ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ግጭቶችን መፍታት
እሱ የሚለው:- “እኔና ሣራ * ከተጋባን በኋላ ከቤተሰቦቼ ጋር በወላጆቼ ቤት እንኖር ነበር። አንድ ቀን የወንድሜ የሴት ጓደኛ በመኪናችን ቤቷ እንዳደርሳት ጠየቀችኝ። እኔም ልረዳት ስለፈለግሁ ትንሹን ልጄን ይዤ ላደርሳት ሄድኩ። ወደ ቤት ስመለስ ግን ሣራ በጣም ተናዳ ነበር። በዚህ የተነሳ መጨቃጨቅ የጀመርን ሲሆን በቤተሰቤ ፊት ሴት አውል ብላ ሰደበችኝ። እኔም በጣም ስለተናደድኩ ይባስ የሚያበሳጯትን ነገሮች መናገር ጀመርኩ።”
እሷ የምትለው:- “ልጃችን ከበድ ያለ የጤና እክል አለበት፤ እንዲሁም በዚያን ወቅት የገንዘብ ችግር ነበረብን። በመሆኑም ፈርናንዶ መኪናውን አስነስቶ ከወንድሙ የሴት ጓደኛና ከልጃችን ጋር ሲሄድ እንድበሳጭ ያደረጉኝ ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። ወደ ቤት ሲመለስ የተሰማኝን ሁሉ አወጣሁት። በዚህ ጊዜ በመካከላችን ከፍተኛ ጭቅጭቅ የተነሳ ከመሆኑም በላይ ተሰዳደብን። በኋላ ግን በተፈጠረው ሁኔታ በጣም አዘንኩ።”
አንድ ባልና ሚስት መጨቃጨቃቸው እንደማይዋደዱ ያሳያል? በፍጹም! ከላይ የተጠቀሱት ፈርናንዶና ሣራ በጣም ይዋደዳሉ። ይሁን እንጂ በጣም ጥሩ በሚባሉት ትዳሮች ውስጥም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ግጭት ሊነሳ ይችላል።
በባልና ሚስት መካከል ግጭት የሚፈጠረው ለምንድን ነው? እነዚህ ግጭቶች ትዳራችሁን እንዳያናጉት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ጋብቻ የአምላክ ዝግጅት በመሆኑ የእሱ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል መመርመሩ ተገቢ ነው።—ዘፍጥረት 2:21, 22፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ችግሮቹን መረዳት
አብዛኞቹ ባልና ሚስት ለትዳር ጓደኛቸው ፍቅርና ደግነት ማሳየት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት እውነታውን አስቀምጦታል። (ሮሜ 3:23) በመሆኑም አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ስሜትን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ግጭት ሲፈጠር አንዳንዶች እንደ መጮኽና መሳደብ ያሉትን መጥፎ ልማዶች መቆጣጠር ያስቸግራቸው ይሆናል። (ሮሜ 7:21፤ ኤፌሶን 4:31) በባልና ሚስት መካከል ውጥረት እንዲሰፍን የሚያደርጉ ምን ሌሎች ነገሮች አሉ?
ባልና ሚስት ብዙውን ጊዜ ስሜታቸውን የሚገልጹት በተለያየ መንገድ ነው። ሜቺኮ እንዲህ ትላለች:- “እንደተጋባን ሰሞን እኔና ባለቤቴ ነገሮችን የምንገልጽበት መንገድ በጣም የተለያየ እንደሆነ አስተዋልኩ። እኔ ምን እንደተከናወነ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ለምን እና እንዴት እንደተከናወነም ጭምር ማውራት እፈልጋለሁ። ባለቤቴ ግን ትኩረት የሚሰጠው ለተከናወነው ነገር ብቻ ነው።”
ሜቺኮ ያጋጠማት ሁኔታ በሌሎች ትዳሮችም የተለመደ ነው። በብዙ ትዳሮች ውስጥ አንደኛው የትዳር ጓደኛ በመካከላቸው ስለተፈጠረው አለመግባባት በሰፊው መወያየት የሚፈልግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ውዝግብ ስለሚጠላ ስለ ጉዳዩ ባያወራ ይመርጣል። አንዳንድ ጊዜ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ብዙ በተናገረ መጠን ሌላኛው ጉዳዩን ገሸሽ ለማድረግ የበለጠ ይጥራል። በእናንተ ትዳር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ብቅ እያለ እንደሆነ ይሰማችኋል? አንዳችሁ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ ስትፈልጉ ሌላው ወገን ውይይቱን በአጭሩ ይቀጨዋል?
ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ሌላው ነጥብ ደግሞ የአንድ ሰው አስተዳደግ፣ ባልና ሚስት እንዴት መወያየት
እንዳለባቸው ባለው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል መሆኑ ነው። በትዳር ውስጥ አምስት ዓመታት ያሳለፈው ጀስቲን እንዲህ ይላል:- “የእኔ ቤተሰብ ቁጥብ በመሆናቸው ስሜቴን በግልጽ መናገር ያስቸግረኛል። ይህ ደግሞ ሚስቴን ያበሳጫታል። የእሷ ቤተሰቦች ግን በጣም ግልጽ ስለሆኑ ስሜቷን ለእኔ መግለጽ ምንም አያስቸግራትም።”ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያለባችሁ ለምንድን ነው?
ስለ ጋብቻ ጥናት ያደረጉ ሰዎች፣ አንድ ባልና ሚስት ትዳራቸው አስደሳች እንደሚሆን የሚጠቁመው ከሁሉ የተሻለ ምልክት እርስ በርስ እንደሚዋደዱ አዘውትረው መግለጻቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ። በጾታ ግንኙነት ረገድ መስማማታቸውም ሆነ በቂ ገንዘብ ያላቸው መሆኑም በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አይመደቡም። ከዚህ ይልቅ አንድ ባልና ሚስት የተሳካ ትዳር እንዳላቸው የሚያሳየው አስተማማኝ ምልክት በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩትን ግጭቶች የሚፈቱበት መንገድ ነው።
ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ አንድ ወንድና ሴት ሲጋቡ የሚያጣምራቸው አምላክ እንጂ ሰው እንዳልሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:4-6) በመሆኑም ጥሩ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት አምላክን ያስከብራሉ። በሌላ በኩል ግን አንድ ባል ለሚስቱ ፍቅርና አሳቢነት የማያሳያት ከሆነ ለይሖዋ አምላክ የሚያቀርበው ጸሎት ተሰሚነት አይኖረውም። (1 ጴጥሮስ 3:7) አንዲት ሚስትም ባሏን የማታከብር ከሆነ ባል የቤተሰብ ራስ እንዲሆን የሾመውን ይሖዋን እንደማታከብር ተደርጎ ይቆጠራል።—1 ቆሮንቶስ 11:3
ትዳር የተሳካ እንዲሆን የሚረዱ ቁልፍ ነጥቦች—ሌላውን ወገን የሚጎዳ ነገር የመናገር ልማድን አስወግዱ
ሐሳባችሁን የምትገልጹበት መንገድ ወይም አስተዳደጋችሁ ምንም ይሁን ምን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ አለመግባባቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንድትችሉ ጎጂ የአነጋገር ልማዶችን ማስወገድ አለባችሁ። እስቲ ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ:-
‘ሌላውን ወገን በሚጎዳ መንገድ ምላሽ ላለመስጠት እጥራለሁ?’
