ሁልጊዜ ሐቀኛ መሆን ይኖርብሃል?
ሁልጊዜ ሐቀኛ መሆን ይኖርብሃል?
ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ሐቀኛ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ብዙ ሰዎች ምናልባትም አብዛኛውን ጊዜ ሐቀኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ሐቀኛ ለመሆን ጥረት የሚያደርጉ ምን ያህል ሰዎች ታውቃለህ?
በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ሐቀኝነትን ሲያጓድሉ ይታያል። ይሁንና አምላክ ስለ ሐቀኝነት ምን አመለካከት እንዳለው የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ሰዎች ከአሥርቱ ትእዛዛት ስምንተኛው የሆነውን “አትስረቅ” የሚለውን ትእዛዝ ያውቃሉ። (ዘፀአት 20:15) ይሁንና በርካታ ሰዎች አንድን ሰው ሁኔታዎች እንዲሰርቅ ወይም ሌላ ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር እንዲፈጽም ሊያስገድዱት እንደሚችሉ ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ ሰዎች ለመስረቃቸው ሰበብ አድርገው የሚያቀርቧቸውን ሦስት ነገሮች እንመልከት።
ድህነት ለመስረቅ ሰበብ ይሆናል?
በአንድ ወቅት አንድ ሮማዊ የፖለቲካ ሰው “ድህነት የወንጀል እናት ናት” በማለት ተናግረው ነበር። ድሃ የሆነው ሰው ለመስረቅ ሰበብ እንዳለው ሊሰማው ይችላል። ሌሎች ሰዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማሙ ይሆናል። ኢየሱስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን አመለካከት ነበረው? ኢየሱስ ለተቸገሩ ሰዎች ይራራ እንዲሁም ‘ያዝንላቸው’ ነበር። (ማቴዎስ 9:36) ሆኖም አንድ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢገኝ ስርቆት እንዲፈጽም አበረታቶ አያውቅም። ታድያ ድሃ የሆነ አንድ ሰው ምን ማድረግ ይኖርበታል?
አምላክ እሱን ከልብ ለመታዘዝ ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች ይራራል፤ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ይባርክላቸዋል። (መዝሙር 37:25) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር፣ ጻድቁ እንዲራብ አያደርግም፤ የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል” ይላል። (ምሳሌ 10:3) ድሃ የሆነ አንድ ሰው አምላክ በገባው በዚህ ቃል መተማመን ይችላል? ቪክቶሪን በዚህ ቃል ትተማመናለች።
ቪክቶሪን ባሏ የሞተባትና አምስት ልጆች ያሏት በመሆኑ ሐቀኛ ሆኖ መኖር ለእሷ ቀላል አይደለም። በታዳጊ አገር የምትኖር በመሆኗ ከመንግሥት በቂ ድጋፍ ልታገኝ አትችልም። አብዛኛውን ጊዜ የዕለት ተዕለት ተግባሯን የምታከናውነው ከቤት ውጪ ስለነበር ለመስረቅ የሚያመቹ ብዙ አጋጣሚዎች ነበሯት። ይሁን እንጂ ቪክቶሪን መስረቅ ይቅርና አስባው እንኳ አታውቅም። ከዚህ ይልቅ በጎዳና ላይ እየተዘዋወረች አንዳንድ ነገሮችን በሐቀኝነት በመሸጥ የሚያስፈልጋትን ለማግኘት ትጥራለች። ቪክቶሪን ሐቀኝነቷን ጠብቃ የኖረችው ለምንድን ነው?
