በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ የሚችል አለ?

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ የሚችል አለ?

ሁላችንም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንፈልጋለን። ምክንያቱም የራሳችንም ሆነ የቤተሰባችን የወደፊት ሕይወት ያሳስበናል። በዚህም የተነሳ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፦ ‘ልጆቼ በተሻለ ዓለም ውስጥ ይኖሩ ይሆን? ምድር በአንድ ዓይነት አደጋ ትጠፋ ይሆን? የወደፊቱ ሕይወቴ የተሻለ እንዲሆን አሁን ማድረግ የምችለው ነገር ይኖራል?’ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ መጓጓታችን ተፈጥሯዊ ነው፤ ምክንያቱም ሕይወታችን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ብሎም ሥርዓት በሰፈነበት ዓለም ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእርግጠኝነት ማወቅ ብትችል ኖሮ በአካልም ሆነ በስሜት ተዘጋጅተህ ትጠብቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም።

ታዲያ የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልሃል? ይህን ማወቅ የሚችል አለ? ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ የሚሞክሩ ባለሙያዎች ከተናገሯቸው ትንቢቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ቢፈጸሙም አብዛኞቹ ግን ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። በሌላ በኩል ግን አምላክ ወደፊት የሚፈጸሙ ክስተቶችን በትክክል መተንበይ እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ። የአምላክ ቃል “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ” ይላል። (ኢሳይያስ 46:10) ታዲያ አምላክ የተነበያቸው ነገሮች ምን ያህል በትክክል ተፈጽመዋል?

ትንቢቶቹ ምን ያህል በትክክል ተፈጽመዋል?

አምላክ በጥንት ጊዜ የተናገራቸው ትንቢቶች ምን ያህል በትክክል እንደተፈጸሙ ማወቅህ ምን ጥቅም አለው? እስቲ ነገሩን በምሳሌ እንመልከት፦ አንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያ በየዕለቱ የሚናገራቸው ትንበያዎች በትክክል እንደሚፈጸሙ ብትመለከትና ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ቢቀጥል መገረምህ አይቀርም። ይህ ሰው ስለ ነገ የአየር ሁኔታ የሚናገረውን ነገር ትኩረት ሰጥተህ እንደምታዳምጥ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም አምላክ የሚተነብያቸው ነገሮች አንድም ሳይቀር በትክክል እንደተፈጸሙ ብትረዳ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገረውን ለማወቅ እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም።

በጥንቷ ነነዌ ፍርስራሽ ውስጥ በድጋሚ የተገነባ ግንብ

የአንዲት ታላቅ ከተማ ጥፋት፦

ለምሳሌ ያህል፣ ለብዙ ዘመናት ኃያል ሆና የኖረች አንዲት ትልቅ ከተማ በቅርቡ ትጠፋለች ብሎ በትክክል መተንበይ በራሱ አስደናቂ ነገር ነው። አምላክ በአንድ ነቢይ በኩል ተመሳሳይ ነገር ይኸውም ስለ ነነዌ ጥፋት ተናግሮ ነበር። (ሶፎንያስ 2:13-15) ታዲያ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለዚህ ጉዳይ ምን ብለዋል? በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ማለትም አምላክ ትንቢቱን ካስነገረ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ ባቢሎናውያንና ሜዶናውያን በነነዌ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ገለበጧት። በተጨማሪም አምላክ ነነዌ “ፍጹም ባድማ፣ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ” እንደምትሆን በመናገር ዝርዝር ጉዳዮችን ገልጾ ነበር። ታዲያ ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል? እንዴታ! ከተማዋ፣ በዙሪያዋ ያሉትን አካባቢዎች ጨምሮ 518 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ከመሆኑ አንጻር ወራሪዎቹ ከተማዋን ይጠቀሙባታል ተብሎ ቢታሰብም እነሱ ግን እንዲህ አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ ነነዌን ሙሉ በሙሉ አጠፏት። ታዲያ በነነዌ ላይ የደረሰውን ጥፋት በትክክል መተንበይ የሚችለው የትኛው የፖለቲካ ተንታኝ ነው?

