በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ያልገባው ለምን ነበር?

ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ያልገባው ለምን ነበር?

ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ያልገባው ለምን ነበር?

በሠላሳ ሁለት ዓ.ም. የተከናወነን አንድ ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ይህ ሁኔታ የተከናወነው ወደ አመሻሹ ላይ ነው። በትንቢት አስቀድሞ በተነገረው መሠረት መሲሕ የሆነው ኢየሱስ የታመሙትን በመፈወስ አልፎ ተርፎም የሞቱትን በማስነሳት ዝና ካተረፈ ሰነባብቷል። በዚህ ወቅት ደግሞ ታላላቅ ተአምራትን በመፈጸሙና የአምላክን ቃል በማስተማሩ በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ አክብሮት አተረፈ። ርቧቸው የነበሩትን እነዚህን ሰዎች በትንንሽ ቡድኖች ከፋፍሎ አስቀመጣቸው። ከዚያም ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ በተአምራዊ መንገድ ሁሉንም መገባቸው። ቀጥሎም ምንም ነገር እንዳይባክን የተረፈው እንዲሰበሰብ አደረገ። ሕዝቡ ይህን ሁሉ ሲመለከቱ ምን አደረጉ?—ዮሐንስ 6:1-13

ሕዝቡ፣ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት እንዲሁም እነሱን በሥርዓት በማደራጀትና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ረገድ ያሳየውን የአመራር ብቃት ሲመለከቱ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ንጉሥ ሊሆን እንደሚችል ተሰማቸው። (ዮሐንስ 6:14) ደግሞም እንዲህ ቢሰማቸው የሚያስገርም አይደለም። ብቃት ያለው ጥሩ መሪ በጣም ያስፈልጋቸው እንደነበር አስታውስ፤ የሚወዷት የትውልድ አገራቸው በባዕድ መንግሥት የጭቆና አገዛዝ ሥር ወድቃለች። ስለዚህ ኢየሱስ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ሊጫኑት ሞከሩ። ይህን ሁኔታ በአእምሯችን ይዘን ኢየሱስ ምን ምላሽ እንደሰጠ እስቲ እንመልከት።

“ኢየሱስ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ” በማለት ዮሐንስ 6:15 ይናገራል። ኢየሱስ አቋሙን በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። በአገሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ፈጽሞ ፈቃደኛ አልነበረም። እስከ መጨረሻውም በዚህ አቋሙ ጸንቷል። የእሱ ተከታዮችም ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) ኢየሱስ ይህን አቋም የያዘው ለምን ነበር?

ኢየሱስ ገለልተኝነትን የመረጠው ለምን ነበር?

በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ኢየሱስ የነበረው የገለልተኝነት አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነበር። እስቲ ሁለት ጥቅሶችን እንመልከት።

“ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክብብ 8:9) መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆችን አገዛዝ በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለረጅም ጊዜ መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ኖሯል። (ዮሐንስ 17:5) በመሆኑም የሰው ልጅ፣ ምንም ያህል በቅን ልቦና ቢነሳሳ የዓለም ሕዝብ የሚያስፈልገውን ነገር በተገቢ ሁኔታ ለማሟላት አቅም እንደሌለው እንዲሁም አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ራሱን የማስተዳደር ችሎታ እንዳልሰጠው ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (ኤርምያስ 10:23) ኢየሱስ የሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት ከሰብአዊ መንግሥታት ሳይሆን ከሌላ ምንጭ እንደሆነ ያውቅ ነበር።

“መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው።” (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ሐሳብ ያስደነግጥሃል? ለብዙዎች አስደንጋጭ ይሆንባቸዋል። ምክንያቱም ያለንበት ዓለም የተሻለና ከስጋት ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ በቅን ልቦና ተነሳስተው በመንግሥታዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚገቡ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ። ይሁንና ቅን ልቦና ያላቸው መሪዎችም እንኳ የቱንም ያህል ቢጥሩ ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት የጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሸነፍ አይችሉም። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30) ኢየሱስ ለአንድ የፖለቲካ ሰው “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎ የነገረው ለዚህ ነው። (ዮሐንስ 18:36) ኢየሱስ ወደፊት የአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ንጉሥ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ቢገባ ኖሮ ለአባቱ መንግሥት ታማኝ ሳይሆን ይቀር ነበር።

ታዲያ ኢየሱስ ተከታዮቹ ለምድራዊ መንግሥታት ምንም ግዴታ እንደሌለባቸው አስተምሮ ነበር? በፍጹም! እንዲያውም አምላክ የሚጠብቅባቸውን በማሟላትና ለሰብዓዊ መንግሥታት ያለባቸውን ግዴታ በመወጣት ረገድ ሚዛናዊ መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል።