ቪክቶሪን እንዲህ ብላለች፦ “በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ሐቀኛ እንደሆነና እሱን የምመስል ከሆነ ለእኔም ሐቀኛ እንደሚሆንልኝ አምናለሁ። በሁለተኛ ደረጃ
ደግሞ ልጆቼ ሐቀኝነትን ሊማሩ የሚችሉት እኔ ሐቀኛ ሆኜ ስገኝ ብቻ ነው።”ታዲያ ኑሮዋን የምትገፋው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ምግብ፣ ልብስና መጠለያ አጥተን አናውቅም። እርግጥ ነው፣ ያልተጠበቀ ነገር ለምሳሌ ያህል የሕክምና ወጪ ሲያጋጥመኝ ጓደኞቼን እንዲረዱኝ ለመጠየቅ የምገደድበት ወቅት አለ። ምንጊዜም አንድ ነገር ጠይቄ ያጣሁበት ጊዜ የለም። ለምን? ምክንያቱም ጓደኞቼ ስላለሁበት ሁኔታ እንደማልዋሻቸውና ከሚያስፈልገኝ የበለጠ ገንዘብ ለማግኘት እንደማልሞክር ያውቃሉ።
“ልጆቼም ሐቀኞች ናቸው። በቅርቡ አንድ ጎረቤታችን ጠረጴዛ ላይ ጥቂት ሳንቲሞች አይታ ‘ልጆቹ ይወስዱታል ብለሽ አትፈሪም?’ ብላ ጠየቀችኝ። ልጆቼ ፈጽሞ እንደዚያ እንደማያደርጉ ስነግራት ማመን አቃታት። እኔ ሳላውቅ ልጆቼን ልትፈትናቸው ፈለገች። ከዚያም ማንም ሳያያት ቤታችን ውስጥ ልጆቹ በቀላሉ ሊያገኙት በሚችሉት ቦታ ሁለት ባለ መቶ ፍራንክ ሳንቲሞችን አስቀመጠች። በማግስቱ ስትመጣ ሳንቲሞቹን ማንም እንዳልወሰዳቸው ስታውቅ በጣም ተገረመች። ሐቀኛ ልጆች ማግኘት በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን ከማግኘት የበለጠ የሚክስ ነው።”
“ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነው”
በሥራ ቦታ ስርቆት የተለመደ ነገር ነው። በዚህም ምክንያት ብዙዎች “ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነው፤ ታዲያ እኔ የማላደርገው ለምንድን ነው?” ብለው ያስባሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል” ይላል። (ዘፀአት 23:2) ቪክትዎር ይህን ምክር ተግባራዊ አድርጋለች። ታዲያ ይህ ጥሩ ውጤት አስገኝቶላታል?
ቪክትዎር 19 ዓመት ሲሆናት ከዘንባባ ፍሬ ዘይት በሚያመርት በአንድ ድርጅት ውስጥ ሥራ አገኘች። ብዙም ሳይቆይ 40 የሚሆኑት የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች የዘንባባ ፍሬዎችን በዘንቢላቸው ደብቀው እንደሚወጡ አስተዋለች። ሴቶቹ በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ፍሬዎቹን ሸጠው የሦስት ወይም የአራት ቀን ደሞዝ የሚያክል ገንዘብ ያገኙ ነበር። ቪክትዎር እንዲህ ትላለች፦ “ቃል በቃል እንዲህ የማያደርግ ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል። እኔም እንደነሱ እንዳደርግ ይጠብቁብኝ ነበር፤ ሆኖም ሐቀኝነት የሕይወቴ መመሪያ እንደሆነ በመግለጽ እንደዚያ እንደማላደርግ ነገርኳቸው። ሞኝ እንደሆንኩኝ በመግለጽ ያሾፉብኝ ነበር።
“አንድ ቀን ልክ ከፋብሪካው እየወጣን እያለ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በድንገት መጣ። የሁሉንም ሠራተኞች ዘንቢል ሲፈትሽ ከእኔ በስተቀር በሁሉም ዘንቢል ውስጥ የዘንባባ ፍሬ ተደብቆ አገኘ። በዘንቢላቸው ውስጥ ፍሬው የተገኘባቸው ሠራተኞች በሙሉ እንዲባረሩ ወይም ሁለት ሳምንት ያለ ደሞዝ እንዲሠሩ ተወሰነ። በእነዚያ ሁለት ሳምንታት ሴቶቹ ሞኝ እንዳልሆንኩ ተገንዝበዋል።”
