በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በስም ማወቅ አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት

አምላክን በስም ማወቅ አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት

የይሖዋን ስም እንዳታውቅና ከእርሱም ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዳይኖርህ ለማድረግ የሚፈልግ አንድ አካል አለ። ይህ ክፉ ጠላት ማነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የዚህ ሥርዓት አምላክ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።” ከአምላክ የራቀው የዚህ ሥርዓት አምላክ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ‘ስለ አምላክ የሚገልጸው ክብራማ እውቀት’ በልብህ ላይ እንዳይፈነጥቅና በጨለማ ውስጥ እንድትኖር ይፈልጋል። ሰይጣን ይሖዋን በስም እንድታውቅ አይፈልግም። ይሁን እንጂ ሰይጣን የሰዎችን አእምሮ የሚያሳውረው እንዴት ነው?—2 ቆሮንቶስ 4:4-6

ሰይጣን፣ ሰዎች አምላክን በስም እንዳያውቁ ለማድረግ ሲል የሐሰት ሃይማኖትን ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን አንዳንድ አይሁዳውያን በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት ከመከተል ይልቅ የአምላክን ስም መጥራትን በሚከለክለው ወግ ለመመራት መርጠዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ አይሁዳውያን ለሕዝብ በሚያነቡበት ጊዜ የአምላክን ስም በቅዱሳን መጽሐፎቻቸው ውስጥ በሰፈረው መንገድ ከማንበብ ይልቅ “ጌታ” የሚል ትርጉም ባለው አዶናይ የሚል ቃል እየተኩ እንዲያነቡ ይነገራቸው ነበር። ይህ ልማድ ሰዎችን ከአምላክ እንዲርቁ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። ብዙዎች ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በመመሥረት የሚገኘውን ጥቅም ሳያገኙ ቀሩ። ኢየሱስስ የይሖዋን ስም በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው?

ኢየሱስና ተከታዮቹ የአምላክን ስም አሳውቀዋል

ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ “ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:26) ኢየሱስ ይህ አስፈላጊ ስም የሚገኝባቸውን ጥቅሶች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ባነበበበት፣ በጠቀሰበትና ባብራራበት ጊዜያት ሁሉ የአምላክን ስም ተጠቅሞ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢየሱስ ከእሱ በፊት የነበሩ ነቢያት በሙሉ እንዳደረጉት የአምላክን ስም በሰፊው ተጠቅሟል። ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ በአምላክ ስም የማይጠቀሙ አይሁዳውያን ቢኖሩ ኖሮ ኢየሱስ የእነሱን ወግ እንደማይከተል የተረጋገጠ ነው። በአንድ ወቅት የሃይማኖት መሪዎችን “ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል” በማለት በጥብቅ አውግዟቸው ነበር።—ማቴዎስ 15:6

ኢየሱስ የአምላክን ስም በማሳወቅ ረገድ ምሳሌ ሆኗል

ኢየሱስ ከሞተና ከተነሣ በኋላም ታማኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክን ስም ማሳወቃቸውን ቀጥለዋል። ( “በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በአምላክ ስም ተጠቅመው ነበር?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት) የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት በ33 ዓ.ም. በተከበረበት የጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢዩኤል ትንቢት በመጥቀስ በርካታ ቁጥር ላላቸው አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ሰዎች “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:21፤ ኢዩኤል 2:32) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ይሖዋን በስም እንዲያውቁ ረድተዋል። በመሆኑም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፣ ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩ ሽማግሌዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ትኩረቱን [እንዳዞረ]” ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 15:14

ያም ቢሆን የአምላክ ስም ጠላት እጁን አልሰጠም። ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ሰይጣን ወዲያውኑ የክህደት ዘር መዝራት ጀመረ። (ማቴዎስ 13:38, 39፤ 2 ጴጥሮስ 2:1) ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ነኝ ባዩ ጀስቲን ማርተር የተወለደው የመጨረሻው ሐዋርያ ማለትም ዮሐንስ በሞተበት ዘመን አካባቢ ነበር። ያም ሆኖ ጀስቲን የሁሉ ነገር ምንጭ “በተጸውኦ ስም የማይጠራ አምላክ ነው” በማለት በተደጋጋሚ በጽሑፎቹ ላይ ያሰፍር ነበር።