አንድ ጥበበኛ የሆነ ሰው የተናገረው ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣል፤ እንዲሁም ቍጣን መጐተት ጠብን ያወጣል።” (ምሳሌ 30:33 የ1954 ትርጉም) ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? የሚከተለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ከቤተሰቡ ባጀት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው የሐሳብ ልዩነት (ለምሳሌ “ወጪያችንን መቀነስ አለብን” የሚለው ሐሳብ) መልኩን ለውጦ አንዳችሁ ሌላውን መንቀፍ (ለምሳሌ “አባካኝ ነህ/ነሽ” በማለት መወቃቀስ) ትጀምሩ ይሆናል። እውነት ነው፣ የትዳር ጓደኛህ አንተን በመንቀፍ ‘አፍንጫህን ብትጨምቀው’ አንተም መልሰህ ‘አፍንጫዋን መጭመቅ’ ትፈልግ ይሆናል። * ይሁን እንጂ አጸፋ መመለስ ሌላውን ወገን ከማስቆጣትና አለመግባባቱ እንዲባባስ ከማድረግ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል:- “ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት።” (ያዕቆብ 3:5, 6) የትዳር ጓደኛሞች አንደበታቸውን መግታት ካቃታቸው ቀላል አለመግባባቶች ተጋግለው ወዲያው የጦፈ ግጭት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ባልና ሚስት ስሜታቸውን መቆጣጠር እየተሳናቸው በተደጋጋሚ በመካከላቸው ጭቅጭቅ የሚፈጠር ከሆነ ፍቅራቸው እያደገ ሊሄድ አይችልም።
አጸፋ ከመመለስ ይልቅ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም” የተባለለትን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ትችላለህ? (1 ጴጥሮስ 2:23) ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ነገሩን ቶሎ ለማብረድ የተሻለው መንገድ የትዳር ጓደኛህ የተናገረችው ነገር ትክክል ሊሆን እንደሚችል አምነህ መቀበልና ግጭቱ እንዲባባስ ላደረግከው ነገር ይቅርታ መጠየቅ ነው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ባለቤቴ ያሳሰባት ነገር ተገቢ እንደሆነ አምኜ ብቀበል ምን ይጎዳኛል? ግጭቱ እንዲባባስ እኔ በበኩሌ ያደረግሁት ነገር አለ? ስህተቴን አምኜ ይቅርታ እንዳልጠይቅ ምን ያግደኛል?’
‘የባለቤቴን አመለካከትና ስሜት በቁም ነገር አልመለከተውም?’
የአምላክ ቃል “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ” የሚል ትእዛዝ ይሰጣል። (1 ጴጥሮስ 3:8) ይህንን ምክር በተግባር እንዳታውል ሊያደርጉህ የሚችሉትን ሁለት ምክንያቶች እንመልከት። አንደኛ፣ የትዳር ጓደኛህን አመለካከት ወይም ስሜት ማስተዋል ያቅትህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛህ አንድ ጉዳይ ከአንተ የበለጠ ካሳሰባት “አንቺ ደግሞ የማያስጨንቀው ነገር ያስጨንቅሻል” ልትላት ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ የምትለው የትዳር ጓደኛህ ጉዳዩን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንድትመለከተው ለመርዳት አስበህ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር እምብዛም አያጽናናም። ሚስቶችም ሆኑ ባሎች የሚወዷቸው ሰዎች ስሜታቸውን እንደሚረዱላቸው ማወቅ ይፈልጋሉ።
ከልክ ያለፈ ኩራትም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ስሜት አቅልሎ እንዲመለከት ሊያደርገው ይችላል። ኩሩ የሆነ ግለሰብ ሁልጊዜ ሌሎችን በማንቋሸሽ ራሱን ከፍ ለማድረግ ይጥራል። እንዲህ የሚያደርገው ሰዎችን የሚያዋርድ ነገር በመናገር ወይም ከሌሎች ጋር በማወዳደር ሊሆን ይችላል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን ፈሪሳውያንና ጸሐፍት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ እንደ እነሱ ፈሪሳዊ የሆነ ባልንጀራቸው እንኳ ከእነዚህ ኩሩ ግለሰቦች የተለየ ሐሳብ ካቀረበ ሰውየውን በሚያዋርድ አነጋገር ይተቹታል። (ዮሐንስ 7:45-52) ኢየሱስ ግን ከእነዚህ ፈሪሳውያን የተለየ ነበር። ሌሎች ችግራቸውን ሲነግሩት ሁኔታቸውን ይረዳላቸው ነበር።—ማቴዎስ 20:29-34፤ ማርቆስ 5:25-34
የትዳር ጓደኛህ፣ የሚያሳስባትን ጉዳይ ስትነግርህ ምን ምላሽ እንደምትሰጣት አስብ። ንግግርህ፣ የድምፅህ ቃና ወይም በፊትህ ላይ የሚነበበው ስሜት ያሳሰባትን ነገር እንደተረዳህላት የሚያሳይ ነው? ወይስ የትዳር ጓደኛህ ስሜት ያን ያህል አሳሳቢ እንዳልሆነ የሚያንጸባርቅ ነገር ለማድረግ ወይም ለመናገር ትፈተናለህ?
እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- በሚቀጥሉት ሳምንታት የትዳር ጓደኛህን እንዴት እንደምታናግራት አስብ። የትዳር ጓደኛህ ስታናግርህ ችላ የምትላት ወይም የሚያቃልል ነገር የምትናገር ከሆነ ወዲያውኑ ይቅርታ ጠይቃት።
‘ብዙውን ጊዜ የትዳር ጓደኛዬ ስለ ራሷ ጥቅም ብቻ እንደምታስብ ይሰማኛል?’
“ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን? በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን?” (ኢዮብ 1:9, 10) ሰይጣን ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት ታማኝ የነበረው ኢዮብ አምላክን የሚያገለግልበትን ምክንያት አጠያያቂ አድርጎት ነበር።
የትዳር ጓደኛሞችም ካልተጠነቀቁ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊያዳብሩ ይችላሉ። ለአብነት ያህል፣ የትዳር ጓደኛህ ጥሩ ነገር ብታደርግልህ ‘በምላሹ አንድ ነገር ለማግኘት ፈልጋ ነው ወይም አንድ ነገር ለመደበቅ እየሞከረች ነው’ ብለህ ታስባለህ? ባለቤትህ አንድ ስህተት ብትሠራ፣ ይህ ራስ ወዳድ እንደሆነችና እንደማታስብ የሚያረጋግጥ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ከዚህ ቀደም የፈጸመቻቸውን ተመሳሳይ ስህተቶች በማስታወስ የአሁኑን ስህተቷንም በልብህ ትይዘዋለህ?
እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- የትዳር ጓደኛህ ያደረገችልህን መልካም ነገሮችና እንዲህ እንድታደርግ የገፋፋትን ምክንያት በዝርዝር ጻፍ።
ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር . . . በደልን አይቈጥርም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) እውነተኛ ፍቅር እውር አይደለም። ያም ቢሆን ግን በደልን አይቆጥርም። ጳውሎስ፣ ፍቅር “ሁሉን ያምናል” በማለትም ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:7 የ1954 ትርጉም) እንዲህ ዓይነት ፍቅር ያለው ሰው የተነገረውን ሁሉ ያምናል ማለት ባይሆንም በሌላው ሰው ላይ እምነት ለመጣል ግን ዝግጁ ነው፤ ተጠራጣሪም አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው ዓይነት ፍቅር ያለው ሰው ሌሎችን ይቅር ለማለት ዝግጁ ከመሆኑም በላይ የሌሎችን ውስጣዊ ግፊት አይጠራጠርም። (መዝሙር 86:5፤ ኤፌሶን 4:32) የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላቸው እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሲያሳዩ አስደሳች ትዳር ይኖራቸዋል።
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .
-
በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ባልና ሚስት የሠሩት ስህተት ምን ነበር?
-
እኔስ በትዳሬ ውስጥ ተመሳሳይ ስህተት ላለመሥራት ምን ማድረግ አለብኝ?
-
በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሐሳቦች መካከል ይበልጥ መሥራት ያለብኝ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ ነው?