የሕይወቴን አቅጣጫ የለወጡ ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች
የሕይወቴን አቅጣጫ የለወጡ ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች
ጆርጅ ዎረንቸክ እንደተናገረው
በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በሰማችሁት ነገር ልባችሁ በጥልቅ በመነካቱ በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳችሁበት ጊዜ አለ? እኔ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኛል። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በተለይ ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች የሕይወቴን አቅጣጫ እንደለወጡት ይሰማኛል። የመጀመሪያው የአውራጃ ስብሰባ ፍርሃቴ እንዲቀንስ፣ ሁለተኛው ባለኝ ረክቼ እንድኖር፣ ሦስተኛው ደግሞ አገልግሎቴን እንዳሰፋ ረድቶኛል። ስላደረግኳቸው ለውጦች ከመናገሬ በፊት ግን እነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች ከመደረጋቸው ከዓመታት በፊት የተካሄዱ ከልጅነት ሕይወቴ ጋር የተያያዙ ክንውኖችን ላውጋችሁ።
የተወለድኩት በ1928 ሲሆን በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት ሦስት ልጆች የመጨረሻው ነኝ። ማርጂ እና ኦልጋ የሚባሉት እህቶቼና እኔ ያደግነው በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ጀርሲ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሳውዝ ባውንድ ብሩክ በተባለች በወቅቱ ወደ 2,000 ገደማ ነዋሪዎች የነበሯት ከተማ ውስጥ ነው። ድሆች ብንሆንም እናታችን ለጋስ ነበረች። ገንዘብ አግኝታ ለየት ያለ ምግብ ስታዘጋጅ ሁልጊዜ ለጎረቤቶቻችን ታካፍል ነበር። የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለሁ የሃንጋሪ ቋንቋ የምትናገር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጥታ እናቴን አነጋገረቻት፤ ይህች ሴት የምትናገረው የእናቴን የአፍ መፍቻ ቋንቋ መሆኑ እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንድትሰማ አነሳሳት። ከጊዜ በኋላ፣ በርታ የተባለች በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ እህት እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት የይሖዋ አገልጋይ እንድትሆን ረዳቻት።
ከእናቴ በተለየ እኔ ፈሪና በራሴ የማልተማመን ሰው ነበርኩ። ይባስ ብሎ ደግሞ እናቴ ዝቅ የሚያደርግ ነገር ትናገረኝ ነበር። በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ዓይኖቼ እንባ አቅርረው “ሁልጊዜ የምትነቅፊኝ ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቋት፤ እናቴም እንደምትወደኝ ሆኖም ልታሞላቅቀኝ እንደማትፈልግ ነገረችኝ። እናቴ ይህን ያደረገችው ለእኔ መልካም በማሰብ ቢሆንም ምስጋና አለማግኘቴ ለራሴ ዝቅ ያለ ግምት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።