ከሃዲ ክርስቲያኖች፣ ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገለብጡበት ጊዜ የይሖዋን የተጸውኦ ስም አውጥተው “ጌታ” የሚል ትርጉም ባለው ኪሪዮስ በተባለ የግሪክኛ ቃል ተክተው እንደነበር ግልጽ ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም ቢሆኑ ከዚህ የተሻለ ዕጣ አልገጠማቸውም። ከሃዲዎቹ አይሁዳውያን ጸሐፍት፣ ሲያነቡ የአምላክን ስም ድምፅ አውጥተው መጥራት አቁመው ስለነበር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከ130 በሚበልጡ ቦታዎች አዶናይ የሚለውን ስም ተኩ። በተጨማሪም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ባለውና በ405 ዓ.ም. በጀሮም በተተረጎመው ቩልጌት ተብሎ በሚጠራው በላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ የአምላክ የተጸውኦ ስም እንዳይካተት ተደርጓል።

የአምላክን ስም ለማጥፋት በዘመናችን የተደረገ ሙከራ

በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ለአይሁድ ወግ በመገዛት አልፎ ተርፎም ለትርፍ ሲሉ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተዋል

በዛሬው ጊዜ ምሑራን፣ የይሖዋ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኝ እንደነበረ ያውቃሉ። በመሆኑም ብዙ ሰዎች እንደሚጠቀሙባቸው ያሉ የካቶሊኩ ጀሩሳሌም ባይብል፣ በስፓንኛ ቋንቋ የተተረጎመው የካቶሊኩ ላ ቢብሊያ ላቲኖአሜሪካ እንዲሁም በሰፊው ተቀባይነት ያገኘው በስፓንኛ የተተረጎመው ሬና ቫሌራ ያሉ ትርጉሞች የአምላክን የተጸውኦ ስም በስፋት ተጠቅመዋል። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን ስም “ያህዌህ” ብለው ተርጉመውታል።

የሚያሳዝነው ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎም ድጋፍ የሚያደርጉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ምሑራኑ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው እንዲያወጡ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቫቲካን ለካቶሊክ ጳጳሳት ፕሬዚዳንቶች ኮንፈረንስ በጻፈችው የሰኔ 29, 2008 ደብዳቤ ላይ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእስራኤልን አምላክ ትክክለኛ ስም የመጥራት ልማድ እየታየ ነው” ይላል። ይህ ደብዳቤ “የአምላክን ስም መጠቀምም ሆነ መጥራት አይገባም” የሚል ጥብቅ መመሪያ ይዟል። ከዚህም በላይ “በዘመናዊ ቋንቋዎች ለሚተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች . . . በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለውን መለኮታዊውን ስም ‘ጌታ’ የሚል ትርጉም ባላቸው አዶናይ/ኪሪዮስ በሚሉት አቻ ቃላት መተርጎም ይኖርባቸዋል።” ይህ የቫቲካን መመሪያ የአምላክን ስም ፈጽሞ እንዲጠፋ ለማድረግ የተቃጣ ጥቃት እንደሆነ ግልጽ ነው።

በይሖዋ ስም አጠቃቀም ረገድ ፕሮቴስታንቶችም ከዚህ ባልተናነሰ ለስሙ አክብሮት እንደሌላቸው አሳይተዋል። በፕሮቴስታንቶች ድጋፍ የተዘጋጀውና በ1978 በእንግሊዝኛ የታተመው ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ትርጉም ቃል አቀባይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “ይሖዋ ለአምላክ የተሰጠ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስም ሲሆን ልንጠቀምበት ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተናል፤ ለምሳሌ፣ መዝሙር 23⁠ን ‘ያህዌህ እረኛዬ ነው’ ብለን ብንተረጉም ይህን የሚያህል ገንዘብ ገደል እንዲገባ ፈረድንበት ማለት ነው።”

