የአምላክን ቃል በመጠቀም ራስህንም ሆነ ሌሎችን እርዳ
“መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ።”
1. በአምላክ ቃል ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
ሽማግሌዎች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በመስክ አገልግሎት ላይ ለመካፈል ብቁ መሆን አለመሆኑን በሚገመግሙበት ጊዜ ‘ከሰውየው አንደበት የሚወጣው ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል አድርጎ እንደሚያምንበት ያሳያል?’ ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። * የመንግሥቱ አስፋፊ ለመሆን የሚፈልግ አንድ ሰው አልፎ ተርፎም ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በአምላክ ቃል እንደሚያምኑ ማሳየት አለባቸው። ለምን? በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነትና ቃሉን በአገልግሎት ላይ በሚገባ መጠቀም መቻላችን ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲድኑ ለመርዳት ያስችለናል።
2. ‘በተማርናቸው ነገሮች ጸንተን መቀጠል’ ያለብን ለምንድን ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ “በተማርካቸውና ሰዎች አሳምነውህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ቀጥል” ብሎ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ጊዜ የአምላክ ቃል በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። እዚህ ላይ ጳውሎስ “ነገሮች” ብሎ የጠቀሳቸው፣ ጢሞቴዎስ በምሥራቹ ላይ እምነት እንዲያሳድር ያነሳሱት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ናቸው። እነዚህ እውነቶች በዛሬው ጊዜ እኛም ተመሳሳይ እምነት እንዲያድርብን ያደረጉን ሲሆን “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲኖረን ይረዱናል። (2 ጢሞ. 3:14, 15) ጳውሎስ ቀጥሎ የተናገራቸውን ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው ለሌሎች ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንጠቅሳቸዋለን፤ ሆኖም እኛ ራሳችን በ2 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ ከሚገኙት ከእነዚህ ቃላት ተጨማሪ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ጥቅሱን አንብብ።) እስቲ ይህን ጥቅስ ጠለቅ ብለን እንመርምር። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ የሚያስተምረን ትምህርቶች በሙሉ ትክክል እንደሆኑ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—መዝ. 119:128
“ለማስተማር . . . ይጠቅማል”
3-5. (ሀ) በጴንጤቆስጤ ዕለት የተሰበሰቡት ሰዎች ጴጥሮስ ላቀረበው ንግግር ምን ምላሽ ሰጡ? ለምንስ? (ለ) በተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች እውነትን የተቀበሉት ለምንድን ነው? (ሐ) በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ የሚያስደንቃቸው ነገር ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ የእስራኤልን ብሔር “ነቢያትን፣ ጥበበኞችንና የሕዝብ አስተማሪዎችን ወደ እናንተ እልካለሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 23:34) ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ ደቀ መዛሙርቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ሲያገለግሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጠቀሙ አስተምሯቸዋል። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ከእነዚህ “የሕዝብ አስተማሪዎች” አንዱ የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩ በርካታ ሰዎች ንግግር ያቀረበ ሲሆን በንግግሩ ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በርከት ያሉ ጥቅሶችን ተጠቅሟል። ብዙ አድማጮች ጴጥሮስ እነዚህን ጥቅሶች ሲያብራራ ሲሰሙ “ልባቸው እጅግ [ተነካ]።” በመሆኑም ከኃጢአታቸው ንስሐ ገቡ። ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች አምላክ ይቅር እንዲላቸው በመለመን ክርስቲያኖች ሆነዋል።—ሥራ 2:37-41
4 ሌላው የሕዝብ አስተማሪ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን ከኢየሩሳሌም ርቆ በሚገኝ አካባቢ ሰብኳል። ለምሳሌ መቄዶንያ ውስጥ በምትገኘው የተሰሎንቄ ከተማ በምኩራብ ውስጥ አምልኮ ያቀርቡ ለነበሩ ሰዎች ሰብኳል። ጳውሎስ ‘ለሦስት ሰንበት ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ የግድ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ ያብራራና ያስረዳ ነበር።’ ውጤቱ ምን ሆነ? ከአይሁዳውያን መካከል “አንዳንዶቹ አማኞች” ሆኑ፤ ‘ከግሪካውያንም መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁ አደረጉ።’—ሥራ 17:1-4