ብዙ ጊዜ በደግነት የምታነጋግረኝ ጎረቤታችን አንድ ቀን ከልጆቿ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰንበት ትምህርት ቤት እንድሄድ ጠየቀችኝ። እንዲህ ማድረጌ ይሖዋን እንደሚያሳዝነው ባውቅም ይህችን ደግ ጎረቤታችንን እንዳላስከፋት ፈራሁ። በዚህም የተነሳ ለበርካታ ወራት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፤ በእርግጥ እንዲህ ማድረጌ ያሳፍረኝ ነበር። በትምህርት ቤትም በሰው ፍርሃት ምክንያት ሕሊናዬን የሚረብሸኝ ነገር አደርግ ነበር። ኃይለኛ የነበረው የትምህርት ቤታችን ርዕሰ መምህር፣ መምህራኑ ሁሉም ተማሪዎች ለባንዲራ ሰላምታ እንዲሰጡ እንዲያደርጉ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። እኔም ለባንዲራ ሰላምታ እሰጥ ነበር። ለአንድ ዓመት ገደማ እንዲህ ማድረጌን ቀጠልኩ፤ ከዚያ በኋላ ግን ነገሮች ተለወጡ።
ደፋር እንድሆን የሚረዳ ትምህርት አገኘሁ
በ1939 በቤታችን የመጽሐፍ ጥናት መደረግ ጀመረ። ቤን ሚስካልስኪ የተባለ አንድ ወጣት አቅኚ መጽሐፍ ጥናቱን ይመራ ነበር። እኛም ትልቁ ቤን እያልን የምንጠራው ሲሆን ለዚህም ምክንያት ነበረን። ቤን የቤታችንን ዋና በር ያህል ረጅምና ግዙፍ ሆኖ ይታየኝ ነበር። ሰውነቱ ሲታይ የሚያስፈራ ቢመስልም በጣም ደግ ሰው ነበር፤ በፊቱ ላይ የሚነበበው ፈገግታ በቀላሉ እንድቀርበው አደረገኝ። በመሆኑም ቤን አብሬው አገልግሎት እንድወጣ ሲጠይቀኝ በደስታ ተስማማሁ። ከቤን ጋር ጓደኛሞች ሆንን። በማዝንበት
ወቅት ቤን አንድ አሳቢ ወንድም ታናሹን በሚያነጋግርበት መንገድ ያዋራኝ ነበር። ይህ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ነበረው፤ እያደር ቤንን በጣም ወደድኩት።ቤን በ1941 በሴይንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ ወደሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ አብረነው በመኪናው እንድንሄድ ቤተሰባችንን ጠየቀን። በዚህ ወቅት ምን ያህል ደስ እንዳለኝ መገመት ትችላላችሁ! ከቤቴ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ርቄ ሄጄ አላውቅም፤ አሁን ግን ከ1,500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ልጓዝ ነው! ይሁንና በሴይንት ሉዊስ አንዳንድ ችግሮች ተከሰቱ። በዚያ ያሉት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በቤታቸው ለመቀበል ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም የአካባቢው ቀሳውስት ምዕመናኖቻቸውን ይህን እንዳያደርጉ አዝዘዋቸው ነበር። በመሆኑም ብዙዎቹ ሐሳባቸውን ቀየሩ። እኛ እንድናርፍ የተመደብንበት ቤተሰብ ማስፈራሪያ ቢደርስበትም ተቀብሎ አስተናገደን። የዚህ ቤተሰብ አባላት እኛን ለመቀበል የገቡትን ቃል ማጠፍ እንዳልፈለጉ ነገሩን። ድፍረታቸው አስገረመኝ።
በዚያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ እህቶቼ ተጠመቁ። በዚያን ዕለት፣ ከብሩክሊን ቤቴል የመጣው ወንድም ራዘርፎርድ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ንግግር የሰጠ ሲሆን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚፈልጉ ልጆች በሙሉ ከመቀመጫቸው ተነስተው እንዲቆሙ ጠየቀ። እኔን ጨምሮ ወደ 15,000 ገደማ የምንሆን ልጆች ተነስተን ቆምን። ከዚያም በስብከቱ ሥራ በተቻለን መጠን ለመካፈል የምንፈልግ ሁሉ “አዎ” እንድንል ጠየቀን። እኔም ከሌሎቹ ልጆች ጋር በመሆን ከፍ ባለ ድምፅ “አዎ!” አልኩ። በዚህ ጊዜ ጭብጨባው እንደ ነጎድጓድ አስተጋባ። በስብከቱ ሥራ የመካፈል ቅንዓት በውስጤ ተቀጣጠለ።
