። እነዚህ ነገሮች ከታሪክ ወይም ከሥነ ጥበብ አንጻር አንዳንድ ጥቅሞች ቢኖሯቸውም ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በተያያዘ ያን ያህል ጠቀሜታ የላቸውም። ከዚህ በተለየ መልኩ፣ የአምላክ ቃል ለሕይወታችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ውድ ሀብት እንድንፈልግ ግብዣ አቅርቦልናል። ይህ ግብዣ የቀረበው ለሁሉም ሰው ሲሆን የሚያስገኘው በረከትም ከማንኛውም ቁሳዊ ሀብት የበለጠ ነው።—ምሳሌ 2:1-6ን አንብብ።

3. የይሖዋ አምላኪዎች እንዲፈልጓቸው የተጋበዙት ውድ ሀብቶች ጠቃሚ የሆኑት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

3 የይሖዋ አምላኪዎች እንዲፈልጓቸው የተጋበዙት ውድ ሀብቶች ምን ጠቀሜታ እንዳላቸው እስቲ እንመልከት። ከእነዚህ ሀብቶች መካከል አንዱ ‘ይሖዋን መፍራት’ ሲሆን ይህም አደገኛ በሆነው በዚህ ዘመን ጥበቃና ከለላ ይሆንልናል። (መዝ. 19:9) ‘አምላክን ማወቅ’ ማንኛውም የሰው ልጅ ሊያገኘው ከሚችለው ሁሉ የላቀ ክብር ይኸውም በግለሰብ ደረጃ ከልዑሉ አምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት መብት ያስገኛል። ከአምላክ የምናገኘው ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋልም ውድ ሀብት ሲሆን እንዲህ ያለውን ሀብት ማግኘታችን በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ችግሮችና አስጨናቂ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ያስችለናል። (ምሳሌ 9:10, 11) ታዲያ እንዲህ ያሉትን ውድ ሀብቶች እንዴት ማግኘት እንችላለን?

ውድ የሆነውን መንፈሳዊ ሀብት ፈልጎ ማግኘት

4. ውድ የሆነውን መንፈሳዊ ሀብት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

4 የተቀበሩ ሀብቶችን ለማግኘት እዚህም እዚያም ከሚዋትቱት የአርኪኦሎጂ ባለሞያዎችና ሌሎች ተመራማሪዎች በተቃራኒ እኛ ውድ የሆነው መንፈሳዊ ሀብት የት እንደሚገኝ ጠንቅቀን እናውቃለን። የተቀበረ ሀብት የሚገኝበትን ቦታ እንደሚጠቁም ካርታ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም አምላክ ቃል የገባልንን ውድ ሀብት የምናገኝበትን ትክክለኛውን ቦታ ያመለክተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው” ብሏል። (ቆላ. 2:3) ይህንን ጥቅስ ስናነብ የሚከተሉት ጥያቄዎች ወደ አዕምሯችን ይመጡ ይሆናል፦ ‘ይህንን ውድ ሀብት መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው? ይህ ሀብት በክርስቶስ ውስጥ “ተሰውሮ የሚገኘው” እንዴት ነው? ልናገኘው የምንችለውስ እንዴት ነው?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሐዋርያው የተናገረውን ሐሳብ በጥልቀት እንመርምር።

5. ጳውሎስ ውድ ስለሆነ መንፈሳዊ ሀብት መጻፍ ያስፈለገው ለምን ነበር?

