በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ይኑርህ

1 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ይኑርህ

1 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ይኑርህ

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16

እንቅፋት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ጥበብ ውጤት እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንዳንዶች በውስጡ የሚገኙት ታሪካዊ ዘገባዎች ትክክለኛ እንዳልሆኑ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተግባራዊ መሆን የማይችሉ ወይም ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው በማለት ይናገራሉ።

እንቅፋቱን እንዴት ልትወጣው ትችላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኝነት ወይም ጠቀሜታ የሚጠራጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በአብዛኛው ጉዳዩን ራሳቸው መርምረው አይደለም። እነዚህ ሰዎች የሚያስተጋቡት ሌሎች የሚናገሩትን ነገር ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ሁሉን [“ቃልን ሁሉ፣” የ1954 ትርጉም] ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ሲል ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 14:15

ከሌሎች የሰማኸውን ነገር በጭፍን ከመቀበል ይልቅ በቤርያ (በአሁኗ ግሪክ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ አካባቢ) ይኖሩ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖችን ምሳሌ ለምን አትከተልም? እነዚያ ክርስቲያኖች ሌሎች የነገሯቸውን እንዲሁ አልተቀበሉም። ከዚህ ይልቅ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ [የመመርመር]” ልማድ ነበራቸው። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን እርግጠኛ እንድትሆን የሚያደርጉህን ሁለት ምክንያቶች በአጭሩ እንመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ዘገባዎች ትክክለኛ ናቸው። ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የሰዎችና የቦታ ስሞች ትክክለኛ ስለመሆናቸው ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ይሁንና የተለያዩ ማስረጃዎች የእነዚህ ሰዎች ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ እንደሆነና የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በኢሳይያስ 20:1 ላይ የተጠቀሰው የአሦር ንጉሥ ሳርጎን በሕይወት የነበረ ሰው ስለመሆኑ ምሑራን በአንድ ወቅት ጥያቄ አንስተው ነበር። ይሁን እንጂ በ1840ዎቹ ዓመታት የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች የዚህን ንጉሥ ቤተ መንግሥት በቁፋሮ አገኙ። በአሁኑ ጊዜ በሚገባ ከሚታወቁት አሦራውያን ነገሥታት መካከል አንዱ ሳርጎን ነው።

ተቺዎች ኢየሱስ እንዲገደል ያዘዘው ሮማዊ አገረ ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ በሕይወት የነበረ ሰው ስለመሆኑ ጥያቄ አንስተው ነበር። (ማቴዎስ 27:1, 22-24) ይሁንና በ1961 በኢየሩሳሌም በምትገኘው በቂሳርያ ከተማ አቅራቢያ የጲላጦስ ስምና ማዕረግ ያለበት ድንጋይ ተገኘ።

ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት፣ በጥቅምት 25, 1999 እትሙ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ትክክለኝነት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ዘመናዊ የአርኪኦሎጂ ምርምር፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ አባቶች፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ስለ መውጣታቸው፣ ስለ ዳዊት ሥርወ መንግሥትና በኢየሱስ ዘመን ስለነበረው የአኗኗር ዘይቤ ከሚናገሩት ታሪኮች ውስጥ ቁልፍ በሆኑት ነገሮች ላይ ጥናት በማድረግ የብሉይ ኪዳንም ሆነ የአዲስ ኪዳን አንኳር ታሪኮች ትክክለኛ መሆናቸውን በሚያስገርም ሁኔታ አረጋግጧል።” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለን እምነት የተመካው በአርኪኦሎጂ ግኝቶች ላይ ባይሆንም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ ከታሪክ አኳያ ትክክል መሆን አለበት ብለህ መጠበቅህ ተገቢ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይጠቅማሉ። በዓይን የማይታዩ ረቂቅ ሕዋሳት ስለመኖራቸውና እነዚህ ሕዋሳት በሽታ በማስተላላፍ ረገድ ስለሚጫወቱት ሚና በሳይንስ ከመታወቁ ከረጅም ዘመናት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሊሠሩ የሚችሉ ከንጽሕና አጠባበቅ ጋር የተያያዙ ምክሮችን ሰጥቷል። (ዘሌዋውያን 11:32-40፤ ዘዳግም 23:12, 13) የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ሌላውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። (ኤፌሶን 5:28 እስከ 6:4) አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወቱ ተግባራዊ የሚደርግ ከሆነ በሥራ ቦታው ይበልጥ ጠንቃቃ ሠራተኛ ወይም ሠራተኞቹን በአግባቡ የሚይዝ አሠሪ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 4:28፤ 6:5-9) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ ለስሜታዊ ጤንነታችንም ይጠቅማል። (ምሳሌ 14:30፤ ኤፌሶን 4:31, 32፤ ቆላስይስ 3:8-10) ፈጣሪያችን እንዲህ ያለ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር መስጠቱ የሚጠበቅ ነው።

ምን በረከት ያስገኛል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር አላዋቂን ወይም ተሞክሮ የሌለውን እንኳ ጥበበኛ ያደርጋል። (መዝሙር 19:7) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዴ እምነት ካሳደርን ይህ መጽሐፍ ጠንካራ እምነት ለመገንባት የሚያስችለንን ቀጣዩን እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል፤ በዚህ ረገድ ሊረዳን የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * ከተባለው መጽሐፍ ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ—አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው መጽሐፍ” የሚለውን ምዕራፍ 2⁠ን ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።