በተጨማሪም አብያተ ክርስቲያናት የላቲን አሜሪካ ሰዎች አምላክን በስሙ እንዳያውቁት እንቅፋት ሆነዋል። የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የትርጉም አማካሪ የሆኑት ስቲቨን ቮት እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “እስከ ዛሬ እልባት ካላገኙት በላቲን አሜሪካ በሚገኙ ፕሮቴስታንቶች መካከል ከሚካሄዱት ክርክሮች አንዱ ይሖዋ በሚለው ስም አጠቃቀም ዙሪያ የሚያጠነጥነው ነው፤ . . . የሚያስገርመው፣ በጣም በርካታ የሆኑና ቁጥራቸው እየጨመረ የሄዱ አዳዲስ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት . . . የ1960 እትም የሆነውን የሬና ቫሌራ ትርጉም፣ ይሖዋ የሚለው ስም ሳይገባበት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ ሴንዮር [ጌታ] በሚለው ቃል እንዲተካ ፈልገዋል።” ቮት እንዳሉት ከሆነ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ይህን ጥያቄ መጀመሪያ ላይ ያልተቀበለው ቢሆንም በኋላ ግን ተሸንፎ “የይሖዋ ስም የሌለበት” የሬና ቫሌራ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም አውጥቷል።

የአምላክን ስም ከቃሉ አውጥቶ “ጌታ” በሚለው ቃል መተካት አንባቢዎች የአምላክን ማንነት በትክክል እንዳይረዱ እንቅፋት ይሆናል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ግራ መጋባት ይፈጥራል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አንባቢ “ጌታ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ይሖዋን ይሁን ወይም ልጁን ኢየሱስን ማስተዋል ሊቸግረው ይችላል። በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ዳዊት “ይሖዋ ጌታዬን [ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ] እንዲህ ብሎታል፦ ‘በቀኜ ተቀመጥ’” በማለት የተናገረውን ጥቅስ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ጌታ ጌታዬን” ብለው ተርጉመውታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:34 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) በተጨማሪም ዴቪድ ክላይንስ በጻፉት ጽሑፍ ላይ “ያህዌህና የክርስትና ሥነ መለኮት አምላክ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር “ያህዌህ ከክርስትና ግንዛቤ ውጭ የመሆኑ አንዱ ምክንያት በክርስቶስ ላይ ብቻ በመተኮሩ ነው” ብለዋል። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ጸሎቱን ያቀረበለት እውነተኛ አምላክ ይሖዋ የተባለ ስም ያለው እውን አካል መሆኑን አይገነዘቡም።

ሰይጣን፣ አምላክን በተመለከተ የሰዎችን አእምሮ ለማሳወር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ያም ቢሆን እንኳ ከይሖዋ ጋር ልትቀራረብ ትችላለህ።

ይሖዋን በስም ማወቅ ትችላለህ

ሰይጣን በመለኮታዊው ስም ላይ ጦርነት እንደከፈተ የተረጋገጠ ነው፤ ለዚህም የሐሰት ሃይማኖትን በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀመበት ነው። ይሁንና ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ስለ እሱም ሆነ ታማኝ ለሆኑ የሰው ልጆች ስላዘጋጀው ታላቅ ዓላማ እውነቱን ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ስሙን እንዳያሳውቅ በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ሊያግደው የሚችል ምንም ኃይል የለም።

የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እንዴት ወደ አምላክ መቅረብ እንደምትችል እንድታውቅ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ወደ አምላክ ሲጸልይ “ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስን አርዓያ ይከተላሉ። (ዮሐንስ 17:26) ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመባረክ ሲል ስለተጫወታቸው የተለያዩ ሚናዎች በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ስታሰላስል ታላላቅ የሆኑ ባሕርያቱ ስላላቸው ውብ ገጽታዎች በይበልጥ ትረዳለህ።

ታማኙ ኢዮብ ‘የአምላክ ወዳጅ’ እንደነበረ ሁሉ አንተም አምላክን ወዳጅህ ማድረግ ትችላለህ። (ኢዮብ 29:4) በአምላክ ቃል እውቀት አማካኝነት ይሖዋን በስም ማወቅ ትችላለህ። እንዲህ ያለው እውቀት ይሖዋ “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” ብሎ ከተናገረው የስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ እርምጃ እንደሚወስድ እንድትተማመን ይረዳሃል። (ዘፀአት 3:14 NW) በመሆኑም ለሰው ልጆች የሰጣቸውን ግሩም ተስፋዎች በሙሉ በእርግጠኝነት ይፈጽማል።