5 ጳውሎስ ከላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው በቆላስይስ ለሚገኙት የእምነት ባልንጀሮቹ ነበር። ሐዋርያው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች “ልባቸው እንዲጽናና” እንዲሁም “ስምም ሆነው በፍቅር እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ” ሲል ትግል እያደረገ መሆኑን ገልጾላቸዋል። (ቆላስይስ 2:1, 2ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ያህል የተጨነቀው ለምን ነበር? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው የግሪካውያንን ፍልስፍናዎች የሚያስፋፉ ወይም እንደገና የሙሴን ሕግ መጠበቅን የሚያበረታቱ አንዳንድ የጉባኤው አባላት በቆላስይስ በሚገኙት ወንድሞች ላይ ተጽዕኖ አድርገውባቸው ሊሆን እንደሚችል ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም እንደሚከተለው በማለት ወንድሞችን አስጠንቅቋቸዋል፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላ. 2:8

6. ጳውሎስ ለሰጠው ምክር ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

6 በዛሬው ጊዜም ሰይጣንና ክፉ የሆነው የእሱ ሥርዓት ተመሳሳይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይሞክራሉ። የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብና በሰብዓዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ያተኮረ ሕይወት መምራት የሚለውን አመለካከት ጨምሮ ሌሎች ዓለማዊ ፍልስፍናዎች የሰዎችን አስተሳሰብ፣ ሥነ ምግባር፣ ግብ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ ይቀርጹታል። ሰይጣን ታዋቂ በሆኑ ክብረ በዓላት በመጠቀምም ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን አብዛኞቹ ታዋቂ በዓላት ደግሞ ምንጫቸው የሐሰት ሃይማኖት ነው። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የተሳሳቱ ሥጋዊ ምኞቶችን ለማርካት የሚያስችሉ ነገሮችን የሚያቀርብ ሲሆን በኢንተርኔት የሚተላለፉት አብዛኞቹ ነገሮች ለወጣቶችም ሆነ ለአዋቂዎች በጣም አደገኛ ናቸው። እንደነዚህ ላሉት የዓለምን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ነገሮች ዘወትር የተጋለጥን መሆናችን ይሖዋ ለሚሰጠን መመሪያ ባለን አመለካከትና ዝንባሌ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ይህም እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀን እንዳንይዝ እንቅፋት ይሆንብናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19ን አንብብ።) እንግዲያው በሰይጣን ማታለያዎች ላለመውደቅ ከፈለግን ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ምን ትርጉም እንዳለው መረዳት ብሎም ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርብን ግልጽ ነው።

7. ጳውሎስ የትኞቹ ሁለት ነገሮች የቆላስይስ ክርስቲያኖችን ሊረዷቸው እንደሚችሉ ተናግሯል?

7 እስቲ ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የጻፈውን ምክር መለስ ብለን እንመልከት። ሐዋርያው የእነዚህ ክርስቲያኖች ሁኔታ እንዳሳሰበው ከገለጸ በኋላ ለመጽናናትና በፍቅር አንድ ለመሆን የሚረዷቸውን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል። በመጀመሪያ፣ እውነትን በተመለከተ ስላላቸው ግንዛቤ “ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ” መሆን እንዳለባቸው ገልጿል። እምነታቸው በተረጋገጠ ነገር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከፈለጉ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸው ግንዛቤ ትክክለኛ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ነበረባቸው። (ዕብ. 11:1) ጳውሎስ በመቀጠል ‘ስለ አምላክ ቅዱስ ሚስጥር ትክክለኛ እውቀት’ መቅሰም እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሷል። እነዚያ ክርስቲያኖች ስለ እውነት መሠረታዊ ነገሮችን ብቻ ከማወቅ አልፈው ስለ አምላክ ጥልቅ ነገሮች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባ ነበር። (ዕብ. 5:13, 14) ለቆላስይስ ክርስቲያኖችም ሆነ በዛሬው ጊዜ ላለነው የሚሆን እንዴት ያለ ጠቃሚ ምክር ነው! ይሁን እንጂ ስለ እውነት ያለንን ግንዛቤ በተመለከተ እርግጠኞች መሆን እንዲሁም ስለ አምላክ ቅዱስ ሚስጥር ትክክለኛ እውቀት መቅሰም የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ “የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው” የሚለውን ጥልቅ ትርጉም ያለው ሐሳብ በተናገረ ጊዜ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚረዳንን ቁልፍ ጠቁሞናል።