ኢየሱስ ለመንግሥታዊ ሥልጣን አክብሮት ነበረው

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ እያስተማረ ሳለ ተቃዋሚዎቹ፣ ሕዝቡ ግብር መክፈል ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ በመጠየቅ ሊያጠምዱት ሞክረው ነበር። ኢየሱስ ግብር መክፈል እንደሌለባቸው ቢናገር ይህ ዓመፅ እንደማነሳሳት ሊቆጠርበት አልፎ ተርፎም ከሮም መንግሥት የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ የሚጓጓውን ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ሊቀሰቅሰው ይችል ነበር። መክፈል እንዳለባቸው ቢናገር ደግሞ ብዙዎች የሚፈጸምባቸውን የፍትሕ መጓደል ከምንም እንዳልቆጠረው ሊሰማቸው ይችል ነበር። ኢየሱስ የሰጠው መልስ ፍጹም ሚዛናዊ ነበር። “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” አላቸው። (ሉቃስ 20:21-25) ስለዚህ ተከታዮቹ ለአምላክም ሆነ ለቄሳር ማለትም ለሰብዓዊ መንግሥታት ግዴታ አለባቸው።

መንግሥታት በመጠኑም ቢሆን ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋሉ። ዜጎቻቸው ሐቀኛ እንዲሆኑ፣ ግብር እንዲከፍሉና ሕግን እንዲያከብሩ የሚጠይቁ ሲሆን ይህን ማድረጋቸውም ተገቢ ነው። ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር” በመስጠት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? የኢየሱስ ወላጆች አስቸጋሪ በሆነ ወቅትም ጭምር ለቄሳር ታዛዥ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የሮም ንጉሠ ነገሥት የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ ባወጣ ጊዜ ዮሴፍና ነፍሰ ጡር የነበረችው ሚስቱ ማርያም 150 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው ወደ ቤተልሔም ሄደዋል። (ሉቃስ 2:1-5) ኢየሱስም እንደነሱ ሕግ አክባሪ ስለነበረ ግብር መክፈል በማይጠበቅበት ጊዜም እንኳ ከፍሏል። (ማቴዎስ 17:24-27) በተጨማሪም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ጣልቃ ባለመግባት ሥልጣኑን አላግባብ ከመጠቀም ተቆጥቧል። (ሉቃስ 12:13, 14) ኢየሱስ በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ለመንግሥታዊ ሥርዓት አክብሮት ነበረው ማለት እንችላለን። ይሁንና ኢየሱስ ‘የአምላክ የሆነውን ነገር ለአምላክ ስጡ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ኢየሱስ ‘የአምላክ የሆነውን ነገር ለአምላክ’ የሰጠው እንዴት ነበር?

ኢየሱስ፣ አምላክ ለሰዎች ከሰጣቸው ሕግጋት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ በአንድ ወቅት ተጠይቆ ነበር። ክርስቶስ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” (ማቴዎስ 22:37-39) ኢየሱስ ‘የአምላክ የሆነውን ነገር ለአምላክ በመስጠት’ ረገድ በቀዳሚነት ለአምላክ ልንሰጠው የሚገባው ነገር ፍቅር እንደሆነና ይህም በሙሉ ልብ ወይም ሙሉ በሙሉ ለእሱ ታማኝ መሆንን እንደሚያጠቃልል አስተምሯል።

እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለሁለት ወገኖች ማሳየት ይቻላል? በአንድ በኩል ለይሖዋ አምላክና ለሰማያዊ መንግሥቱ በሌላ በኩል ደግሞ ለምድራዊ መንግሥታት ታማኝ መሆን እንችላለን? ኢየሱስ ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም ለአንዱ ተገዝቶ ሌላውን ይንቃል።” (ማቴዎስ 6:24) ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ የነበረው አምላክንና ሀብትን በአንድነት መውደድን አስመልክቶ ቢሆንም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ አመለካከት እንደነበረው ግልጽ ነው፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ተከታዮቹም እንደዚህ ይሰማቸው ነበር።

በጣም ጥንታዊ የሆኑት የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ አልነበራቸውም። የሚያመልኩት ክርስቶስ ያመለከውን አምላክ ብቻ ስለነበር ለሮምና ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ እንደሚሆኑ ቃል ለመግባት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠትና መንግሥታዊ ሥልጣን ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ስደት ደርሶባቸዋል። ክርስቲያኖች ለሰው ዘር ጥላቻ እንዳላቸው በመግለጽ ጠላቶቻቸው የወነጀሏቸው ጊዜ ነበር። ይሁንና ይህ ውንጀላ ትክክል ነበር?

