ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
የትዳር ጓደኛ ልዩ እንክብካቤ ሲያስፈልገው
ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም የተባለ ኃይለኛ ድካም የሚያስከትልና አቅም የሚያሳጣ በሽታ ስላለብኝ ቤተሰባችንን የሚያስተዳድረው ባለቤቴ ብቻ ነበር። ወጪዎቻችንን በተመለከተ ምንም አይነግረኝም። ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማይነግረኝ ለምንድን ነው? ባለቤቴ እንዲህ የሚያደርገው ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያለንበት ሁኔታ በጣም መጥፎ ስለሆነና ይህንን ቢነግረኝ እንደምበሳጭ ስለሚያውቅ ነው ብዬ አስባለሁ።—ናንሲ *
በትዳር ውስጥ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ጤነኛ ሆኖ ሌላው በጠና ሲታመም ደግሞ ሁኔታዎች ይበልጥ ሊወሳሰቡ ይችላሉ። * የትዳር ጓደኛችሁ በጠና ታሞ እየተንከባከባችሁት ነው? ከሆነ የሚከተሉት ጉዳዮች ያስጨንቋችሁ ይሆናል፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ ጤንነት እያሽቆለቆለ ቢሄድ ሁኔታውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው? በአንድ በኩል ባለቤቴን እያስታመምኩ በሌላ በኩል ደግሞ ምግብ እያበሰልኩ፣ ቤት እያጸዳሁና በውጭ እየሠራሁ መቀጠል የምችለው እስከ መቼ ነው? እኔ ጤነኛ በመሆኔ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማኝ ለምንድን ነው?’
በሌላ በኩል ደግሞ የታመምከው አንተ ከሆንክ እንዲህ እያልክ ታስብ ይሆናል፦ ‘ኃላፊነቴን መወጣት ሳልችል ስቀር ለራሴ ጥሩ ግምት እንዲኖረኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ታማሚ በመሆኔ ባለቤቴ ትማረርብኝ ይሆን? በትዳራችን ደስተኛ መሆናችን አበቃለት ማለት ነው?’
የሚያሳዝነው አንዳንዶች፣ የትዳር ጓደኛ በጠና መታመሙ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም ስለከበዳቸው ጋብቻቸው ፈርሷል። ይህ ሲባል ግን የእናንተም ትዳር መፍረሱ አይቀርም ማለት አይደለም።
በርካታ ባለትዳሮች፣ የትዳር ጓደኛቸው ከባድ ሕመም ቢያጋጥመውም ችግሮቹን ማሸነፍ አልፎ ተርፎም ትዳራቸው የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ችለዋል። ዮሺአኪንና ካዙኩን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮሺአኪ በአከርካሪ አጥንቱ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ሌላ ሰው ሳይረዳው ምንም መንቀሳቀስ አይችልም። ካዙኩ እንዲህ ትላለች፦ “ባለቤቴ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሰው እርዳታ ያስፈልገዋል። ለእሱ በማደርገው እንክብካቤ የተነሳ አንገቴን፣ ትከሻዬንና ክንዶቼን ስለሚያመኝ የመገጣጠሚያና የአጥንት ሕክምና በሚሰጥበት ሆስፒታል ውስጥ እየተመላለስኩ እታከማለሁ። አብዛኛውን ጊዜ፣ እሱን መንከባከብ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ይሰማኛል።” እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ካዙኩ “በመካከላችን ያለው ግንኙነት ተጠናክሯል” ብላለች።