5 በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቀሙበት መንገድ ብዙዎችን ያስደንቃቸዋል። በስዊዘርላንድ አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ለአንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አነበበችለት፤ በዚህ ጊዜ ግለሰቡ “ለመሆኑ እነማን ናችሁ?” በማለት ጠየቃት። እሷም “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን” አለችው። ሰውየውም “ማወቅ ነበረብኝ። ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ቤቴ መጥቶ ማን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያነብልኝ ይችላል?” አላት።
6, 7. (ሀ) በጉባኤ የሚያስተምሩ ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 በምናስተምርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በተሟላ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ጉባኤውን ከመድረክ ሆነህ የማስተማር መብት ካለህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ተጠቀም። ቁልፍ ጥቅሶችን በራስህ አባባል ከመናገር ወይም በወረቀት ላይ አትመህ አሊያም በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ተጠቅመህ ከማንበብ ይልቅ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን አውጥተህ አንብብ፤ እንዲሁም አድማጮች እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታታ። በተጨማሪም አድማጮች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ በሚረዳ መንገድ ጥቅሶቹን አብራራ። እንዲሁ ዘና የሚያደርጉ የተወሳሰቡ ምሳሌዎችንና ተሞክሮዎችን ከመጠቀም ይልቅ የተመደበልህን ጊዜ የአምላክን ቃል በሚገባ ለማብራራት ተጠቀምበት።
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስናስጠና በአእምሯችን መያዝ ያለብን ነገር ምንድን ነው? ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን ስንጠቀም የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቸል ብለን እንዳናልፍ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ጥቅሶችን እንዲያነብ ማበረታታትና ትርጉማቸው እንዲገባው መርዳት ይኖርብናል። እንዴት? ይህን ማድረግ የሚቻለው ጥናቱ ንግግር የሚቀርብበት ፕሮግራም እስኪመስል ድረስ ረጅም ማብራሪያ በመስጠት ሳይሆን ተማሪው ስሜቱን እንዲገልጽ በማበረታታት ነው። ምን ማመን እንዳለበት ወይም ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ከመንገር ይልቅ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ በሚገባ የታሰበባቸው ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን። *
“ለመገሠጽ . . . ይጠቅማል”
8. ጳውሎስ በውስጡ ምን ዓይነት ትግል ማድረግ አስፈልጎት ነበር?
8 ብዙውን ጊዜ “መገሠጽ” ወይም መውቀስ የክርስቲያን ሽማግሌዎች ሥራ እንደሆነ አድርገን እናስባለን። በእርግጥም የበላይ ተመልካቾች “ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች” የመውቀስ ኃላፊነት አለባቸው። (1 ጢሞ. 5:20፤ ቲቶ 1:13) ይሁንና ራሳችንንም መውቀሳችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊና የነበረው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን ነው። (2 ጢሞ. 1:3) ያም ሆኖ ‘በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና ለኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ’ ሲል ጽፏል። የዚህን ጥቅስ ዐውድ በማጥናት ጳውሎስ የኃጢአት ዝንባሌውን ለመቆጣጠር ምን ዓይነት ትግል ማድረግ እንዳስፈለገው በተሻለ መንገድ መረዳት እንችላለን።—ሮም 7:21-25ን አንብብ።
9, 10. (ሀ) ጳውሎስ ከየትኞቹ ድክመቶች ጋር መታገል አስፈልጎት ሊሆን ይችላል? (ለ) ጳውሎስ የነበረበትን ድክመት የታገለው እንዴት ሊሆን ይችላል?
9 ጳውሎስ የትኞቹን ድክመቶች ለማሸነፍ ጥረት አድርጓል? ድክመቶቹን ለይቶ ባይጠቅስም እንኳ “እብሪተኛ” እንደነበር ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል። (1 ጢሞ. 1:13) ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽሟል። ለክርስቶስ ተከታዮች የነበረውን ስሜት ሲገልጽ “በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጥቼ [ነበር]” ብሏል። (ሥራ 26:11) ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ የቁጣ ስሜቱን መቆጣጠር ችሏል፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስሜቱንና የሚናገረውን ቃል ለመቆጣጠር ትግል ማድረግ ይጠይቅበት ነበር። (ሥራ 15:36-39) በዚህ ረገድ እንዲሳካለት የረዳው ነገር ምንድን ነው?