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሰዎች ያስባሉ

ኢየሱስ ከሁሉ ከሚበልጡት ትእዛዛት ሁለተኛው “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ መናገሩን አስታውስ። ከዚህ ትእዛዝ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ነኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ የሰውን ዘር ሊጠላ አይችልም። ኢየሱስ ሰዎችን ይወድ፣ እነሱን ለመርዳት ተግቶ ይሠራ እንዲሁም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ጭምር ያሟላላቸው ነበር።—ማርቆስ 5:25-34፤ ዮሐንስ 2:1-10

ይሁንና ኢየሱስ በዋነኝነት ይታወቅ የነበረው በምን ነበር? ኢየሱስ የታመሙትን የፈወሰ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመገበ እንዲሁም ሙታንን ያስነሳ ቢሆንም ከእነዚህ አስደናቂ ተግባሮች ጋር የተያያዘ ስም አልተሰጠውም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች “መምህር” እያሉ ይጠሩት ነበር፤ እንዲህ ብለው መጥራታቸውም ትክክል ነበር። (ዮሐንስ 1:38፤ 13:13) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋና ምክንያት ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማር እንደሆነ ገልጿል።—ሉቃስ 4:43

የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮችም ጌታቸው በዚህ ምድር ሳለ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ሲያከናውን በነበረው ሥራ ይኸውም ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በማስተማሩ ሥራ ራሳቸውን የሚያስጠምዱት ለዚህ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች በመላው ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲያስተምሩ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ከሙስናና ከምግባረ ብልሹነት የጸዳው ይህ ሰማያዊ መንግሥት በአምላክ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ከፍቅር ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ ይገዛል። ይህ መንግሥት መከራና ሞትንም እንኳ ሳይቀር በማጥፋት የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን መልእክት “ምሥራች” ብሎ መጥራቱ ምንም አያስደንቅም!—ሉቃስ 8:1

ይሁንና በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እየፈለግህ ከሆነ ለይተህ ልታውቃቸው የምትችለው እንዴት ነው? በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ መሆን አለባቸው? ወይስ በዋነኝነት ትኩረት ሰጥተው የሚያከናውኑት ኢየሱስ ያከናወነውን ሥራ ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክና የማስተማሩን ሥራ መሆን ይገባዋል?

ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ሕይወትህን እንዴት እንደሚለውጠው የበለጠ ብታውቅ ደስ ይልሃል? በአካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድታነጋግር አለዚያም የሚለውን የይሖዋ ምሥክሮች ድረ ገጽ እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበረሰቡን ይረዳሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ናቸው። ይሁን እንጂ በአካባቢያቸው የሚገኙ ሰዎች ምንም ዓይነት ዘርና የኑሮ ደረጃ ይኑራቸው እነሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ጥቂት ማስረጃዎችን እንመልከት፦

▪ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት ተነሳስተው መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን መልእክት እንዲሁም ይህ መልእክት ከጎጂ ልማዶችና ተግባሮች ለመላቀቅ፣ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ለመመሥረት አልፎ ተርፎም በሌሎች መንገዶች ሕይወትን ለማሻሻል እንዴት እንደሚረዳ ለሰዎች በማስተማር በዓመቱ በድምሩ ከ1.5 ቢሊዮን ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ።

▪ ሌላ ጽሑፍ ታትሞባቸው የማያውቁ አንዳንድ ቋንቋዎችን ጨምሮ ከ500 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ጽሑፎችን እያተሙ ያለ ክፍያ ያሠራጫሉ።

▪ ግልጽና ሥርዓታማ በሆነ መንገድ በሕዝብ ፊት ሐሳብን በመግለጽ ረገድ ሥልጠና የሚሰጡ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ሥልጠና ተጠቅመዋል።

▪ በመላው ዓለም የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም የሚያካሂዱ ሲሆን በዚህም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ረድተዋል።

▪ በዓለም ዙሪያ ከ400 በላይ የሚሆኑ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸውን ማዕከሎች በመገንባቱ ሥራ እንዲካፈሉ ሙያዊ ሥልጠና ሰጥተዋል። ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ከ20,000 በላይ የአምልኮ ቦታዎችን ወይም የመንግሥት አዳራሾችን ገንብተዋል።

▪ የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክር ለሆኑና ላልሆኑ ሰዎች እርዳታ በመስጠት ተግባር ይካፈላሉ። በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ በከባድ አውሎ ነፋስ በተከታታይ ከተመታች በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ ፈቃደኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከ90 በላይ የመንግሥት አዳራሾችንና 5,500 መኖሪያ ቤቶችን መልሰው ሠርተዋል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ሕዝቡ ጫና ባደረገበት ወቅት ‘ብቻውን ወደ ተራራ’ ገለል አለ