በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?

“ይህ ነው የማይባል ስኬት አግኝተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለወጣባቸው ፊልሞችና . . . እጅግ ተፈላጊ ለሆኑ መጻሕፍት መነሻ ሐሳብ ሆነዋል። . . . የክርስትና ኑፋቄዎች ተቀብለዋቸዋል። ለሃይማኖትም ሆነ ለተለያዩ የክህደት ጽንሰ ሐሳቦች ብቅ ማለት ምክንያት ሆነዋል።”—ሱፐር ኢንቴሬሳንቴ፣ የብራዚል የዜና መጽሔት

ይህ ሁሉ አስተያየት የተሰጠው ስለ ምንድን ነው? ይህ መጽሔት እንዲህ ያለውን አስተያየት የሰጠው በቅርቡ የብዙዎችን ትኩረት ስለሳቡትና ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች መነሻ ስለሆኑት ጽሑፎች ነው፤ እነዚህ ጽሑፎች በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በግብፅ፣ ናግ ሃማዲ በሚባለው መንደርና በሌሎች አካባቢዎች የተገኙት የሐሰት ወንጌሎች፣ መልእክቶችና ራእዮች ናቸው። እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ሰነዶች የግኖስቲክ ወይም የአፖክሪፋ (የአዋልድ) መጻሕፍት ተብለው ይጠራሉ። *

የተፈጸመ ደባ ነበር?

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መጠራጠር በጀመሩበት ዘመን ግኖስቲክ ወይም የአዋልድ መጻሕፍት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ነበር። እነዚህ መጻሕፍት በርካታ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ላስተማራቸው ትምህርቶችና ለክርስትና ሃይማኖት ባላቸው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። አንድ መጽሔት እንደገለጸው “የቶማስ ወንጌልና ሌሎች የአዋልድ [መጻሕፍት] በዚህ ዘመን መንፈሳዊ ጥማት ያላቸውን ሆኖም በሃይማኖታዊ [ድርጅት] ላይ እምነት ያጡትን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎችን ቀልብ ስቧል።” የቆጠራ ውጤቶች እንደሚያሳዩት በብራዚል ብቻ “ትምህርቶቻቸው በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ቢያንስ 30 የሚሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ።”

የእነዚህ ጽሑፎች መገኘት በአራተኛው መቶ ዘመን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ሐቁ እንዳይታወቅ ለማድረግ ደባ እንደፈጸመች፣ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚገኙት ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩ አንዳንድ ዘገባዎች እንደተሰወሩ እንዲሁም በዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የሚገኙት አራቱም ወንጌሎች እንደተዛቡ የሚገልጹት ጽንሰ ሐሳቦች በብዙዎች ዘንድ እንዲታወቁ ምክንያት ሆነዋል። የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ኢሌን ፔጀልዝ ሁኔታውን እንዲህ በማለት አስቀምጠውታል፦ “ክርስትና ብለን የምንጠራው ሃይማኖትና የክርስትና ወጎች የምንላቸው ነገሮች ከበርካታ ምንጮች መካከል ተመርጠው የተወሰዱ ጥቂት ነገሮች ብቻ መሆናቸውን ማስተዋል ጀምረናል።”

እንደ ፔጀልዝ ያሉ ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና እምነት ብቸኛው ምንጭ አይደለም፤ እንደ አዋልድ መጻሕፍት ያሉ ሌሎች ምንጮችም አሉ የሚል አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥሮች፣ “እውነተኛዋ መግደላዊት ማርያም” በሚል ርዕስ በተላለፈ አንድ የቢቢሲ ፕሮግራም ላይ የአዋልድ መጻሕፍት መግደላዊት ማርያምን እንደሚከተለው በማለት እንደገለጿት ጠቅሷል፦ “ለሌሎች ደቀ መዛሙርት አስተማሪና መንፈሳዊ መሪ ነበረች። ተራ ደቀ መዝሙር አልነበረችም፤ ለሐዋርያት ሐዋርያ ነበረች።” ክዋን አርያስ የተባለ ጸሐፊ ኦ ኤስታዶ ዴ ሳው ፓውሎ በተባለ አንድ የብራዚል ጋዜጣ ላይ መግደላዊት ማርያም ነበራት ተብሎ የሚታሰበውን የሥራ ድርሻ አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ የምናገኘው ማስረጃ ሁሉ ኢየሱስ የመሠረተው የጥንቱ የክርስትና እንቅስቃሴ ‘በሴቶች’ ላይ ያተኮረ ነበር የሚለውን አመለካከት እንድንቀበል የሚያደርገን ነው፤ ምክንያቱም የመጀመሪያዎቹ የቤት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኖች የተቋቋሙት በሴቶች ቤት ውስጥ ሲሆን በዚያም ሴቶች ቀሳውስትና ጳጳሳት ሆነው ያገለግሉ ነበር።”

ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የአዋልድ መጻሕፍት የበለጠ ክብደት ያለው መረጃ እንደያዙ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ አመለካከት እንደሚከተሉት ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን ያስነሳል፦ የክርስትና እምነት ትክክለኛ መሠረት የአዋልድ መጻሕፍት ናቸው? የአዋልድ መጻሕፍት ግልጽ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ መቀበል ያለብን የትኛውን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ወይስ የአዋልድ መጻሕፍትን? በአራተኛው መቶ ዘመን እነዚህን መጻሕፍት ለመሰወርና ስለ ኢየሱስ፣ ስለ መግደላዊት ማርያምና ስለ ሌሎች የሚናገሩትን አስፈላጊ መረጃዎች ለማውጣት ሲባል አራቱን ወንጌሎች ለማዛባት የተደረገ ደባ ነበር? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከአራቱ ወንጌሎች አንዱ የሆነውን የዮሐንስን ወንጌል እንመርምር።

የዮሐንስ ወንጌል የሚሰጠው ማስረጃ

በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ግብፅ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ፓፓይረስ ራይላንድስ 457 (P52) በመባል የሚጠራ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ ተገኝቷል። ይህ ቁራጭ በአሁኑ ጊዜ ባሉ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ያለውን ዮሐንስ 18:31-33, 37, 38⁠ን የያዘ ሲሆን ማንቸስተር፣ እንግሊዝ ጆን ራይላንድስ በተባለው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። ይህ ቅጂ በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ሁሉ በጣም ጥንታዊው ነው። በርካታ ምሑራን ይህ ቅጂ ዮሐንስ ከሞተ ከ25 ወይም ከዚያ ትንሽ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ማለትም በ125 ዓ.ም. ገደማ ተጽፏል ብለው ያምናሉ። የሚገርመው ነገር በዚህ ቁራጭ ላይ ያለው ጽሑፍ በኋላ ከተገለበጡት ቅጂዎች ጋር በጣም ይመሳሰላል። ይህን ያህል ዕድሜ ያለው የዮሐንስ ወንጌል ቅጂ፣ ቁራጩ ወደተገኘበት ወደ ግብፅ መወሰዱ የዮሐንስን ወንጌል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዮሐንስ ራሱ ጽፎታል የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የሚደግፍ ነው። በመሆኑም የዮሐንስ መጽሐፍ የዓይን ምሥክር በነበረ ሰው የተጻፈ ነው።

በሌላ በኩል ግን ሁሉም የአዋልድ መጻሕፍት የተጻፉት በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኸውም የያዟቸው ታሪኮች ከተፈጸሙ ከመቶ ወይም ከዚያ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ነው። አንዳንድ ምሑራን የአዋልድ መጻሕፍት የተጻፉት በጥንታዊ ጽሑፎች ወይም ወጎች ላይ ተመሥርተው ነው ብለው ለመከራከር ቢሞክሩም ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የላቸውም። በመሆኑም ይበልጥ እምነት ልትጥል የሚገባህ በዓይን ምሥክር በተጻፈው ነው ወይስ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከመቶ ዓመት በኋላ በኖሩ ሰዎች በተጻፈው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው። መልሱ ግልጽ ነው። *

ፓፓይረስ ራይላንድስ 457 (P52) ተብሎ የሚጠራው በሁለተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ የተገለበጠው የመጀመሪያው ቅጂ ከተጻፈ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ ነበር

ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩ አንዳንድ ዘገባዎች እንዳይታወቁ ለማድረግ ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች ላይ ለውጦች ተደርገዋል ስለሚባለው ሐሳብስ ምን ማለት ይቻላል? ሐቁን ለማዛባት ሲባል ለምሳሌ፣ በአራተኛው መቶ ዘመን በዮሐንስ ወንጌል ላይ አንዳንድ ለውጦች ተደርገዋል ለሚባለው ሐሳብ ማስረጃ ሊኖር ይችላል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በዘመናችን ለሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት መካከል አንዱን ይኸውም ቫቲካን 1209 የተባለውን በአራተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀ ቅጂ መመልከታችን አስፈላጊ ነው። አሁን በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘቱ በአራተኛው መቶ ዘመን ተለውጦ ከነበረ ለውጡ በዚህ ቅጂ ላይ መገኘት አለበት። ደስ የሚለው ነገር አብዛኛውን የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች የያዘው ቦድመር 14, 15 (P75) የተባለው ቅጂ እንደተጻፈ የሚገመተው ከ175 ዓ.ም. እስከ 225 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው። ምሑራን እንደሚሉት ከሆነ ይህ ቅጂ ይዘቱ ከቫቲካን 1209 ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። በሌላ አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች ላይ ምንም የጎላ ለውጥ እንዳልተደረገ ቫቲካን 1209 ማስረጃ ይሆነናል።