10 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ ራሱን ለመውቀስ ምን ያደርግ እንደነበር ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 9:26, 27ን አንብብ።) ፍጽምና የጎደለውን ሰብዓዊ ዝንባሌውን ለመቆጣጠር በራሱ ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስድ ነበር። ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቃሚ ምክሮችን በመፈለግ እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ለማዋል ይሖዋ እንዲረዳው ይለምን እንዲሁም ለመሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርግ እንደነበር መገመት ይቻላል። * እኛም ፍጽምና ከጎደለው ዝንባሌያችን ጋር ተመሳሳይ ትግል ማድረግ ስላለብን እሱ ከተወው ምሳሌ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።
11. በእውነት መንገድ እየተመላለስን መሆናችንን ለማወቅ ‘ዘወትር ራሳችንን መፈተን’ የምንችለው እንዴት ነው?
11 ከአምልኳችን ጋር በተያያዘ ፈጽሞ መዘናጋት የለብንም። ከዚህ ይልቅ በእውነት መንገድ እየተመላለስን መሆኑን ለማወቅ ራሳችንን ‘ዘወትር መፈተን’ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 13:5) እንደ ቆላስይስ 3:5-10 ያሉ ጥቅሶችን ስናነብ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘የኃጢአት ዝንባሌዎቼን ለመግደል የተቻለኝን ጥረት እያደረግኩ ነው ወይስ የሥነ ምግባር አቋሜ እየላላ ነው? ኢንተርኔት ስጠቀም የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይበት ድረ ገጽ ቢያጋጥመኝ ድረ ገጹን ወዲያው እዘጋለሁ ወይስ ተገቢ ያልሆኑ ድረ ገጾችን እፈላልጋለሁ?’ በአምላክ ቃል ላይ የሚገኘውን ምክር በዚህ መንገድ በግለሰብ ደረጃ በሥራ ላይ ማዋላችን ‘ነቅተን እንድንኖርና የማመዛዘን ችሎታችንን እንድንጠብቅ’ ይረዳናል።—1 ተሰ. 5:6-8
“ነገሮችን ለማቅናት . . . ይጠቅማል”
12, 13. (ሀ) “ነገሮችን ለማቅናት” በምንሞክርበት ጊዜ ግባችን ምን መሆን አለበት? በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ “ነገሮችን ለማቅናት” ስንሞክር ምን ዓይነት አነጋገር መጠቀም የለብንም?
12 “ነገሮችን ለማቅናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማሻሻል፣ ማስተካከል፣ ተገቢና ትክክለኛ ወደሆነ ሁኔታ መመለስ” የሚል ትርጉም አለው። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች የተናገርነውን ወይም ያደረግነውን ነገር በትክክል ሳይረዱ ሲቀሩ ነገሮችን ለማቅናት እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስ ‘ለቀረጥ ሰብሳቢዎችና ለኃጢአተኞች’ ደግነት ያሳያል በማለት አጉረምርመው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ በማለት መልስ ሰጣቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ።” (ማቴ. 9:11-13) ኢየሱስ ለሁሉም ሰው በትዕግሥትና በደግነት የአምላክን ቃል ያብራራ ነበር። በመሆኑም ትሑት ሰዎች ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” መሆኑን ማወቅ ችለዋል። (ዘፀ. 34:6) ከዚህም የተነሳ የአምላክ ልጅ “ነገሮችን ለማቅናት” ያደረገውን ጥረት የተመለከቱ ብዙ ሰዎች በምሥራቹ አመኑ።
13 ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። አንድ በጣም የተናደደ ሰው ‘ከአንተ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማስተካከል እፈልጋለሁ’ ብሎ በቁጣ ስሜት ይናገር ይሆናል። ይሁንና በ2 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ ያለው ሐሳብ እንዲህ እንድናደርግ አያበረታታንም። “ቅዱስ መጽሐፉ” ሌሎች ሰዎችን በኃይለ ቃል የመናገር መብት አይሰጠንም። ብዙውን ጊዜ የሰላ ትችት ልክ ‘እንደሚዋጋ ሰይፍ’ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትላል፤ ደግሞም እምብዛም ጥቅም አያስገኝም።—ምሳሌ 12:18