በክርስቶስ ውስጥ ‘ተሰውሮ የሚገኝ’ ውድ ሀብት

8. ‘በክርስቶስ ውስጥ ተሰውሯል’ የሚለው አባባል ምን ማለት እንደሆነ አብራራ።

8 የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ ‘ተሰውሯል’ ሲባል ማንኛውም ሰው ይህንን ሀብት ሊያገኘው አይችልም ማለት አይደለም። ይልቁንም ይህንን ሀብት ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረግ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማተኮር እንደሚኖርብን የሚጠቁም ነው። ይህም ኢየሱስ ስለ ራሱ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው፦ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ. 14:6) አዎን፣ የአምላክን እውቀት ለማግኘት የኢየሱስ እርዳታና መመሪያ ያስፈልገናል።

9. ኢየሱስ ምን ሚና ይጫወታል?

9 ኢየሱስ “መንገድ” ብቻ ሳይሆን “እውነትና ሕይወት” ጭምር እንደሆነ ተናግሯል። ይህም ወደ አብ ለመቅረብ የሚረዳ መንገድ ከመሆን ያለፈ የላቀ ሚና እንደሚጫወት ያመለክታል። ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲረዱና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በመርዳት ረገድም የሚጫወተው ሚና አለ። በእርግጥም በኢየሱስ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙት መንፈሳዊ ሀብቶች በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥቅም አላቸው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም እነዚህን ሀብቶች በጥንቃቄ ሊፈልጓቸው ይገባል። ከወደፊት ተስፋችን እንዲሁም ከአምላክ ጋር ካለን ዝምድና ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን አንዳንዶቹን መንፈሳዊ እንቁዎች እስቲ እንመርምር።

10. ከቆላስይስ 1:19 እና 2:9 ስለ ኢየሱስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 “የመለኮታዊው ባሕርይ ሙላት ሁሉ በአካላዊ ሁኔታ የሚኖረው በእሱ ውስጥ ነው።” (ቆላ. 1:19፤ 2:9) ኢየሱስ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት በመኖሩ ከማንም ይበልጥ የአባቱን ባሕርያትና ፈቃድ ያውቃል። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፣ አባቱ ያስተማረውን ነገር ለሌሎች ያስተማረ ከመሆኑም ሌላ ከአባቱ ባገኘው ሥልጠና ያዳበራቸውን ባሕርያት በሕይወቱ አንጸባርቋል። ኢየሱስ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሎ መናገር የቻለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 14:9) የአምላክ ጥበብና እውቀት በሙሉ የተደበቀው ወይም የሚኖረው በክርስቶስ ውስጥ በመሆኑ ስለ ይሖዋ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ስለ ኢየሱስ የቻልነውን ያህል በጥልቀት መማር ነው።

11. ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ምን ሚና ይጫወታል?

11 “ትንቢት የሚነገርበት ዓላማ ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነው።” (ራእይ 19:10) ይህ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር በተያያዘ ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ መሆኑን ያመለክታል። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ይሖዋ ከተናገረው የመጀመሪያ ትንቢት አንስቶ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እስከሚገኙት አስደናቂ ራእዮች ድረስ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በትክክል መረዳት የምንችለው ኢየሱስ ከመሲሐዊው መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚጫወተውን ሚና ከተገነዘብን ብቻ ነው። ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ለማይቀበሉ ሰዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ትንቢቶች አብዛኞቹ እንቆቅልሽ የሚሆኑባቸው ለዚህ ነው። ስለ መሲሑ የሚናገሩ በርካታ ትንቢቶችን የያዙትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የማይቀበሉ ሰዎችም ኢየሱስን በምድር ላይ የኖረ አንድ ታላቅ ሰው እንደሆነ ብቻ አድርገው የሚመለከቱት ለዚህ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ግን ስለ ኢየሱስ ማወቃቸው ወደፊት የሚፈጸሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ትርጉም ለመረዳት ያስችላቸዋል።—2 ቆሮ. 1:20

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” የሆነው እንዴት ነው? (ለ) የክርስቶስ ተከታዮች ከመንፈሳዊ ጨለማ ነፃ መውጣታቸው ምን ግዴታ አስከትሎባቸዋል?