ከስብሰባው በኋላ አንድ ወንድምን ለመጠየቅ ወደ ዌስት ቨርጂኒያ ሄድን። ይህ ወንድም በአንድ ወቅት እያገለገለ እያለ በቁጣ የተሞሉ በርካታ ሰዎች እንደደበደቡትና በሰውነቱ ላይ ሬንጅ ካፈሰሱ በኋላ ላባ እንዳደረጉበት ነገረን። ከዚያም “መስበኬን ግን አላቋርጥም” አለ። ወንድም ተሞክሮውን ሲነግረን በአግራሞት ተውጬ አዳመጥኩት። ወንድምን ተሰናብተነው ስንሄድ የዳዊት ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ለእኔ እንደ ጎልያድ የሆነውን የትምህርት ቤታችንን ርዕሰ መምህር ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበርኩ።
ወደ ትምህርት ቤት ስመለስ ርዕሰ መምህሩን አነጋገርኩት። እሱም በንዴት አፈጠጠብኝ። ይሖዋ እንዲረዳኝ በልቤ ከጸለይኩ በኋላ እንዲህ አልኩት፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። ከአሁን በኋላ ለባንዲራ ሰላምታ አልሰጥም!” በዚህ ጊዜ ጸጥታ ሰፈነ። ርዕሰ መምህሩ ቀስ ብሎ ከመቀመጫው በመነሳት ወደ እኔ መጣ። ፊቱ በንዴት ቲማቲም መስሎ ነበር። “ለባንዲራው ሰላምታ ስጥ፤ አለዚያ ትባረራለህ!” በማለት አንቧረቀብኝ። በዚህ ጊዜ ግን አቋሜን አላላላሁም፤ በውስጤ ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ደስታ ተሰማኝ።
የሆነውን ነገር ለቤን ለመንገር በጣም ቸኩዬ ነበር። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ቤንን ሳገኘው ጮክ ብዬ “ከትምህርት ቤት ተባረርኩ! ለባንዲራ ሰላምታ አልሰጠሁም!” አልኩት። ቤን ፊቱ ላይ ፈገግታ እየተነበበ እቅፍ አድርጎኝ “ይሖዋ እንደሚወድህ ምንም ጥርጥር የለውም” አለኝ። (ዘዳ. 31:6) ይህን መስማቴ በጣም አበረታታኝ! ከዚያም ሰኔ 15, 1942 ተጠመቅኩ።
ባለኝ ረክቼ የመኖርን ሚስጥር ተማርኩ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት እያሳየ ሲሄድ ብዙዎች ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ጀመሩ። ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ስለነበረኝ ከዚያ በፊት ይኖሩኛል ብዬ እንኳ የማላስባቸውን ዕቃዎች መግዛት ቻልኩ። አንዳንድ ጓደኞቼ የሞተር ብስክሌት ሲገዙ ሌሎቹ ደግሞ ቤታቸውን በአዲስ መልክ ሠሩት። እኔም አዲስ መኪና ገዛሁ። ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት የነበረኝ ፍላጎት ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዳላደርግ እያደር እንቅፋት ይሆንብኝ ጀመር። አካሄዴ ትክክል እንዳልሆነ ይታወቀኝ ነበር። ጥሩነቱ፣ በ1950 በኒው ዮርክ ሲቲ የተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ አካሄዴን እንዳስተካክል ረዳኝ።
በዚያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ተናጋሪዎች በስብከቱ ሥራ የበለጠ እንድንካፈል የሚያበረታቱ ንግግሮችን አቀረቡ። አንደኛው ተናጋሪ “መሠረታዊ በሆኑት ነገሮች በመርካት ሩጫውን ሩጡ”
