አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?
አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?
አይደግፍም። አምላክ በኤደን የመጀመሪያውን ጋብቻ ሲያቋቁም በጋብቻ ያጣመረው አንድ ወንድና አንዲት ሴትን ነበር። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስም ለተከታዮቹ ይህንኑ ሥርዓት በመናገር የአምላክ ሐሳብ አለመለወጡን ጠቁሟል።—ዘፍጥረት 2:18-24፤ ማቴዎስ 19:4-6
ይሁንና ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት የኖሩት እንደ አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ዳዊትና ሰለሞን ያሉት ሰዎች ከአንድ በላይ ሚስቶች አግብተው አልነበረም? እውነት ነው አግብተዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የእነዚህን ሰዎች ጋብቻ በተመለከተ ምን ይጠቁማል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብርሃምም ሆነ ያዕቆብ ከአንድ በላይ ማግባታቸው በቤተሰባቸው ውስጥ ግጭትና አለመግባባት እንዲፈጠር እንዳደረገ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 16:1-4፤ 29:18 እስከ 30:24) ከጊዜ በኋላ አምላክ እያንዳንዱን የእስራኤል ንጉሥ በተመለከተ “ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ” የሚል ሕግ ሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 17:15, 17) ሰለሞን ይህንን ሕግ ችላ በማለት ከ700 በላይ ሚስቶችን አገባ! የሚያሳዝነው ሰለሞን ያገባቸው በርካታ ሚስቶች መጥፎ ተጽዕኖ ስላሳደሩበት ልቡ ይሖዋን ከማገልገል ወደ ሌላ አዘነበለ። (1 ነገሥት 11:1-4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ማግባት ጉዳት እንዳለው ያሳያል።
ያም ሆኖ አንዳንዶች፣ ‘አምላክ ሕዝቦቹ ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ለምን ፈቀደ?’ በማለት ይጠይቁ ይሆናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ መቀየር እንዳለበት እያወቅህ ለጊዜው እንዲቀመጥ የተውከው የቤት ዕቃ አለህ? ምናልባት ይህን ያደረግከው በዚህ ወቅት ዕቃውን ማስወገዱ ሌላ ችግር እንደሚያስከትል በማሰብ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ የአምላክ ሐሳብና መንገድ ከእኛ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ያም ቢሆን አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ለጊዜው የፈቀደበት በቂ ምክንያት እንዳለው ማስተዋል እንችላለን።
በኤደን ገነት ውስጥ ይሖዋ፣ ሰይጣንን የሚያጠፋ ‘ዘር’ እንደሚመጣ ቃል መግባቱን አስታውስ። በኋላ ላይ አብርሃም የታላቅ ሕዝብ አባት እንደሚሆንና አስቀድሞ የተነገረው ዘር በእሱ የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ተገልጾለታል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:18) ሰይጣን ይህ ዘር እንዳይመጣ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። በመሆኑም የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ለማጥፋት ተነስቶ ነበር። እስራኤላውያን ኃጢአት ሠርተው የአምላክን ሞገስና ጥበቃ እንዲያጡ ለማድረግ ሲል በተደጋጋሚ ጊዜያት ፈተና አቅርቦላቸዋል።
ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን በሰይጣን ወጥመድ እንዳይወድቁ ለመርዳት ሲል ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ዘወር በሚሉበት ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜያት ነቢያቱን በመላክ ያስጠነቅቃቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ከጣዖት አምልኮ መራቅን በተመለከተ የሰጣቸውን ሕግ ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን እንኳ መታዘዝ እንደሚከብዳቸው ይሖዋ ቀድሞውንም ቢሆን ያውቅ ነበር። (ዘፀአት 32:9) እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ሕግ መታዘዝ የሚከብዳቸው ከሆነ ከአንድ በላይ ማግባትን የሚከለክል ሕግ ቢወጣ ኖሮ እንዴት ሊያከብሩት ይችላሉ? ይሖዋ የሰው ልጆችን ባሕርይ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለዘመናት የቆየውን ይህን ልማድ በዚያ ወቅት ለማስቆም ጊዜው እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ልማድ የሚከለክል ሕግ ቢያወጣ ኖሮ ሰይጣን፣ እስራኤላውያን በኃጢአት እንዲወድቁ ማድረግ ቀላል ይሆንለት ነበር።
አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ለተወሰነ ጊዜ መፍቀዱ ሌሎች ጥቅሞችም ነበሩት። ይህ ልማድ የብሔሩ ቁጥር በፍጥነት እንዲያድግ አድርጓል። የሕዝቡ ቁጥር መብዛቱ ደግሞ መሲሑ እስኪመጣ ድረስ ብሔሩ ሳይጠፋ እንዲቆይ ለማድረግ አስችሏል። ከዚህም ሌላ ከአንድ በላይ ማግባት መፈቀዱ አንዳንድ ሴቶች መጠለያና ቤተሰብ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ አደገኛ በሆነ ወቅት ጥበቃ እንዲያገኙ ሳያደርጋቸው አልቀረም።
ይሁን እንጂ ይህንን ልማድ ያቋቋመው ይሖዋ እንዳልሆነ ልብ በል። ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እንዲቀጥል ቢፈቅድም ከዚህ ልማድ ጋር በተያያዘ ግፍ እንዳይፈጸም ለማድረግ ጥብቅ መመሪያዎችን አውጥቷል። (ዘፀአት 21:10, 11፤ ዘዳግም 21:15-17) ይሖዋ ሕዝቡ ከአንድ በላይ ማግባታቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሲወስን አገልጋዮቹ ጋብቻን በተመለከተ በኤደን ያወጣውን ሥርዓት ሊከተሉ እንደሚገባ በልጁ አማካኝነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከአንድ በላይ ማግባት እንደሌለባቸው አስተምሯል። (ማርቆስ 10:8) በመሆኑም የሚከተለው እውነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ሆኗል፦ የሙሴ ሕግ በጊዜው ጥሩ ነበር፤ ሆኖም ‘የክርስቶስ ሕግ’ ከዚያ የላቀ ነው።—ገላትያ 6:2