14-16. (ሀ) ሽማግሌዎች፣ ሌሎች ሰዎች ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲችሉ በሚረዳ መንገድ ‘ነገሮችን ማቅናት’ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ልጆችን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ‘ነገሮችን ማቅናት’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ታዲያ “ነገሮችን ለማቅናት” ትዕግሥትና ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ባልና ሚስት በየጊዜው የሚጨቃጨቁበትን ጉዳይ አስመልክተው እርዳታ ለማግኘት አንድን የጉባኤ ሽማግሌ አነጋገሩ እንበል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው ምን ያደርጋል? ለአንዳቸውም ሳይወግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመርኩዞ ባልና ሚስቱን ሊያነጋግራቸው ይችላል፤ ምናልባትም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ላይ ያለውን ሐሳብ ሊጠቀም ይችላል። ሽማግሌው በሚያወያያቸው ጊዜ ባልና ሚስቱ እያንዳንዳቸው ይበልጥ ሊሠሩበት የሚገባው ምክር የትኛው እንደሆነ ያስተውሉ ይሆናል። የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሽማግሌው በቤተሰባቸው ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ያህል እንደተሻሻለ በመጠየቅ አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ እርዳታ ሊያደርግላቸው ይችላል።
15 ወላጆች የልጆቻቸው መንፈሳዊነት እንዲጠናከር በሚረዳ መንገድ ‘ነገሮችን ማቅናት’ የሚችሉት እንዴት ነው? በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ልጃችሁ የመሠረተችውን አጠያያቂ ጓደኝነት እንድትተው መርዳት ፈለጋችሁ እንበል። በመጀመሪያ ሁኔታውን በትክክል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል። ከዚያም ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ከተረዳችሁ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱ ነጥቦችን በመጠቀም ልጃችሁን ልታናግሯት ትችላላችሁ። በቀጣዮቹ ቀናት ከእሷ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፋችሁ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በመስክ አገልግሎት ስትካፈል ወይም በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆናችሁ ስትዝናኑ አመለካከቷን ማጤን ትችላላችሁ። ትዕግሥትና ደግነት ካሳያችኋት ልጃችሁ እንደምትወዷትና ትኩረት እንደምትሰጧት ትገነዘባለች። ደግሞም የሰጣችኋትን ምክር ሥራ ላይ ልታውልና አደገኛ ጎዳና ከመከተል ልትርቅ ትችላለች።
16 በተመሳሳይም ጤንነታቸው የሚያሳስባቸውን፣ ከሥራ በመፈናቀላቸው ተስፋ የቆረጡትን አሊያም አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መረዳት የከበዳቸውን ግለሰቦች በትዕግሥትና በደግነት ማበረታታት እንችላለን። የአምላክን ቃል ተጠቅሞ ‘ነገሮችን ማቅናት’ ለይሖዋ ሕዝቦች በርካታ ጥቅም ያስገኛል።
“በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል”
17. የሚሰጠንን ተግሣጽ በአመስጋኝነት መንፈስ መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?
17 “ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም፤ በኋላ ግን በእሱ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች ሰላማዊ ፍሬ ይኸውም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብ. 12:11) በአሁኑ ጊዜ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች አማኝ የሆኑ ወላጆቻቸው የሰጧቸው ምክር ወይም ተግሣጽ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። በተጨማሪም ይሖዋ በክርስቲያን ሽማግሌዎች አማካኝነት የሚሰጠንን ተግሣጽ መቀበላችን ከሕይወት ጎዳና እንዳንወጣ ይረዳናል።—ምሳሌ 4:13
18, 19. (ሀ) በምሳሌ 18:13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ “በጽድቅ ለመምከር” በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች፣ ኃጢአት ከሠሩ ሰዎች ጋር በገርነትና በፍቅር መንፈስ መወያየታቸው ብዙውን ጊዜ ምን ውጤት ያስገኛል?