በማለት አጥብቆ መከረን። በቀጥታ ለእኔ የተናገረ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ከዚህም በተጨማሪ የጊልያድ ተማሪዎች ሲመረቁ ተመለከትሁ፤ ይህም ‘በእኔ ዕድሜ የሚገኙት እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሌላ አገር ሄደው ለማገልገል ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ካደረጉ እኔም እዚሁ ሆኜ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለብኝ’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። የአውራጃ ስብሰባው ሲያበቃ አቅኚ ለመሆን ወስኜ ነበር።በዚህ መሃል ኤቭሊን ሞንዳክ ከተባለች በጉባኤያችን የምትገኝ ቀናተኛ እህት ጋር መጠናናት ጀምሬ ነበር። ስድስት ልጆችን ያሳደገችው የኤቭሊን እናት ደፋር ሴት ነበረች። በአንድ ትልቅ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ቆማ ማገልገል ትወድድ ነበር። እንዲህ ማድረጓ ያናደደው ቄስ ከዚያ አካባቢ ዘወር እንድትል በተደጋጋሚ ጊዜ ቢነግራትም እሷ ግን ከአቋሟ ንቅንቅ አላለችም። ኤቭሊንም እንደ እናቷ የሰው ፍርሃት አልነበራትም።—ምሳሌ 29:25
በ1951 እኔና ኤቭሊን የተጋባን ሲሆን ሥራችንን አቁመን አቅኚነት ጀመርን። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ ከኒው ዮርክ ሲቲ 160 ኪሎ ሜትር ርቃ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ወደ አማጋንሴት መንደር እንድንዛወር አበረታታን። በዚያ የሚገኘው ጉባኤ መኖሪያ ቤት እንዳልተገኘልን ሲነግረን ተጎታች ቤት ለመግዛት ማፈላለግ ጀመርን፤ ሆኖም ያገኘናቸው ሁሉ ከአቅማችን በላይ ነበሩ። በዚህ መሃል አንድ ያረጀ ተጎታች ቤት አገኘን። ባለቤቱ ዋጋው 900 ዶላር መሆኑን ነገረን፤ ለሠርጋችን የተሰጠን ስጦታም ይህን ያህል ነበር። ተጎታች ቤቱን ገዝተን ካደስነው በኋላ ወደ አዲሱ ክልላችን ወሰድነው። ይሁንና የተመደብንበት ቦታ ስንደርስ ቤሳ ቤስቲን ስላልነበረን አቅኚ ሆነን እንዴት እንደምንቀጥል አሳስቦን ነበር።
ኤቭሊን የሰዎችን ቤት ማጽዳት ጀመረች፤ እኔ ደግሞ በአንድ የጣሊያን ምግብ ቤት ውስጥ ምሽት ላይ የጽዳት ሥራ አገኘሁ። ባለቤቱ “የተረፈውን ምግብ ለሚስትህ መውሰድ ትችላለህ” አለኝ። ስለዚህ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ቤት ስደርስ ቤታችን በፒሳ እና በፓስታ ሽታ ይታወድ ነበር። በተለይ በቅዝቃዜው ወራት በረዶ በሚሆነው ተጎታች ቤታችን ውስጥ በብርድ በምንቆራመድበት ወቅት ይህንን ምግብ ሞቅ አድርገን መመገብ በጣም ያስደስተን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የጉባኤያችን ወንድሞች ደጃፋችን ላይ ትልቅ ዓሣ ያስቀምጡልን ነበር። በአማጋንሴት ከሚገኙት ውድ ወንድሞቻችን ጋር ባሳለፍናቸው ዓመታት መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች መርካት ሕይወትን አስደሳች እንደሚያደርግ ተምረናል። በዚያ መንደር ያገለገልንባቸው ዓመታት በጣም አስደሳች ነበሩ።
ራሳችንን ይበልጥ ለማቅረብ ተነሳሳን