“የወደቀ አንሱ”
አንድ ሰው የጠፋበትን ውድ ነገር ብታገኝ ምን ይሰማሃል? ብዙዎች ያገኙት ነገር የራሳቸው ንብረት እንደሆነ ስለሚሰማቸው ለባለቤቱ የመመለስ ሐሳብ ፈጽሞ አይመጣላቸውም። “የወደቀ አንሱ፤ የሞተ ቅበሩ” የሚል መርሆ አላቸው። አንዳንዶቹ እንዲህ በማድረጋቸው ማንንም እንዳልጎዱ ይሰማቸው ይሆናል። ‘ባለቤቱ ፈልጎ ሲያጣው ጠፍቷል ብሎ ረስቶት ሊሆን ይችላል’ የሚል ሰበብ ያቀርቡ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ባለቤቱን መፈለግ ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚያስከትል ስለሚያስቡ እንደዚያ የማድረግ ግዴታ እንደሌለባቸው ይሰማቸዋል።
አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አለው? ዘዳግም 22:1-3 የጠፋን ዕቃ ያገኘ ሰው ዕቃውን ዝም ብሎ መውሰድ እንደሌለበት ከዚህ ይልቅ ባለቤቱ ዕቃውን ‘ፈልጎ እስኪመጣ ድረስ በቤቱ እንዲያቆየውና ባለቤቱ ሲመጣ መልሶ መስጠት እንዳለበት’ ይናገራል። የጠፋን ዕቃ ያገኘ ሰው ዕቃውን ማግኘቱን ካላሳወቀ በሌብነት ሊጠየቅ ይችል ነበር። (ዘፀአት 22:9) ታዲያ በዛሬው ጊዜ ይህ ሐሳብ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? ክሪስቲን እንዲህ ያለ እምነት አላት።
ክሪስቲን የአንድ የግል ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናት። አንድ ረቡዕ ቀን ደሞዟን ተቀብላ በምዕራብ አፍሪካ ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት ገንዘቡን አንድ ላይ በላስቲክ ታስርና ቦርሳዋ ውስጥ ከትታ ሄደች። ከዚያም ሞተር ብስክሌት አስቁማ ቀጥታ ወደ ስብሰባ አመራች። እዚያም ስትደርስ ለሾፌሩ የምትከፍለው ሳንቲም ለማውጣት ቦርሳዋን መበርበር ጀመረች። ጊዜው መሽቶ ስለነበር የታሰረው ገንዘብ ከቦርሳዋ ሲወድቅ አልታወቃትም ነበር።
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ብሌዝ የተባለ የ19 ዓመት ወጣት በዚያ በኩል አለፈ። ብሌዝ፣ ክሪስቲን በምትካፈልበት ጉባኤ ከሚገኝ አንድ ወንድም ጋር ቀጠሮ ነበረው። የታሰረውን ገንዘብ ሲመለከት አንስቶ ኪሱ ከተተው። ስብሰባው እንዳለቀ ለጓደኛው ከመንግሥት አዳራሹ ውጪ ገንዘብ ወድቆ እንዳገኘና የጠፋበት ሰው ካለ ደውሎ ሊጠይቀው እንደሚችል ነገረው።
ያን ዕለት ምሽት ክሪስቲን ወደ ቤት ስትገባ የተቀበለችው ደሞዝ እንደሌለ ስታውቅ በጣም ደነገጠች። ከሳምንት በኋላ ዦዜፊን ለተባለች ጓደኛዋ ስለ ገንዘቡ መጥፋት ስትነግራት ጉባኤያቸው መጥቶ የነበረ አንድ ሰው የወደቀ ነገር አግኝቶ እንደነበር ነገረቻት። ክሪስቲን ለብሌዝ ደውላ የጠፋው ገንዘብ የእሷ መሆኑን የሚጠቁሙ ነገሮችን ነገረችው። ብሌዝ ገንዘቡን ሲመልስላት በጣም ተደሰተች። ብሌዝስ ምን ተሰማው? ገንዘቡ ለሳምንት ያህል እሱ ጋር ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም “ገንዘቡ እኔ ጋር ከተቀመጠበት ጊዜ ይልቅ ስመልሰው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል” በማለት ተናግሯል።
ሁልጊዜ ሐቀኛ ለመሆን የሚጥሩት ለምንድን ነው?