ታዲያ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ደስተኛ ለመሆን የሚረዳው ቁልፍ ምንድን ነው? አንዳንዶች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ከትዳራቸው የሚያገኙትን ደስታና እርካታ እንዳያጡ የረዳቸው አንዱ ነገር በሽታው፣ ታማሚውን የትዳር ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም የሚነካ ችግር እንደሆነ አድርገው ማሰባቸው ነው። ደግሞም አንደኛው የትዳር ጓደኛ መታመሙ በሁለቱም ላይ በተለያየ መንገድም ቢሆን ከፍተኛ ተጽዕኖ ዘፍጥረት 2:24 ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሲገልጽ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል። በመሆኑም አንደኛው የትዳር ጓደኛ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አቅም የሚያሳጣ ሕመም ሲያጋጥመው ሁኔታውን ለመቋቋም ባልና ሚስት ተባብረው መሥራታቸው ወሳኝ ነገር ነው።
ማሳደሩ አይቀርም።በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከባድ ሕመም በሚያጋጥምበት ወቅት ባለትዳሮች በመካከላቸው ያለውን ጥሩ ግንኙነት ጠብቀው ማቆየት የቻሉት ያሉበትን ሁኔታ ተቀብለው በመኖራቸው እንዲሁም ከሁኔታው ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚያስችሏቸውን መንገዶች በመማራቸው ነው። ያጋጠማቸውን ችግር ለመቋቋም ከረዷቸው ዘዴዎች አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙ ጊዜ የማይሽራቸው ምክሮች ጋር ይስማማሉ። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ምክሮች እንመልከት።
አንዳችሁ ለሌላው አሳቢነት አሳዩ
መክብብ 4:9 “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” ይላል። ለምን? ምክንያቱም ቁጥር 10 እንደሚገልጸው “አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።” እናንተስ አድናቆታችሁን በመግለጽ የትዳር ጓደኛችሁን ‘ደግፋችሁ ታነሱታላችሁ?’
አንዳችሁ ለሌላው ጠቃሚ እርዳታ ለማበርከት የሚያስችሏችሁን መንገዶች መፈለግ ትችሉ ይሆን? ዮንግ የተባለ ግማሽ አካሏ መንቀሳቀስ የማይችል የትዳር ጓደኛ ያለችው ሰው እንዲህ ብሏል፦ “በማንኛውም ሁኔታ ለባለቤቴ አሳቢነት ለማሳየት እጥራለሁ። እኔ ውኃ ሲጠማኝ እሷም ጠምቷት ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ። ወደ ውጭ ወጣ ብዬ ውብ የሆኑ አካባቢዎችን ለማየት ስፈልግ እሷም አብራኝ መሄድ ትፈልግ እንደሆነ እጠይቃታለሁ። ሁኔታው ያስከተለብንን ሥቃይ እየተጋራን ችግሮቹን አብረን በጽናት ለመቋቋም እንጥራለን።”
በሌላ በኩል ደግሞ አንተ ታምመህ የትዳር ጓደኛህ እንክብካቤ የምታደርግልህ ከሆነ ጤንነትህን ሳትጎዳ ለራስህ ማድረግ የምትችላቸው አንዳንድ ነገሮች ይኖሩ ይሆን? ከሆነ እንዲህ ማድረግህ ለራስህ ያለህ ግምት ከፍ እንዲል የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ የትዳር ጓደኛህ አንተን መንከባከቧን መቀጠል እንድትችል አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።
ለትዳር ጓደኛችሁ አሳቢነት ማሳየት የምትችሉበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምን እንደሆነ እንደምታውቁ ከማሰብ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ የበለጠ የሚፈልገው ወይም የምትፈልገው ምን እንደሆነ ለምን አትጠይቁም? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ናንሲ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ቤተሰቡ ያለበትን ሁኔታ አለማወቋ ቅር እንዳሰኛት ከጊዜ በኋላ ለባለቤቷ ነገረችው። ከዚያ በኋላ ባለቤቷ በዚህ ረገድ ያለውን ሁኔታ ሊያሳውቃት ይጥራል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኞቻችሁ አሁን ያላችሁበት ሁኔታ በትንሹም ቢሆን እንዲሻሻል እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጓቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፉ፤ እነሱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ጠይቋቸው። ከዚያም የጻፋችሁትን ተለዋወጡ። ሁለታችሁም ከቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን ምረጡ።