12 “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።” (ዮሐ. 8:12፤ 9:5) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ዘመናት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ለኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 9:2) ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ በጀመረበት ወቅት የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ሐዋርያው ማቴዎስ ገልጿል። (ማቴ. 4:16, 17) የኢየሱስ ስብከት፣ ሰዎች መንፈሳዊ ብርሃን እንዲወጣላቸው ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርት ነፃ እንዲወጡ አስችሏቸዋል። ኢየሱስ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐ. 1:3-5፤ 12:46

13 ከበርካታ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ በአንድ ወቅት ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን የጌታ በመሆናችሁ ብርሃን ናችሁ። የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:8) ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ጨለማ ነፃ በመውጣታቸው የብርሃን ልጆች ሆነው የመመላለስ ግዴታ አለባቸው። ይህም ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት ለተከታዮቹ ከሰጠው ምክር ጋር የሚስማማ ነው። (ማቴ. 5:16) በኢየሱስ ውስጥ ላገኘሃቸው ውድ የሆኑ መንፈሳዊ ሀብቶች አድናቆት አለህ? ይህ አድናቆትህስ በንግግርህም ሆነ መልካም በሆነው ክርስቲያናዊ አኗኗርህ እነዚህን ሀብቶች ለሰዎች ለማሳወቅ ያነሳሳሃል?

14, 15. (ሀ) በጥንት ዘመን በጎችና ሌሎች እንስሳት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ምን ሚና ነበራቸው? (ለ) ኢየሱስ “የአምላክ በግ” በመሆን በሚጫወተው ሚና፣ ወደር የማይገኝለት ውድ ሀብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ “የአምላክ በግ” ነው። (ዮሐ. 1:29, 36) በጥንት ዘመን ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘትና ወደ አምላክ ለመቅረብ በጎችን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በተዘጋጀበት ወቅት ይሖዋ በልጁ ላይ ምንም ጉዳት እንዳያደርስ ከነገረው በኋላ በእሱ ምትክ መሥዋዕት የሚሆን በግ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 22:12, 13) እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ በወጡበት ጊዜም ‘የይሖዋን ፋሲካ’ ሲያከብሩ አንድ በግ አርደው ደሙን በበሩ መቃንና ጉበን ላይ መቀባት ነበረባቸው። (ዘፀ. 12:1-13) ከዚህም በተጨማሪ የሙሴ ሕግ፣ በጎችንና ፍየሎችን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ ያዝዝ ነበር።—ዘፀ. 29:38-42፤ ዘሌ. 5:6, 7

15 ይሁንና ከእነዚህ መሥዋዕቶች አንዱም ቢሆን፣ እንዲያውም ሰዎች ያቀረቡት ማንኛውም መሥዋዕት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ሙሉ በሙሉ ነፃ ሊያወጣ አልቻለም። (ዕብ. 10:1-4) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” ነው። ይህ ሐቅ ብቻ እንኳ ኢየሱስን እስከ ዛሬ ከተገኘው ከየትኛውም ቁሳዊ ሀብት የላቀ ውድ ሀብት እንዲሆን ያደርገዋል። እንግዲያው ጊዜ ወስደን ስለ ቤዛው ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግና በዚህ ድንቅ ዝግጅት ላይ እምነት ማሳደር ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ታላቅ በረከትና ሽልማት የማግኘት ይኸውም ‘የትንሹ መንጋ’ አባላት ከሆንን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ክብር የመጎናጸፍ መብት፣ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ከሆንን ደግሞ በምድር ላይ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የመውረስ ተስፋ ይኖረናል።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 6:40, 47፤ 10:16

16, 17. ኢየሱስ “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ” በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ኢየሱስ “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ” ነው። (ዕብራውያን 12:1, 2ን አንብብ።) ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ እምነትን አስመልክቶ ግሩም ማብራሪያ ሰጥቷል፤ በዚህ ምዕራፍ ላይ ስለ እምነት አጠር ያለ ፍቺ የሰጠ ከመሆኑም ሌላ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ እና ረዓብ ያሉ በእምነታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶችን ጠቅሷል። ጳውሎስ ይህንን ከተናገረ በኋላ ክርስቲያኖች “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት [እንዲመለከቱ]” አጥብቆ አሳስቧል። ሐዋርያው፣ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያሳሰበው ለምን ነበር?