ቪክቶሪን፣ ቪክትዎርና ብሌዝ የሚኖሩት በተለያየ አካባቢ ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ አይተዋወቁም። ሆኖም ሁሉም አንድ የጋራ የሆነ ነገር አላቸው። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐቀኝነት የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። አምላክ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ የተናገረው የሚከተለው ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ ለማየት ይናፍቃሉ፦ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።” በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጻድቅና ሐቀኞች ይሆናሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13
ቪክቶሪን አምላክ ነገሮችን የሚያስተካክልበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ኑሮዬ ሙሉ በሙሉ ይለወጣል ብላ ተስፋ አታደርግም። ይሁንና በመንፈሳዊ ሀብታም ነች፤ ይህ ደግሞ ገንዘብ ሊገዛው የሚችለው ነገር አይደለም። ልጆቿ ሐቀኞችና ሥርዓታማ ናቸው። በየሳምንቱ እሁድ በደስታ ተሞልተው ለሰዎች ስለ አምላክ ጥሩነት ይናገራሉ፤ እንዲሁም አምላክ “በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ” ፍላጎታቸውን እንዴት እንደሚያረካና “የሚወዱትን” እንዴት እንደሚጠብቅ ይናገራሉ።—መዝሙር 145:7, 18, 20
ከጊዜ በኋላ ቪክትዎር ትሠራበት ከነበረው ዘይት ፋብሪካ ለቃ ወጣች። ከዚያም ጋሪ (ከካሳቫ የሚዘጋጅ ዱቄት) በመሸጥ የራሷን ሥራ ጀመረች። ሐቀኛ መሆኗ ብዙ ደንበኞች እንድታገኝ ረድቷታል። ብዙም ሳይቆይ ገበያ የምትውልበትን ጊዜ ቀንሳ ከማጭበርበር የጸዳ ዓለም ውስጥ ስለመኖር የሚናገረውን ተስፋ ለሌሎች በመናገር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ያገባች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እሷና ባለቤቷ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው።
ክሪስቲን ገንዘቧ የወደቀው በይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፊት ለፊት ነበር። ብሌዝ በአዳራሹ ከተሰበሰቡት መካከል የሚያውቃቸው ጥቂቶቹን ብቻ ቢሆንም እዚያ ያሉት በሙሉ ሁልጊዜ ሐቀኞች ለመሆን የሚጥሩ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ እንደሆኑ ተገንዝቦ ነበር።
ከልብ ተነሳስተው ሁልጊዜ ሐቀኛ ለመሆን ጥረት የሚያደርጉ ምን ያህል ሰዎች ታውቃለህ? ሐቀኛ ከሆኑ 50, 100 ወይም 200 ሰዎች ጋር ስትሆን ምን እንደሚሰማህ እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ደስ የሚለው የይሖዋ ምሥክሮች በአዳራሾቻቸው ውስጥ የሚሰበሰቡት እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ነው። ታዲያ ወደሚሰበሰቡበት አዳራሽ ሄደህ ለምን አትተዋወቃቸውም?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሐቀኛ ልጆች ማግኘት በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን ከማግኘት የበለጠ የሚክስ ነው።”—ቪክቶሪን
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምሳሌ 6:30 ለስርቆት ሰበብ ይሆናል?
ምሳሌ 6:30 “ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም” ይላል። ይህ ጥቅስ ለስርቆት ምክንያት ይሆናል? በፍጹም። በዙሪያው ያለው ሐሳብ ሌባው ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆን አምላክ እንደሚፈልግ ይጠቁማል። ቀጥሎ ያለው ጥቅስ “በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት እጥፍ መክፈል አለበት” ይላል። (ምሳሌ 6:31) እርግጥ ነው፣ ርቦት የሰረቀ ሰው በስግብግብነት ተነሳስቶ ወይም ሆነ ብሎ ሌላውን ለመጉዳት አስቦ የሰረቀን ሰው ያህል በደለኛ ባይሆንም ‘እንዲከፍል’ ይጠበቅበት ነበር። የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በየትኛውም ዓይነት የስርቆት ተግባር መካፈል አይገባቸውም።