በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበራቸው

ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበራቸው

ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበራቸው

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን በተቻለ መጠን ብዙዎች እንዲያነቧቸው ለማድረግ ሲሉ በበርካታ ቋንቋዎች ይተረጉሟቸዋል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከብዙ ዘመናት በፊት ቢሆንም መጽሐፉ የተዘጋጀው “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” እንዲሁም መጽናኛና ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ እንዲሰጠን ነው።—ሮም 15:4

በመሆኑም እስከ ዛሬ በጽሑፍ ከሰፈሩት መልእክቶች ሁሉ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሐሳብ የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቋንቋዎች መተርጎሙ ምክንያታዊ ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ከባድ ሕመም፣ መንግሥት የጣለው እገዳ ሌላው ቀርቶ የሞት ማስፈራሪያ እንኳ ሳይበግራቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? ለአምላክ ቃል ፍቅር ስለነበራቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ጥረት ያደረጉ አንዳንድ ሰዎች ያሳለፉት አስገራሚ ታሪክ ከዚህ በታች ቀንጨብ ተደርጎ ቀርቧል።

“እንግሊዛውያን የክርስቶስን ሕግ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መማር የሚችሉት በእንግሊዝኛ ነው”

በ1330 ገደማ ጆን ዊክሊፍ በተወለደበት ወቅት እንግሊዝ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑት በላቲን ቋንቋ ነበር። በሌላ በኩል ግን የሕዝቡ የዕለት ተዕለት መግባቢያ እንግሊዝኛ ነበር። ሕዝቡ እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩትም ሆነ ወደ አምላክ የሚጸልዩት በእንግሊዝኛ ነበር።

የካቶሊክ ቄስ የሆነው ዊክሊፍ የላቲን ቋንቋን አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ያም ሆኖ ዊክሊፍ፣ ላቲን በማኅበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ሰዎች ከሌላው ኅብረተሰብ ለመለየት የሚያገለግል ቋንቋ እንደሆነ ስለተሰማው ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስተማር በላቲን መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ ያስብ ነበር። ዊክሊፍ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሰዎች የአምላክን ሕግ መማር ያለባቸው ለመረዳት በሚቀላቸው ቋንቋ ነው፤ ምክንያቱም የሚማሩት የአምላክን ቃል ነው።” በዚህም ምክንያት ዊክሊፍና ጓደኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጉም ቡድን አቋቋሙ። ሥራውን ለማጠናቀቅ ወደ 20 ዓመት ገደማ ፈጅቶባቸዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግን አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የመዘጋጀቱ ሐሳብ አላስደሰታትም። ዘ ሚስትሪስ ኦቭ ዘ ቫቲካን የተሰኘው መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያኗ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መዘጋጀቱን የተቃወመችበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ምዕመናኑ፣ የጥንቱ ክርስትና በወቅቱ ከነበረው የካቶሊክ እምነት ጋር ሲወዳደር ምን ያህል ቀላል እንደነበረ መገንዘብ ቻሉ። . . . የክርስትና እምነት መሥራች ባስተማረው ትምህርትና የእሱ ወኪል እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሾሙት ግለሰብ [ሊቀ ጳጳሱ] በሚያስተምሩት ትምህርት መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ገሃድ ወጣ።”

በመሆኑም ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ 11ኛ ዊክሊፍን የሚያወግዙ አምስት አዋጆች አወጡ። ይሁንና ተርጓሚው ሥራውን ከማከናወን ወደኋላ አላለም። ዊክሊፍ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቷል፦ “እንግሊዛውያን የክርስቶስን ሕግ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መማር የሚችሉት በእንግሊዝኛ ነው። ሙሴ የአምላክን ሕግ የሰማው በገዛ ቋንቋው ነበር፤ የክርስቶስ ሐዋርያትም እንዲሁ።” ዊክሊፍ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ በ1382 ገደማ የዊክሊፍ የሥራ ባልደረቦች የመጀመሪያውን የተሟላ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አወጡ። ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ከሥራ ባልደረቦቹ አንዱ አንዳንድ እርማቶችን አስገብቶ ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጀ።

በወቅቱ የማተሚያ ማሽን ስላልተፈለሰፈ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ በጥንቃቄ በእጅ መገልበጥ ነበረበት፤ ይህም አሥር ወራት የሚፈጅ አድካሚ ሥራ ነበር! የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግን ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠሩ በጣም አሳስቧት ነበር፤ በመሆኑም አንድ ጳጳስ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ማንኛውም ሰው እንደሚወገዝ አስጠነቀቁ። ዊክሊፍ ከሞተ ከ40 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ በጳጳሳቱ ምክር ቤት ትእዛዝ፣ ቀሳውስቱ አፅሙን ከመቃብር አውጥተው ካቃጠሉት በኋላ አመዱን በስዊፍት ወንዝ ላይ በተኑት። ያም ቢሆን እውነትን ለማግኘት የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የዊክሊፍን መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት ይጥሩ ነበር። ፕሮፌሰር ዊልያም ብላክበርን እንደተናገሩት “የዊክሊፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በበርካታ ቅጂዎች ተዘጋጅቶ በስፋት ከመሰራጨቱም ሌላ ለቀጣዩም ትውልድ መተላለፍ ችሏል።”

ለገበሬው የሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ

ዊክሊፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙን ሲያዘጋጅ የተጠቀመበት እንግሊዝኛ በ200 ዓመታት ውስጥ ጊዜ ያለፈበት ሆነ። በብሪስቶል አቅራቢያ የሚሰብክ አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ብዙዎች ሊረዱት አለመቻላቸው በጣም አሳዝኖት ነበር። በአንድ ወቅት አንድ የተማረ ሰው፣ የሊቀ ጳጳሱን ሕግ ሳያውቁ ከመቅረት የአምላክን ሕግ ሳያውቁ መቅረት እንደሚሻል ሲናገር ዊልያም ቲንደል የተባለው ሰባኪ ሰማ። ቲንደል ይህን ሲሰማ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገበሬው እንኳ ከተማረው ሰው የበለጠ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ገለጸ።

ዊክሊፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙን ያዘጋጀው ከላቲኑ ቩልጌት ሲሆን እያንዳንዱ ቅጂ በእጅ የተገለበጠ ነበር። በ1524 ቲንደል እንግሊዝን ለቅቆ ወደ ጀርመን በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅጂዎች በቀጥታ መተርጎም ጀመረ፤ ከዚያም የትርጉም ሥራው በኮሎኝ በሚገኝ ማተሚያ ቤት እንዲታተም አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ግን ባላንጣዎቹ ቲንደል ያከናወነውን የትርጉም ሥራ ስለደረሱበት የኮሎኝ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን በማሳመን ቲንደል ያዘጋጃቸው ቅጂዎች በሙሉ እንዲወረሱ ትእዛዝ እንዲወጣ አደረጉ።

ቲንደል፣ ዎርምዝ ወደተባለችው የጀርመን ከተማ በመሸሽ ሥራውን ቀጠለ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቲንደል ያዘጋጀው የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የእንግሊዝኛ ትርጉም በድብቅ ወደ እንግሊዝ እንዲገባ ተደረገ። በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ስለተሸጡ ጳጳሳቱ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱሶቹ እንዲቃጠሉ ትእዛዝ አስተላለፉ።

የለንደኑ ጳጳስ፣ ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡን እንዲያቆም ለማድረግ እንዲሁም መናፍቅ ብለው የጠሩት ቲንደል የሚያከናውነውን ሥራ ለማገድ ስለፈለጉ ቲንደልን የሚያወግዝ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ሰር ቶማስ ሞርን አዘዟቸው። ሰር ቶማስ ሞር ይበልጥ ያስቆጣቸው ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉም “ቤተ ክርስቲያን” ከማለት ይልቅ “ጉባኤ” እንዲሁም “ቄስ” ከማለት ይልቅ “ሽማግሌ” ማለቱ ነበር። ቲንደል የተጠቀመባቸው ቃላት፣ የሊቀ ጳጳሱ ሥልጣን እንዲሁም በቀሳውስቱና በምዕመናኑ መካከል ያለው ልዩነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ነበሩ። ቲንደል አጋፔ የሚለውን የግሪክኛ ቃል “ልግስና” ከማለት ይልቅ “ፍቅር” ብሎ በመተርጎሙም ሞር አውግዘውታል። ኢፍ ጎድ ስፔር ማይ ላይፍ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “[እንዲህ ያለው አተረጓጎምም] ለቤተ ክርስቲያኗ አደገኛ ነበር። ምክንያቱም ለልግስና ብዙም ትኩረት እንዳይሰጠው መደረጉ [ቤተ ክርስቲያኗ] ታማኝ የሆኑ ሰዎች ወደ ሰማይ ለመግባት እንደሚረዳቸው በማሰብ የሚሰጧት ከፍተኛ እርዳታ፣ በመንጽሔ ውስጥ ያለ ሰው በዚያ የሚቆይበት ጊዜ እንዲያጥርለት ሲባል የሚከፈለው ገንዘብ እንዲሁም ከኑዛዜ የምታገኘው ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል።”

ቶማስ ሞር “መናፍቃን” እንዲቃጠሉ ማበረታታት ጀመሩ፤ በዚህም ምክንያት ጥቅምት 1536 ቲንደል በስቅላት የተገደለ ሲሆን አስከሬኑም እዚያው እንዳለ እንዲቃጠል ተደረገ። ከጊዜ በኋላ ግን ቶማስ ሞር የንጉሡን ሞገስ ስላጡ በሰይፍ ተቀልተው ተገድለዋል። ይሁንና በ1935 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቶማስ ሞርን ቅዱስ ብላ የሰየመቻቸው ሲሆን በ2000 ደግሞ ሊቀ ጳጳስ ዳግማዊ ጆን ፖል፣ የፖለቲከኞች ቅዱስ ጠባቂ የሚል ክብር ሰጥተዋቸዋል።

ቲንደል ግን እንዲህ ያለ እውቅና አልተሰጠውም። ያም ሆኖ ቲንደል ከመሞቱ በፊት ጓደኛው ማይልዝ ከቨርዴል፣ ቲንደል የተረጎማቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንድ ላይ በማሰባሰብ ከበኩረ ጽሑፉ የተተረጎመ የመጀመሪያው የተሟላ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲወጣ አደረገ! በዚህ መንገድ እያንዳንዱ ገበሬ የአምላክን ቃል የማንበብ አጋጣሚ አገኘ። ከእንግሊዝኛ ውጪ በሌሎች ቋንቋዎች ስለተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችስ ምን ማለት ይቻላል?

“ፈጽሞ የማይቻል ይመስል ነበር”

ሮበርት ሞሪሰን የተባለው የብሪታንያ ዜጋ የሆነ ሚስዮናዊ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በቻይንኛ ለማዘጋጀት ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ የቤተሰቦቹም ሆነ የጓደኞቹ ተቃውሞ ሳይበግረው በ1807 ወደ ቻይና አቀና። የትርጉም ሥራው ቀላል አልነበረም። በወቅቱ የምሥራቅ ሕንድ ኩባንያ ዳይሬክተር የነበሩት ቻርልስ ግራንት “ሊከናወን የታሰበው ሥራ ፈጽሞ የማይቻል ይመስል ነበር” ብለዋል።

ሞሪሰን ቻይና ሲደርስ ቻይናውያን ቋንቋቸውን ለውጪ አገር ዜጋ ሲያስተምሩ ቢገኙ በሞት እንደሚቀጡ የሚገልጽ ሕግ እንዳለ ተገነዘበ። ሞሪሰን የራሱንም ሆነ ቋንቋውን ሊያስተምሩት ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ሕይወት ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከቤት ሳይወጣ ቆየ። አንድ ዘገባ እንደገለጸው ሞሪሰን “ለሁለት ዓመት ያህል ከተማረ በኋላ የማንዳሪንን ቋንቋ እንዲሁም ከአንድ በላይ የሆኑ ቀበሌኛዎችን መናገር ብሎም ማንበብና መጻፍ ችሎ ነበር።” በዚህ መሃል ንጉሠ ነገሥቱ፣ የክርስትና መጻሕፍትን ማተም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን የሚገልጽ አዋጅ አወጡ። ሞሪሰን ይህ ሁሉ ማስፈራሪያ ሳይበግረው ኅዳር 25, 1819 ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በቻይንኛ ተርጉሞ ጨረሰ።

በ1836 በቻይንኛ ቋንቋ የተዘጋጁ 2,000 የሚያህሉ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንዲሁም 10,000 የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችና 31,000 የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ታትመው ነበር። ሞሪሰን ለአምላክ ቃል የነበረው ፍቅር “ፈጽሞ የማይቻል ይመስል” የነበረውን ሥራ ለማከናወን አስችሎታል።

በትራስ ውስጥ የተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ

አዶናይራም ጀድሰን እና አን የተባሉ አሜሪካዊ ሚስዮናውያን፣ የካቲት 1812 ከተጋቡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ረጅም ጉዞ ለማድረግ ተነሱ፤ ከዚያም በ1813 በበርማ መኖር ጀመሩ። * እነዚህ ባልና ሚስት እዚያ እንደደረሱ በዓለም ላይ በጣም ከባድ ከሆኑት ቋንቋዎች አንዱ የሆነውን የበርማን ቋንቋ መማር ጀመሩ። ለተወሰኑ ዓመታት ቋንቋውን ካጠኑ በኋላ ጀድሰን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በምድር ላይ በሌላኛው ጫፍ የሚኖሩ ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ እየተማርን ሲሆን ሰዎቹ የሚያስቡበት መንገድ ከእኛ በጣም የተለየ ነው። . . . መዝገበ ቃላት አልነበረም፤ ሌላው ቀርቶ አንድም ቃል እንኳ የሚተረጉምልን ሰው የለም።”

ጀድሰን የበርማን ቋንቋ ከመማር ጋር በተያያዘ ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተስፋ እንዲቆርጥ አላደረጉትም። ሰኔ 1823 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በበርማ ቋንቋ ተርጉሞ አጠናቀቀ። ከጊዜ በኋላ በርማ በጦርነት ትታመስ ጀመር። ጀድሰን፣ ሰላይ እንደሆነ ስለተጠረጠረ እስር ቤት ተጣለ፤ እዚያም በሦስት ጥንድ የእግር ብረቶች የታሰረ ከመሆኑም በላይ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ከአንድ ረጅም ምሰሶ ጋር ተጠርቆ ነበር። ፍራንሲስ ዌይላንድ በ1853 ስለ ጀድሰን የሕይወት ታሪክ በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ሚስተር ጀድሰን፣ ከሚስዝ ጀድሰን ጋር እንዲገናኙና በእንግሊዝኛ እንዲነጋገሩ ሲፈቀድላቸው መጀመሪያ የጠየቃት ነገር ተርጉሞት ስለነበረው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር።” አን፣ በቤታቸው ውስጥ ተቀብሮ የሚገኘው የጀድሰን የትርጉም ሥራ እርጥበትና ሻጋታ እንዳያበላሸው ስለፈራች ትራስ ውስጥ ከትታ ከሰፋችው በኋላ ወደ ወኅኒ ቤት ወስዳ ለባለቤቷ ሰጠችው። ሁኔታዎቹ በጣም አስቸጋሪ ቢሆኑም የትርጉም ሥራው ምንም ሳይሆን መትረፍ ቻለ።

ጀድሰን ለበርካታ ወራት በእስር ቤት ከቆየ በኋላ ተለቀቀ። ይሁን እንጂ ደስታው ብዙም አልዘለቀም። በዚያው ዓመት ባለቤቱ አን ኃይለኛ ትኩሳት የያዛት ሲሆን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሕይወቷ አለፈ። ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ሁለት ዓመት እንኳ ያልሞላት ልጁ ማሪያ የማይድን በሽታ የያዛት ሲሆን ብዙም ሳትቆይ ሞተች። ጀድሰን በሐዘን ቢዋጥም ሥራውን አላቋረጠም። በመጨረሻም በ1835 ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ተርጉሞ ጨረሰ።

አንተስ ለአምላክ ቃል ፍቅር አለህ?

ለአምላክ ቃል እንደዚህ ዓይነት ፍቅር የነበራቸው እነዚህ ተርጓሚዎች ብቻ አልነበሩም። በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው መዝሙራዊ “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” በማለት ለይሖዋ አምላክ ዘምሯል። (መዝሙር 119:97) መጽሐፍ ቅዱስ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ብቻ አይደለም። በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ በማንበብ ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዳለህ ታሳያለህ? የአምላክን ቃል የምታነብና ያነበብከውን በተግባር የምታውል ከሆነ ‘ይህን በማድረግህ ደስተኛ ትሆናለህ።’—ያዕቆብ 1:25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.22 በርማ በአሁኑ ጊዜ ምያንማር ተብላ ትጠራለች። የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋም ምያንማር ይባላል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እንግሊዛውያን የክርስቶስን ሕግ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መማር የሚችሉት በእንግሊዝኛ ነው።”—ጆን ዊክሊፍ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዊልያም ቲንደል እና እሱ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ገጽ

[የሥዕል ምንጭ]

ቲንደል፦ From the book The Evolution of the English Bible

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሮበርት ሞሪሰን እና በቻይንኛ ቋንቋ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ

[የሥዕል ምንጭ]

In the custody of the Asian Division of the Library of Congress

Robert Morrison, engraved by W. Holl, from The National Portrait Gallery Volume IV, published c.1820 (litho), Chinnery, George (1774-1852) (after)/Private Collection/Ken Welsh/The Bridgeman Art Library International

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዶናይራም ጀድሰን እና በበርማ ቋንቋ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ

[የሥዕል ምንጭ]

ጀድሰን፦ Engraving by John C. Buttre/Dictionary of American Portraits/Dover

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ዊክሊፍ፦ From the book The History of Protestantism (Vol. I); መጽሐፍ ቅዱስ፦ Courtesy of the American Bible Society Library, New York