በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳሳተ ትምህርት 2፦ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉ

የተሳሳተ ትምህርት 2፦ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉ

ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?

“ቀደምት ከሆኑት የግሪክ ፈላስፎች መካከል ስለ መቃጠያ እሳት የሚገልጸው በስፋት ተቀባይነት ያገኘ አመለካከት እንዲዳብር ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ፕላቶ ነው።”—በዦርዥ ሚንዋ የተዘጋጀው ሂስትዋር ዴዝ ኦንፌር (የመቃጠያ እሳት ታሪካዊ አመጣጥ) የተባለው መጽሐፍ ገጽ 50

“የግሪክን ፍልስፍና በተወሰነ ደረጃ የተማሩ ክርስቲያኖች ከ2ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ አንስቶ . . . እምነታቸውን ከግሪክ ፍልስፍና አኳያ መግለጽ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው። . . . ይህንን ለማድረግ ይበልጥ የተስማማቸው የፕላቶ ፍልስፍና ነበር።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1988)፣ ጥራዝ 25፣ ገጽ 890

“የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የመቃጠያ እሳት እንዳለና ዘላለማዊ እንደሆነ ያረጋግጣል። ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነፍሳቸው ወዲያውኑ ወደ ሲኦል ይወርዳል፤ በዚያም ነፍሳቸው ‘በዘላለማዊ እሳት’ ይሠቃያል። በሲኦል ውስጥ ያለው ዋነኛ ቅጣት ከአምላክ ለዘላለም እንዲለዩ መደረግ ነው።”—ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች፣ የ1994 እትም፣ ገጽ 270

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም። . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።”—መክብብ 9:5, 10 የ1954 ትርጉም

‘የሙታን ማደሪያን’ የሚያመለክተው ሺኦል የሚለው የዕብራስይጥ ቃል በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ “ሲኦል” ተብሎ ተተርጉሟል። ከላይ ያለው ጥቅስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ምን ይጠቁማል? ሙታን የሠሩት ኃጢአት እንዲሰረይላቸው በሺኦል ይሠቃያሉ? በፍጹም፤ ምክንያቱም ‘ሙታን አንዳች አያውቁም።’ በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ የተባለ የአምላክ አገልጋይ በደረሰበት ከባድ ሕመም እጅግ በመሠቃየቱ “በሲኦል [በዕብራይስጥ፣ ሺኦል] ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ” በማለት አምላክን የለመነው ለዚህ ነው። (ኢዮብ 14:13 የ1954 ትርጉም) ሺኦል፣ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ቦታ ቢሆን ኖሮ ኢዮብ ያቀረበው ልመና ምን ትርጉም ይኖረዋል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲኦል፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይኖርበትን የሰው ልጆች መቃብር ያመለክታል።

ሲኦል እንዲህ ዓይነት ፍቺ ያለው መሆኑ ይበልጥ ትርጉም የሚሰጥ እንዲሁም ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ አይደለም? የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ከባድ ኃጢአት ቢሠሩ የፍቅር አምላክ ለዘላለም ያሠቃያቸዋል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ይሆናል? (1 ዮሐንስ 4:8) ይሁን እንጂ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉ የሚለው ትምህርት ስህተት ከሆነ ወደ ሰማይ ስለመሄድ ስለሚገልጸው ትምህርትስ ምን ማለት ይቻላል?

እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ መዝሙር 146:3, 4፤ የሐዋርያት ሥራ 2:25-27፤ ሮም 6:7, 23

እውነታው፦

አምላክ ሰዎችን በእሳት በማቃጠል አይቀጣም