ሁኔታዎችን ያገናዘበ ፕሮግራም ይኑራችሁ
ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 3:1) ይሁንና አንድ የቤተሰብ አባል በጠና መታመሙ የቤተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ስለሚያዛባው ሚዛኑን የጠበቀ ፕሮግራም ማውጣት የማይቻል ነገር ይመስል ይሆናል። በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሚዛናችሁን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ሁለታችሁም ከበድ ስላሉ የሕክምና ጉዳዮች ከማሰብ ነፃ የምትሆኑባቸውን አጋጣሚዎች በየጊዜው መፍጠር ትችሉ ይሆናል። በሽታው ከመከሰቱ በፊት አብራችሁ ታደርጓቸው የነበሩ አንዳንድ ነገሮችን አሁንም ማድረግ ትችላላችሁ? ካልሆነ ደግሞ አብራችሁ ልትካፈሉባቸው የምትችሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች አሉ? አንዳችሁ ለሌላው እንደ ማንበብ ያሉ ቀላል ነገሮችን ወይም አዲስ ቋንቋ እንደ መማር ያሉ ከበድ ያሉ ተግባሮችን ልታከናውኑ ትችላላችሁ። የትዳር ጓደኛችሁ የጤና ሁኔታ እስከፈቀደላችሁ ድረስ አብራችሁ አንዳንድ ነገሮችን ማከናወናችሁ በመካከላችሁ ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ “አንድ ሥጋ” እንድትሆኑ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ደስተኞች ያደርጋችኋል።
ሚዛናዊ እንድትሆኑ የሚረዳችሁ ሌላው ነገር ደግሞ ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 18:1 ላይ “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” ይላል። ወዳጅነትን አለመፈለግ ወይም ራስን ማግለል በአስተሳሰባችን ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስተዋልክ? ከዚህ በተቃራኒ ግን በየጊዜው ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፋችሁ መንፈሳችሁ እንዲታደስ እንዲሁም ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማየት ሊረዳችሁ ይችላል። ሌሎች ወደ ቤታችሁ እንዲመጡ ለምን አትጋብዟቸውም?
አንዳንድ ጊዜ በጠና የታመመ የትዳር ጓደኛቸውን የሚንከባከቡ ሰዎች ሚዛናቸውን መጠበቅ ከባድ ሊሆንባቸው * አንዳንዶች ተመሳሳይ ፆታ ላለው የሚያምኑት ወዳጃቸው አልፎ አልፎ ጭንቀታቸውን ማውራታቸው ቀለል እንዲላቸው እንደሚረዳቸው ተገንዝበዋል።
ይችላል። አንዳንዶች ብዙ ነገሮችን ስለሚያከናውኑ ቀስ በቀስ ኃይላቸው ይሟጠጥና ጤንነታቸው ይቃወሳል። ውሎ አድሮ የሚወዱትን የትዳር ጓደኛቸውን መንከባከብ እንኳ ሊያቅታቸው ይችላል። በመሆኑም በጠና የታመመ የትዳር ጓደኛችሁን የምትንከባከቡ ከሆነ ለራሳችሁ ማድረግ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች ችላ አትበሉ። የሚረብሻችሁ ነገር ሳይኖር ዘና የምትሉበት ቋሚ ጊዜ መድቡ።እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁን ስታስታምሙ የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች በዝርዝር ጻፉ። ከዚያም እነዚህን ችግሮች ለመወጣት ወይም በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም ማድረግ የምትችሏቸውን ነገሮች አስፍሩ። ሁኔታውን እያሰባችሁ ከሚገባው በላይ ከመጨነቅ ይልቅ ‘ሁኔታውን ለማሻሻል ልወስደው የምችለው ቀላል እርምጃ ምንድን ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርጉ
መጽሐፍ ቅዱስ “‘ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?’ አትበል” በማለት ያስጠነቅቃል። (መክብብ 7:10) ስለዚህ የትዳር ጓደኛችሁ ጤንነት ባይጓደል ኖሮ ሕይወት ምን ሊመስል ይችል እንደነበር በማሰብ ከመብሰልሰል ተቆጠቡ። በዚህ ዓለም ላይ የተሟላ ደስታ ማግኘት እንደማይቻል አስታውሱ። ሁኔታውን መቀበሉና ችግሩ እያለም ሕይወታችሁን አስደሳች ለማድረግ ጥረት ማድረጉ የተሻለ ነው።
አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? ያገኛችኋቸውን በረከቶች እያነሳችሁ ተጫወቱ። በጤንነትህ ረገድ የተወሰነ መሻሻል እንኳ ስትመለከት ደስ ሊልህ ይገባል። በጉጉት የምትጠብቃቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክር፤ እንዲሁም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ሆናችሁ ልትደርሱባቸው የምትችሏቸው ግቦች አውጡ።
ሾጂ እና አኪኮ የተባሉት ባልና ሚስት ከላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን ጥሩ ውጤትም አግኝተዋል። በአንድ ወቅት አኪኮ፣ ፋይብሮሚአልጂያ የተባለ በሽታ ስለያዛት በክርስቲያናዊ አገልግሎት በሙሉ ጊዜያቸው ይካፈሉ የነበሩት እነዚህ ባልና ሚስት የነበራቸውን ልዩ የአገልግሎት መብት ለመተው ተገደው ነበር። ይህ በመሆኑ አዝነው ነበር? ማዘናቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ሆኖም ሾጂ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ላጋጠማቸው ሰዎች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “አሁን ማድረግ የማትችሏቸውን ነገሮች እያሰባችሁ አትዘኑ። አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። ነገሮች ተስተካክለው አንድ ቀን ሁለታችሁም ወደ ቀድሞው ሁኔታችሁ የመመለስ ተስፋ ቢኖራችሁ እንኳ ለጊዜው አሁን ባላችሁ ሕይወት ላይ ትኩረት አድርጉ። እኔ ይህንን ያደረግኩት ለሚስቴ ትኩረት በመስጠትና እሷን መርዳት ስለምችልበት መንገድ በማሰብ ነው።” የትዳር ጓደኛችሁ ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ከሆነ እንዲህ ያለው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር እናንተንም ሊጠቅማችሁ ይችላል።
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.4 ይህ ርዕስ የሚያተኩረው አንደኛው የትዳር ጓደኛ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይና አቅም የሚያሳጣ ሕመም በሚያጋጥመው ወቅት በሚኖረው ሁኔታ ላይ ነው። ይሁን እንጂ በአደጋ ምክንያት የአካል ጉዳት የደረሰበት ወይም እንደ መንፈስ ጭንቀት ያሉ ከስሜት ጋር የተያያዙ ችግሮች ያለበትን የትዳር ጓደኛቸውን የሚንከባከቡ ሰዎችም በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ሊጠቀሙ ይችላሉ።
^ አን.20 ያላችሁበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የሚቻል ከሆነ የጤና እንክብካቤ የሚሰጡ ባለሞያዎች ወይም ተቋማት ለተወሰነ ሰዓት እንዲረዷችሁ ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦
እኔና ባለቤቴ በአሁኑ ወቅት ይበልጥ የሚያስፈልገን . . .
-
ስለ ሕመሙ ይበልጥ መነጋገር ነው?
-
ስለ ሕመሙ ብዙ አለመነጋገር ነው?
-
ብዙ አለመጨነቅ ነው?
-
አንዳችን ለሌላው የበለጠ አሳቢነት ማሳየት ነው?
-
ከሕመሙ ጋር ያልተያያዙ ነገሮችን አብረን ማከናወን ነው?
-
ከሌሎች ሰዎች ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ ነው?
-
ሁለታችንንም የሚያሳትፉ ግቦች ማውጣት ነው?