አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
አንድ ሰው ደስተኛ ለመሆን የግድ ማግባት ይኖርበታል?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የግድ ማግባት እንዳለበት ይናገራል? የአምላክ ቃል ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን ሐሳብ በጥልቀት ካላየን እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚደግፍ ሊመስል ይችላል። እንዴት?
የዘፍጥረት ዘገባ እንደሚገልጸው አምላክ፣ የመጀመሪያው ሰው አዳም “ብቻውን መሆኑ መልካም [እንዳልሆነ]” ተናግሯል። በመሆኑም አምላክ ለአዳም “ረዳት” ወይም ማሟያ እንድትሆን ሔዋንን ፈጠራት። (ዘፍጥረት 2:18) ከዚህ ዘገባ በመነሳት፣ አንድ ሰው ሙሉ እንዲሆን ረዳት ስለሚያስፈልገው ማግባት አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርስ ይሆናል። በተጨማሪም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋብቻ በረከትና ደስታ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ። የሩትን ታሪክ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጠቀስ ይቻላል።
ይሁን እንጂ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ካላገቡና ልጅ ካልወለዱ አስደሳች፣ ትርጉም ያለውና የተሟላ ሕይወት መምራት እንደማይችሉ ያሳያሉ? በፍጹም! በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ትርጉም ያለውና የተሟላ ሕይወት የመራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይሁንና ኢየሱስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ አላገባም። እስከዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ኢየሱስ ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነው የይሖዋ ፍጹም ነጸብራቅም ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ በዚህ ዓለም ላይ ደስተኛ እንድንሆንና በረከት እንድናገኝ የሚያደርጉን ነገሮች ምን እንደሆኑ ዘርዝሯል። (ማቴዎስ 5:1-12) ይሁን እንጂ ጋብቻን በዚህ ዝርዝር ውስጥ አላካተተውም።
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ሐሳብ እርስ በርሱ ይጋጫል? በጭራሽ! ጋብቻን ከይሖዋ ዓላማ አንጻር መመልከት ይኖርብናል። አምላክ ጋብቻን ያዘጋጀው የትዳር ጓደኛሞች ደስታና የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው እንዲሁም እርስ በርስ እንዲደጋገፉ ስለሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ፈቃዱን በማስፈጸም ረገድ ወሳኝ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክትም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለአዳምና ለሔዋን የነበረው ዓላማ ‘እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሏት’ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) አዳምም ሆነ ሔዋን ለየብቻቸው ይህን የአምላክ ዓላማ ሊፈጽሙ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ አንዳቸው የሌላው እርዳታ የግድ ያስፈልጋቸዋል።
በተመሳሳይም ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር በነበረው ግንኙነት ጋብቻንና የቤተሰብ ሕይወትን ለየት ያለ ዓላማ ለመፈጸም ተጠቅሞበታል። ሕዝቦቹ በጠላቶቻቸው እንዳይጠፉ ሲል በቁጥር እንዲበዙ ይፈልግ ነበር። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚያወጣው መሲሕ በይሁዳ ነገድ በኩል እንዲመጣ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 49:10) በመሆኑም በእስራኤል በነበሩ ታማኝ ሴቶች ዘንድ ባል ማግባትና ልጅ መውለድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች ነበሩ፤ እንዲያውም ይህን ማድረግ አለመቻል ለኃፍረትና ለሐዘን እንደሚዳርግ ይቆጠር ነበር።
ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? በሕዝብ በተሞላችው ፕላኔታችን ላይ የሚኖሩት ክርስቲያኖች፣ አምላክ “ምድርን ሙሏት” በማለት ጥንት የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ሲሉ አግብተው ልጆች መወለድ ይጠበቅባቸዋል? በፍጹም! (ማቴዎስ 19:10-12) ከዚህም ሌላ አምላክ፣ መሲሑ የሚመጣበትን የዘር ሐረግ ወይም ይህን አዳኝ የሚያስገኘውን ብሔር በአሁኑ ጊዜ ከጥቃት መጠበቅ አያስፈልገውም። ታዲያ ክርስቲያኖች ለትዳርና ለነጠላነት ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
ጋብቻም ሆነ ነጠላነት ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው ሊባል ይችላል። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ስጦታ ለሌላው ያን ያህል የማያስደስት ሊሆን ይችላል። ትዳር በቤተሰብ ውስጥ ፍቅር፣ ወዳጅነትና የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችል ቅዱስ ዝግጅት ነው። ያም ቢሆን ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ላይ ትዳር የሚመሠርቱ ሰዎች ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ወይም “በሥጋቸው ላይ መከራ” እንደሚደርስባቸው በመግለጽ ስለ ትዳር ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ነጠላነትን ለኃፍረት ወይም ለሐዘን እንደሚዳርግ ነገር አድርጎ አይመለከተውም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ቃል፣ ነጠላነት ከማግባት የተሻለ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ይገልጻል።—1 ቆሮንቶስ 7:28, 32-35
ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻም ሆነ ስለ ነጠላነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። የጋብቻና የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ፣ ነጠላም ሆኑ ያገቡ አገልጋዮቹ በሙሉ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል።