በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሰዎች በጸሎት መጨረሻ ላይ “አሜን” የሚሉት ለምንድን ነው?

“አሜን” የሚለው የአማርኛም ሆነ የግሪክኛ ቃል ከዕብራይስጡ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ነው። ብዙውን ጊዜ ጸሎት ከቀረበ እንዲሁም የመሐላ፣ የበረከት ወይም የእርግማን ቃል ከተነገረ በኋላ ሰዎች በአንድ ላይ “አሜን” ይላሉ፤ የቃሉ መሠረታዊ ትርጉምም “ይሁን” ወይም “በእርግጥ” ማለት ነው። ሰዎች “አሜን” ማለታቸው አስቀድሞ ከተገለጸው ሐሳብ ወይም ስሜት ጋር መስማማታቸውን ያሳያል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “ቃሉ፣ የተነገረው ነገር እርግጠኛ፣ እውነተኛ፣ እምነት የሚጣልበት እንዲሁም የማያጠራጥር መሆኑን ያመለክታል።” በጥንት ጊዜ አንድ ሰው ለመሐላ ወይም ለቃል ኪዳን “አሜን” ካለ በሕግ ፊት በጉዳዩ እንደተስማማና መሐላውን ቢያፈርስም የሚያስከትልበትን ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።—ዘዳግም 27:15-26

ኢየሱስ በሚሰብክበትና በሚያስተምርበት ጊዜ በአንዳንድ ዓረፍተ ነገሮች መጀመሪያ ላይ “አሜን” የሚለውን ቃል ተጠቅሞ ነበር። እንዲህ ማድረጉ ቀጥሎ የሚናገረው ሐሳብ ፍጹም እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚያጎላ ነው። ኢየሱስ በዚህ መንገድ ዓረፍተ ነገሩን በጀመረባቸው ቦታዎች ላይ አሜን የሚለው ግሪክኛ ቃል በአማርኛ “እውነት” ተብሎ ተተርጉሟል። (ማቴዎስ 5:18፤ 6:2, 5) በዮሐንስ ወንጌል ላይ በብዛት እንደሚገኘው ኢየሱስ “አሜን” የሚለውን ቃል ሁለት ጊዜ አከታትሎ በተጠቀመባቸው ቦታዎች ላይ “እውነት እውነት” ተብሎ ተተርጉሟል። (ዮሐንስ 1:51) ኢየሱስ ይህን ቃል በማከታተል የተጠቀመበት መንገድ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ አይገኝም።

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “አሜን” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስን ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ይህም ምሥክርነቱ ‘የታመነና እውነተኛ’ መሆኑን ያሳያል።—ራእይ 3:14

ኡሪምና ቱሚም የሚባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

ኡሪምና ቱሚም፣ በጥንት እስራኤል መላውን ብሔር ወይም መሪዎቻቸውን ያሳሰባቸውን ጉዳይ በተመለከተ የይሖዋን ፈቃድ ለመጠየቅ ያገለግሉ የነበሩ ነገሮች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መረዳት ይቻላል። ኡሪምና ቱሚም፣ ሊቀ ካህናቱ ይይዛቸው የነበሩ ነገሮች ሲሆኑ የሚቀመጡትም ‘በፍርድ መስጫው የደረት ኪስ’ ውስጥ ነው። (ዘፀአት 28:15, 16, 30) ቅዱሳን መጻሕፍት ኡሪምና ቱሚም ምን እንደሆኑ ወይም እንዴት ያገለግሉ እንደነበር በግልጽ ባይናገሩም የተለያዩ ጥቅሶች አምላክ የሚሰጠውን መልስ ለማወቅ የሚረዱ ነገሮች እንደነበሩ ይጠቁማሉ፤ ልክ እንደ ዕጣ አምላክ በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ለሕዝቡ “አዎን” ወይም “አይደለም” የሚል መልስ ይሰጣቸው አሊያም ደግሞ ምንም መልስ እንደማይሰጥ ያሳውቃቸው ነበር።

ኡሪምና ቱሚም እንዴት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ ወቅት ዳዊት፣ ኡሪምና ቱሚም የያዘውን ኤፉድ (የሊቀ ካህናቱ ሳይሆን አይቀርም) እንዲያመጣለት አብያታርን ጠይቆት ነበር። በዚህ ወቅት ዳዊት ለይሖዋ የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች ጠየቀ፦ ‘ሳኦል ወደዚህ መጥቶ ያሳድደኝ ይሆን?’ ‘የቅዒላ ሰዎች ለእሱ አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን?’ ይሖዋ ለሁለቱም ጥያቄዎች የሰጠው መልስ አዎን የሚል ሲሆን ይህም ዳዊት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አስችሎታል።—1 ሳሙኤል 23:6-12

ንጉሥ ሳኦልም ቀደም ሲል በኡሪምና በቱሚም ተጠቅሟል፤ በመጀመሪያ ከሕዝቡ ወይም ከእሱና ከዮናታን የበደለው ማን እንደሆነ ለመለየት፣ ቀጥሎም ከእሱና ከልጁ በደሉ በማን ላይ እንደሆነ ለማወቅ በኡሪምና በቱሚም ተጠቅሟል። (1 ሳሙኤል 14:40-42) ሳኦል መለኮታዊ ሞገስ ካጣ በኋላ ግን አምላክ “በሕልምም ሆነ በኡሪም ወይም በነቢያት” ለሳኦል መመሪያ መስጠቱን አቆመ።—1 ሳሙኤል 28:6

በአይሁዳውያን አፈ ታሪክ መሠረት የይሖዋ ቤተ መቅደስ በ607 ዓ.ዓ. ከወደመበት ጊዜ አንስቶ በኡሪምና በቱሚም መጠቀም ቀርቷል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አሜን” ራእይ 3:14 ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ 5ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.