የዮሐንስ ወንጌል ወይም ሌሎች ወንጌሎች በአራተኛው መቶ ዘመን ለውጥ እንደተደረገባቸው የሚያሳይ የጽሑፍም ሆነ ሌላ ዓይነት ማስረጃ የለም። በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ፒተር ሄድ በኦክሲሪንኩስ ግብፅ በተገኙ ጥንታዊ ቁርጥራጮች ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች፣ ከጥንታዊው (ግሪክኛ) ለተገለበጡ ዘመናዊ ቅጂዎች መሠረት የሆነው የአጻጻፍ ዘዴ [በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ ከአራተኛው መቶ ዘመን ወዲህ ያሉ ጥንታዊ ጽሑፎች] ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። እነዚህ ግኝቶች የመጀመሪያዎቹን [የአዲስ ኪዳን] ጽሑፎች በአዲስ መልኩ እንድንመለከታቸው የሚያደርግ ምንም ነገር አይጠቁሙም።”

ከላይ የሚታየው በ4ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው ቫቲካን 1209 በወንጌሎች ላይ እምብዛም ለውጥ እንዳልተደረገ ማስረጃ ይሆናል

ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?

አራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎች ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ገና ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ከ160 እስከ 175 ዓ.ም. ድረስ የተጠናቀረውና በሰፊው ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የቴሸን ዳያቴሳሮን (“ከአራ[ቱ]” የሚል ትርጉም ያለው የግሪክኛ ቃል) ተቀባይነት ባላቸው በአራቱ ወንጌሎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነበር፤ ከአዋልድ “ወንጌሎች” አንዱንም እንኳ አይጨምርም። ( “በጥንት ጊዜ ለወንጌሎች ተሟግቷል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የኖረው ኢራንየስ የሰጠው አስተያየትም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። በምድር ላይ አራት አቅጣጫዎችና አራት ዋና ዋና ነፋሳት እንዳሉ ሁሉ ወንጌሎችም አራት መሆን አለባቸው የሚል ሐሳብ ሰጥቶ ነበር። ንጽጽሩ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም የተናገረው ነጥብ በዚያን ጊዜ ተቀባይነት የነበራቸው ወንጌሎች አራት ብቻ እንደነበሩ ያረጋግጣል።

እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ምን ያሳያሉ? አራቱን ወንጌሎች ጨምሮ በዛሬው ጊዜ በእጃችን የሚገኙት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ከሁለተኛው መቶ ዘመን አንስቶ እምብዛም ለውጥ አልተደረገባቸውም። በመለኮታዊ መሪነት በተጻፉት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ላይ በአራተኛው መቶ ዘመን ለውጥ ለማድረግ የተደረገ ደባ ነበር ብለን እንድናምን የሚያደርግ ጠንካራ ማስረጃ የለም። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ብሩስ መትስገር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ . . . በሜድትራንያን አካባቢ ብቻ ሳይሆን ከብሪታንያ እስከ ሜሶጶጣሚያ ድረስ ተሰራጭተው በነበሩት የተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አማኞች አብዛኛውን የአዲስ ኪዳን ክፍል በተመለከተ ፍጹም አንድ ዓይነት አቋም ነበራቸው።”

ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ደግፈው ተናግረዋል። ሁለቱም ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ከተማሩት ትምህርት ውጭ ምንም ነገር እንዳይቀበሉ ወይም እንዳያምኑ በጥብቅ አስጠንቅቀዋቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ። ምክንያቱም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እንዲታይላቸው ለማድረግ ሲጣጣሩ ከእምነት ጎዳና ወጥተዋል።” ጴጥሮስ ደግሞ እንዲህ የሚል ምሥክርነት ሰጥቷል፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መገኘት ያሳወቅናችሁ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ተከትለን ሳይሆን ግርማውን በገዛ ዓይናችን አይተን ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21፤ 2 ጴጥሮስ 1:16

ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ መሪነት “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 40:8) እኛም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈው አምላክ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ለማድረግ ሲል ቅዱሳን መጻሕፍት እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደርጋል ብለን መተማመን እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:4

^ አን.3 “ግኖስቲሲዝም” የሚለው ቃል በ2ኛው መቶ ዘመን የተነሳውን በፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ያመለክታል። ከግሪክኛ የተወሰዱት “ግኖስቲክ” እና “አፖክሪፋል” የሚሉት ቃላት በቅደም ተከተል “ሚስጥራዊ እውቀት” እና “በጥንቃቄ የተሰወረ” የሚል ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። እነዚህ ቃላት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙትና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመሆናቸው ተቀባይነት ካገኙት ወንጌሎች፣ የሐዋርያት ሥራ፣ መልእክቶችና ራእዮች ጋር በሚመሳሰል መንገድ የተዘጋጁ የሐሰት ጽሑፎችን ያመለክታሉ።

^ አን.11 ከአዋልድ መጻሕፍት ጋር በተያያዘ ሌላው አስቸጋሪ ነገር ከእነዚህ መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያሉት በጣም ጥቂት መሆናቸው ነው። ከመግደላዊት ማርያም ወንጌል ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ሦስት ቁርጥራጮች ብቻ ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ትናንሽ ቁርጥራጮች ሲሆኑ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ ረዘም የሚለው ደግሞ ዋናው ቅጂ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ግማሽ ያህል ብቻ የያዘ ነው። ከዚህም በላይ ባሉት ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል የጎላ ልዩነት አለ።