17 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት እነዚያ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት የነበራቸው ቢሆንም አምላክ የገባውን ቃል በመሲሑ እና በመንግሥቱ አማካኝነት እንዴት እንደሚፈጽመው የተሟላ እውቀት አልነበራቸውም። ከዚህ አንጻር እምነታቸው ሙሉ አልነበረም። ይሖዋ ስለ መሲሑ የሚገልጹትን በርካታ ትንቢቶች እንዲጽፉ የተጠቀመባቸው ሰዎችም እንኳ የጻፉት ነገር ምን ትርጉም እንዳለው የተሟላ ግንዛቤ አልነበራቸውም። (1 ጴጥ. 1:10-12) እምነት፣ ፍጹም ወይም ሙሉ መሆን የሚችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው። እንግዲያው ኢየሱስ “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ” በመሆን የሚጫወተውን ሚና በግልጽ መረዳታችንና መቀበላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ሳታቋርጡ ፈልጉ

18, 19. (ሀ) በክርስቶስ ውስጥ ተሰውረው የሚገኙት ሌሎች መንፈሳዊ እንቁዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ስለ ኢየሱስ መመርመራችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

18 አምላክ ከሰው ልጆች መዳን ጋር በተያያዘ ባለው ዓላማ ውስጥ ኢየሱስ ከሚጫወታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሚናዎች መካከል እስካሁን የተመለከትነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። በክርስቶስ ውስጥ ተሰውረው የሚገኙ ሌሎች መንፈሳዊ እንቁዎችም አሉ። እነዚህን እንቁዎች ፈልገን ማግኘታችን የሚያስደስተን ከመሆኑም ሌላ በርካታ ጥቅሞች ያስገኝልናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን ‘የሕይወት ዋና ወኪል’ እንዲሁም እየበራ የሚሄድ “የንጋት ኮከብ” በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 3:15፤ 5:31፤ 2 ጴጥ. 1:19) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “አሜን” የሚለውን ቃል ኢየሱስን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ የሚጫወታቸው እነዚህ ሚናዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው እንዲሁም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ታውቃለህ? ኢየሱስ “ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ” ብሏል።—ማቴ. 7:7

19 በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኢየሱስን ያህል ሕይወቱ ትልቅ ትርጉም ያለው እንዲሁም ከሰው ልጆች ዘላለማዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ወሳኝ ሚና የተጫወተ ሰው ኖሮ አያውቅም። ማንኛውም ሰው ልባዊ ጥረት ካደረገ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል ውድ የሆነ መንፈሳዊ ሀብት በኢየሱስ ውስጥ ተሰውሯል። ‘በክርስቶስ ውስጥ በሚገባ የተሰወረውን’ ይህን ውድ ሀብት ፈልገህ በማግኘት ደስታና በረከት እንድታጭድ ምኞታችን ነው።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያኖች እንዲፈልጉ የተጋበዙት የትኛውን ሀብት ነው?

• ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች የሰጠው ምክር በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ክርስቲያኖችም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• በክርስቶስ ውስጥ ‘ተሰውሮ የሚገኝ’ ውድ የሆነ መንፈሳዊ ሀብት ከተባሉት መካከል አንዳንዶቹን አብራራ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተቀበረ ሀብት የሚገኝበትን ቦታ እንደሚጠቁም ካርታ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም በክርስቶስ ውስጥ ‘በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘውን’ ውድ ሀብት ለማግኘት ይረዳናል