መከራ የሚወገድበት ጊዜ ቀርቧል!
ወንጀል፣ ጦርነት፣ በሽታና የተፈጥሮ አደጋዎች በሌሉበት ይኸውም ከመከራ ነፃ በሆነ ዓለም መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ ስለ መድልዎ፣ ጭቆና ወይም የኢኮኖሚ አለመረጋጋት መጨነቅ እንደማይኖርብህ ስታውቅ ምን ያህል እፎይታ እንደሚሰማህ አስብ። ይህ ሁሉ ሊፈጸም የማይችል የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማሃል? እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ሰው ወይም ሰዎች ያቋቋሙት የትኛውም ድርጅት እንዲህ ያሉትን ሁኔታዎች ሊያመጣ አይችልም። ይሁን እንጂ አምላክ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተመለከትናቸውን ጨምሮ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ ለማስወገድ ቃል ገብቷል። የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ተስፋዎች እስቲ እንመልከት፦
መልካም አስተዳደር
“የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44
የአምላክ መንግሥት፣ በሰማይ ሆኖ የሚገዛ መስተዳድር ነው። የዚህ መንግሥት መሪ እንዲሆን የተመረጠው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሁሉንም ሰብዓዊ አገዛዞች አስወግዶ መግዛት ይጀምራል፤ በዚህ ጊዜ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ጭምር እንዲፈጸም ያደርጋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ መንግሥት ‘የጌታችንና የአዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት’ ስለሆነ ከዚያ በኋላ በማንኛውም ዓይነት ሰብዓዊ መስተዳድር አይተካም። ይህ መንግሥት፣ ሰላም ለዘለቄታው እንዲሰፍን ያደርጋል።—2 ጴጥሮስ 1:11
የሐሰት ሃይማኖት ይጠፋል
“ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን ይለዋውጣል። ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል በየጊዜው ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል።”—2 ቆሮንቶስ 11:14, 15
የሐሰት ሃይማኖት የዲያብሎስ ሥራ መሆኑ ተጋልጦ ከምድር ይወገዳል። በሃይማኖት ቆስቋሽነት የሚፈጠረው ጭፍን ጥላቻ እና ደም መፋሰስ አይኖርም። ይህ ደግሞ “ሕያው የሆነውንና እውነተኛውን አምላክ” የሚወድዱ ሁሉ እሱን ‘በአንድ እምነት’ እንዲሁም “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩት ያስችላቸዋል። በዚህ ወቅት የሚኖረው ሰላምና አንድነት ተወዳዳሪ አይኖረውም!—1 ተሰሎንቄ 1:9፤ ኤፌሶን 4:5፤ ዮሐንስ 4:23
የሰው ልጆች ፍጹም ይሆናሉ
“አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4
ይሖዋ አምላክ፣ ለሰው ዘር ሕይወቱን አሳልፎ በሰጠው በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ይህ ሁሉ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዮሐንስ 3:16) በኢየሱስ አገዛዝ ሥር የሰው ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳል። ‘አምላክ ራሱ ከእነሱ ጋር ስለሚሆን’ እና ‘እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ስለሚጠርግ’ ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት መከራ አይኖርም። አለፍጽምናና መከራ የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ፤ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
ክፉ መናፍስት አይኖሩም
“እሱም [ኢየሱስ ክርስቶስ] ዘንዶውን ያዘውና ለአንድ ሺህ ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስና ሰይጣን የሆነው የመጀመሪያው እባብ ነው። . . . ከእንግዲህ ብሔራትን እንዳያሳስት ወደ ጥልቁ ወረወረውና ዘጋበት፤ በማኅተምም አሸገው።”—ራእይ 20:2, 3
ሰይጣንና አጋንንቱ ታስረው “ወደ ጥልቁ” ሲወረወሩ ይኸውም ምንም ማድረግ እንዳይችሉ ሲታገዱ ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይቀራል። ሰይጣንና አጋንንቱ ከዚያ በኋላ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ክፉ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። ከሰይጣንና ከክፉ መናፍስቱ ተጽዕኖ ነፃ በሆነ ዓለም ላይ መኖር እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!
‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ያልፋሉ
ኢየሱስ “ታላቅ መከራ” ብሎ የጠራው ወቅት ሲመጣ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ያበቃሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል።”—ማቴዎስ 24:21
ይህ መከራ ታላቅ የተባለው፣ ከዚያ በፊት ታይተው የማይታወቁ መቅሠፍቶች የሚከሰቱበት ወቅት ስለሆነ ነው። ታላቁ መከራ ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ይደመደማል፤ ይህ ጦርነት፣ “አርማጌዶን” ተብሎም ይታወቃል።—ራእይ 16:14, 16 የግርጌ ማስታወሻ
ትክክል የሆነውን ነገር የሚወዱ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። እነዚህ ሰዎች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ከሚያገኟቸው በረከቶች መካከል እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።
አምላክ ከዚህም የበለጠ ያደርጋል!
“እጅግ ብዙ ሕዝብ” በሕይወት ተርፈው ሰላም ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም ይገባሉ፦ ቁጥራቸው የማይታወቅ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” “ታላቁን መከራ አልፈው [እንደሚመጡ]” እንዲሁም ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚገቡ የአምላክ ቃል ይናገራል። (ራእይ 7:9, 10, 14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እነሱም መዳን ያገኙት “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” በተባለው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ዮሐንስ 1:29
መለኮታዊ ትምህርት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፦ በአዲሱ ዓለም ውስጥ “ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) በዚህ ወቅት የሚሰጠው መለኮታዊ ትምህርት፣ የሰው ልጆች በሙሉ እርስ በርስ እንዲሁም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጋር ተስማምተው መኖር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ሥልጠናን ይጨምራል። አምላክ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17
በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ከመቃብር ይወጣሉ፦ ኢየሱስ በምድር ሳለ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። (ዮሐንስ 11:1, 5, 38-44) ይህም ኢየሱስ፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚያከናውነውን ከዚህ እጅግ የላቀ ተግባር የሚያሳይ ናሙና ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
ሰላምና ጽድቅ ለዘላለም ይሰፍናል፦ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ዓመፅ የተረሳ ነገር ይሆናል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ልብን ማንበብ ስለሚችል ይህን ችሎታውን ጻድቁን ከክፉው ለመለየት ይጠቀምበታል። ክፉ መንገዳቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም።—መዝሙር 37:9, 10፤ ኢሳይያስ 11:3, 4፤ 65:20፤ ማቴዎስ 9:4
ወደፊት ስለሚመጣው አስደናቂ ዘመን ከሚገልጹት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መካከል እስካሁን የመረመርነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። የአምላክ መንግሥት ምድርን መግዛት ሲጀምር “ታላቅ ሰላም” ለዘላለም ይሰፍናል። (መዝሙር 37:11, 29) ለሰው ዘር ሥቃይና መከራ ምክንያት የሆኑት ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ። አምላክ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ። . . . እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና እውነት [ናቸው]።”—ራእይ 21:5