በሐምሌ ወር 1953 በኒው ዮርክ ሲቲ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከተመደቡባቸው አገሮች ከመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚስዮናውያን ጋር ተገናኘን። እነዚህ ሚስዮናውያን የሚያስደንቁ ተሞክሮዎችን ነገሩን። ደስታቸው በቀላሉ የሚጋባ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባው ላይ አንድ ተናጋሪ የመንግሥቱ መልእክት ገና ያልተዳረሰባቸው ብዙ አገሮች እንዳሉ ጎላ አድርጎ ሲናገር አገልግሎታችንን በማስፋት ራሳችንን ይበልጥ ማቅረብ እንደሚገባን ተሰማን። በዚህ ስብሰባ ላይ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ለመካፈል አመለከትን። በዚያው ዓመት በጊልያድ ትምህርት ቤት በ23ኛው ክፍል ገብተን እንድንሠለጥን ተጋበዝን፤ ትምህርት ቤቱ የጀመረው የካቲት 1954 ነበር። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
በብራዚል እንድናገለግል እንደተመደብን ስናውቅ በጣም ተደሰትን። በእንፋሎት በሚሠራ መርከብ የምናደርገውን የ14 ቀን ጉዞ ከመጀመራችን በፊት በቤቴል የሚያገለግል አንድ ኃላፊነት ያለው ወንድም እንዲህ አለኝ፦ “ከአንተና ከባለቤትህ ጋር ነጠላ የሆኑ ዘጠኝ ሚስዮናውያን እህቶች ወደ ብራዚል ይሄዳሉ። እነዚህን እህቶች ተንከባከባቸው!” አሥር ወጣት ሴቶችን አስከትዬ መርከቡ ላይ ስሳፈር የመርከቡ ሠራተኞች እንዴት በአግራሞት እንደተመለከቱኝ መገመት ትችላላችሁ! እህቶች ግን ምንም አልተቸገሩም ነበር። እንደዚያም ሆኖ እፎይ ያልኩት የብራዚልን መሬት ስንረግጥ ነበር።
የፖርቹጋል ቋንቋ ከተማርን በኋላ በደቡብ ብራዚል ግዛት በምትገኘው በሪዮ ግራንደ ዶ ሱል የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ነጠላ የነበረው እኔ የተካሁት የወረዳ የበላይ ተመልካች እኔና ባለቤቴን እንዲህ አለን፦ “ወደዚህ ቦታ ባልና ሚስት መላካቸው አስገርሞኛል። ይህ አካባቢ ወጣ ገባ በመሆኑ በጣም አስቸጋሪ ነው።” ጉባኤዎቹ ሰፊ በሆነ ገጠራማ አካባቢ ተራርቀው የሚገኙ ሲሆን ወደ አንዳንዶቹ ጉባኤዎች መድረስ የሚቻለው በጭነት መኪና ብቻ ነበር። ለሹፌሩ ምግብ ከጋበዝነው በጭነት መኪናው ላይ እንድንሳፈር ይፈቅድልን ነበር። በፈረስ ላይ እንደሚፈናጠጥ ሰው በጭነቱ አናት ላይ እግራችን አንፈራጠን ከተቀመጥን በኋላ ጭነቱ የታሰረበትን ገመድ በሁለት እጃችን አጥብቀን እንይዝ ነበር። የጭነት መኪናው ኃይለኛ ኩርባ ላይ ሲታጠፍ ከላይ የተቆለለው ጭነት ወደ አንድ ጎን ያዘነብል ስለነበር ቁልቁል በሚታየን ገደል ውስጥ እንዳንወድቅ ገመዱን ሙጭጭ አድርገን እንይዝ ነበር። ሆኖም የእኛን መምጣት በጉጉት በሚጠባበቁት ወንድሞች ፊት ላይ የሚነበበውን ደስታ ስንመለከት እንዲህ ዓይነት ረጅም ጉዞ ማድረጋችን የሚክስ እንደሆነ ይሰማናል።
የምናርፈው በወንድሞች ቤት ውስጥ ነበር። እነዚህ ወንድሞች በጣም ድሆች ቢሆኑም ይህ ለጋስ ከመሆን አላገዳቸውም። በአንድ ገለልተኛ ክልል ውስጥ የሚኖሩት ወንድሞች በሙሉ የሚሠሩት ሥጋ በሚያሽግ ድርጅት ውስጥ ነበር። የሚከፈላቸው ደሞዝ በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚበሉት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። አንድ ቀን ሳይሠሩ ከቀሩ አይከፈላቸውም። እንደዚያም ሆኖ በምንጎበኛቸው ወቅት የጉባኤውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የሁለት ቀን ፈቃድ ወሰዱ። እነዚህ ወንድሞች በይሖዋ ላይ ይታመኑ ነበር። ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆነው እነዚህ ወንድሞች ለአምላክ መንግሥት ሲሉ መሥዋዕት በመክፈል ረገድ ፈጽሞ የማንረሳው ትምህርት አስተምረውናል። ከእነርሱ ጋር ስንኖር በየትኛውም ትምህርት ቤት ልናገኘው የማንችለውን ትምህርት ቀስመናል። ወደኋላ መለስ ብዬ እነዚህን ወንድሞች ሳስባቸው ዓይኖቼ በደስታ እንባ ይሞላሉ።
በ1976 እናቴን ለማስታመም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። ብራዚልን ለቆ መሄድ ከባድ ቢሆንብንም በዚያ አገር የአስፋፊዎችና የጉባኤዎች ቁጥር አስገራሚ እድገት ሲያደርግ መመልከት በመቻላችን አመስጋኞች ነን። ከብራዚል ደብዳቤዎች ሲደርሱን በዚያ ያሳለፍናቸውን አስደሳች ጊዜያት በትዝታ መለስ ብለን እንድናስብ ያደርጉናል።
ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን ጋር እንደገና መገናኘት
እናቴን እየተንከባከብን እያለ የጽዳት ሥራ እየሠራን በአቅኚነት እናገለግል ነበር። እናቴ፣ ለይሖዋ ታማኝነቷን እንደጠበቀች በ1980 አረፈች። ከዚያ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በ1990 እኔና ባለቤቴ በከነቲከት የሚገኝ አንድ ጉባኤ ስንጎበኝ በሕይወታችን ውስጥ ልዩ ስፍራ የምንሰጠውን አንድ ሰው አገኘን። በዚያ ጉባኤ ውስጥ ካሉት ሽማግሌዎች አንዱ ቤን ነበር፤ ቤን ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት ከይሖዋ ጎን እንድቆም የረዳኝ ወንድም ነው። በዚህ ጊዜ ምን እንደተሰማን መገመት ትችላላችሁ፤ ከቤን ጋር በደስታ ተቃቀፍን።
ከ1996 አንስቶ እኔና ኤቭሊን በኤሊዛቤት፣ ኒው ጀርሲ በሚገኝ በፖርቹጋል ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነን አቅማችን የፈቀደውን ያህል እናገለግላለን። የጤንነት ችግር ቢኖርብኝም ውዷ ባለቤቴ እየረዳችኝ በአገልግሎት የቻልኩትን ያህል እካፈላለሁ። ኤቭሊን አቅመ ደካማ የሆኑ አንዲት አረጋዊት ጎረቤታችንንም ትረዳለች። እኚህ ጎረቤታችን ማን እንደሆኑ መገመት ትችላላችሁ? በርታ ይባላሉ፤ ከ70 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት እናቴን የይሖዋ አገልጋይ እንድትሆን የረዷት እህት ናቸው! እህት በርታ ቤተሰባችን እውነትን እንዲያውቅ ላደረጉልን እርዳታ ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ይህን አጋጣሚ በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።
ቀደም ባሉት ዓመታት የተካፈልኳቸው እነዚያ የአውራጃ ስብሰባዎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን እንድቆም፣ ሕይወቴን ቀላል እንዳደርግ እንዲሁም አገልግሎቴን እንዳሰፋ ስላነሳሱኝ አመስጋኝ ነኝ። አዎን፣ እነዚያ የአውራጃ ስብሰባዎች የሕይወቴን አቅጣጫ ለውጠውታል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤቭሊን እናት (በስተ ግራ) እና የእኔ እናት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወዳጄ ቤን
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በብራዚል እያለን
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ከኤቭሊን ጋር