18 ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ተግሣጽ መስጠት ችሎታ ይጠይቃል። ይሖዋ ክርስቲያኖች ተግሣጽ መስጠት ያለባቸው “በጽድቅ” እንደሆነ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:16) ስለሆነም ተግሣጽ ስንሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጠቀም ይኖርብናል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱ በምሳሌ 18:13 ላይ ይገኛል፤ ጥቅሱ “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ይላል። በመሆኑም ሽማግሌዎች አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ሠርቷል ተብሎ ክስ ሲቀርብላቸው የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጉዳዩን በሚገባ መመርመር ይኖርባቸዋል። (ዘዳ. 13:14) “በጽድቅ” መምከር የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው።
19 ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሌሎችን “በገርነት” እንዲያርሙ ይመክራል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24-26ን አንብብ።) እውነት ነው፣ አንድ ሰው ይሖዋን ሊያስነቅፍም ሆነ ንጹሐን በሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ያም ሆኖ እንዲህ ያለውን ግለሰብ በቁጣ የሚመክር አንድ ሽማግሌ ግለሰቡን ሊረዳው አይችልም። ይሁንና ሽማግሌዎች ‘የአምላክን ደግነት’ በመምሰል ስህተት የፈጸመው ግለሰብ ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሱት ይችላሉ።—ሮም 2:4
20. ወላጆች ልጆቻቸውን በሚገሥጹበት ጊዜ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል አለባቸው?
20 ወላጆች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” ሲያሳድጉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው። (ኤፌ. 6:4) አንድ አባት ስለ ልጁ ጠባይ ከአንድ ወገን በሰማው ወሬ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ልጁን ከመቅጣት መቆጠብ አለበት። ደግሞም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም። “ይሖዋ ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” በመሆኑ ልጆችን የመገሠጽ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች የይሖዋን ፍቅራዊ ባሕርያት ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው።—ያዕ. 5:11
ይሖዋ የሰጠን ወደር የሌለው ስጦታ
21, 22. ለይሖዋ ቃል ያለህን ስሜት በተሻለ ሁኔታ የሚገልጸው በመዝሙር 119:97-104 ላይ የሚገኘው የትኛው ሐሳብ ነው?
21 በአንድ ወቅት አንድ የአምላክ አገልጋይ የይሖዋን ሕግ የሚወደው ለምን እንደሆነ ተናግሮ ነበር። (መዝሙር 119:97-104ን አንብብ።) ቃሉን በማጥናት ጥበብ፣ ማስተዋልና ጥልቅ ግንዛቤ አግኝቷል። ምክሩን ተግባራዊ ማድረጉ በሌሎች ላይ መከራ ካስከተለ የሐሰት መንገድ እንዲርቅ ረድቶታል። ይህ ሰው ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ይደሰትና እርካታ ያገኝ ነበር። የአምላክ መመሪያዎች በሕይወቱ ውስጥ በርካታ ጥቅሞች ስላስገኙለት ይሖዋን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል።
22 ‘ቅዱስ መጽሐፉን ሁሉ’ ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ቃሉ አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም ጠንካራ እምነት እንዲያድርብህ ያደርግሃል። በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኘው ምክር ኃጢአት መሥራት ከሚያስከትላቸው ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ነገሮች ይጠብቅሃል። ቃሉን በሚገባ በመጠቀም ሌሎች በሕይወት መንገድ እንዲጓዙና ከጎዳናው እንዳይወጡ መርዳት ትችላለህ። እንግዲያው ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ስናገለግል ‘ቅዱስ መጽሐፉን’ በተሟላ ሁኔታ እንጠቀምበት።
^ စာပိုဒ်၊ 1 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 79ን ተመልከት።
^ စာပိုဒ်၊ 7 ኢየሱስ ሲያስተምር ብዙውን ጊዜ “እስቲ ምን ትላላችሁ?” ብሎ ይጠይቅ ነበር። ከዚያም የሚሰጡትን መልስ ያዳምጣል።—ማቴ. 18:12፤ 21:28፤ 22:42
^ စာပိုဒ်၊ 10 ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች የኃጢአት ዝንባሌዎችን እንድንዋጋ የሚያበረታቱ በርካታ ሐሳቦችን ይዘዋል። (ሮም 6:12፤ ገላ. 5:16-18) ለሌሎች የሰጠውን ምክር እሱ ራሱ በሥራ ላይ አውሎ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።—ሮም 2:21