የሰዎች አጥንት ይነድዳል፦

በአንድ መሠዊያ ላይ የሰዎችን አፅም የሚያቃጥል ሰው እንደሚነሳ ብሎም የዚህን ሰው ስምና የዘር ሐረግ እንዲሁም መሠዊያው የሚገኝበትን ከተማ ከ300 ዓመታት በፊት በትክክል ለመናገር የሚደፍር ማን ይኖራል? እንዲህ ያለ ለየት ያለ ትንቢት በትክክል ቢፈጸም ትንቢቱን የተናገረውን አካል ዝነኛ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም። አንድ የአምላክ ቃል አቀባይ ‘ኢዮስያስ የተባለ ሰው ለዳዊት ቤት እንደሚወለድ’ እና በቤቴል ከተማ በሚገኘው መሠዊያ ላይ ‘የሰዎችን አጥንት እንደሚያነድ’ ተናገረ። (1 ነገሥት 13:1, 2) ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ኢዮስያስ የተባለ ንጉሥ በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል መጣ፤ ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እምብዛም ያልተለመደ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ደግሞም ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢዮስያስ ‘አፅሞቹን ከየመቃብሩ አስወጣ’፤ ከዚያም ቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይ ‘አቃጠላቸው።’ (2 ነገሥት 23:14-16) አንድ ግለሰብ ከሰው በላይ በሆነ ኃይል ተመርቶ ካልሆነ በቀር እንዲህ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን እንዴት በትክክል መተንበይ ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ስለ ባቢሎን ውድቀት የተናገሩት ትንቢት አስገራሚ በሆነ መንገድ በትክክል ተፈጽሟል

የአንድ መንግሥት ውድቀት፦

የጦር ሠራዊት በማደራጀት አንድን ኃያል መንግሥት የሚገረስስ ሰው እንደሚነሳና የግለሰቡ ስም ማን እንደሆነ ሌላው ቀርቶ ስለሚጠቀምበት ያልተለመደ የጦር ስልት ግለሰቡ ከመወለዱ በፊት ትንቢት መናገር የሚችል ሰው ቢኖር በጣም አስገራሚ ይሆን ነበር! አምላክ ግን ቂሮስ የሚባል ሰው አንድን አገር ድል አድርጎ እንደሚይዝ አስታውቋል። በተጨማሪም ቂሮስ አይሁዳዊ ምርኮኞችን ነፃ እንደሚያወጣና ቤተ መቅደሳቸውን መልሰው እንዲገነቡ ድጋፍ እንደሚሰጥ አምላክ ተናግሯል። እንዲሁም የቂሮስ የጦር ስልት ወንዞችን ማድረቅን እንደሚያካትትና ከተማይቱን በቀላሉ መያዝ እንዲችል በሮቹ ክፍት ሆነው እንደሚጠብቁት ገልጿል። (ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:2) ታዲያ አምላክ በትንቢት የተናገራቸው እነዚህ በርካታ ዝርዝር ነገሮች በትክክል ተፈጽመዋል? ታሪክ ጸሐፊዎች ቂሮስ ከተማይቱን ድል አድርጎ መያዙ በትክክል የተፈጸመ ነገር እንደሆነ ይስማማሉ። የቂሮስ ሠራዊት ከባቢሎን ወንዞች መካከል የአንዱን አቅጣጫ የማስለወጥ አስገራሚ የምሕንድስና ብልሃት ስለተጠቀመ ወንዞቹ የደረቁ ያህል ሆነው ነበር። ከዚህም ሌላ ሠራዊቱ ክፍት በተተዉት በሮች በኩል ወደ ከተማዋ መግባት ችሎ ነበር። ከዚያ በኋላ ቂሮስ የአይሁድን ሕዝብ ነፃ በማውጣት በኢየሩሳሌም ያለውን ቤተ መቅደስ መልሰው መገንባት እንደሚችሉ አወጀ። ይህ አስገራሚ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ቂሮስ የአይሁድን አምላክ የሚያመልክ ሰው አልነበረም። (ዕዝራ 1:1-3) እነዚህን ዝርዝር ታሪካዊ ክስተቶች ከአምላክ በስተቀር ማን በትክክል ሊተነብይ ይችላል?

አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል መተንበይ እንደሚችል የሚያሳዩ ሦስት ምሳሌዎችን አይተናል። ይሁንና ፍጻሜያቸውን ያገኙት ትንቢቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። የአይሁዳውያን መሪ የነበረው ኢያሱ በፊቱ ለተሰበሰበው እጅግ ብዙ ሕዝብ እንዲህ በማለት እነሱ የሚያውቁትን አንድ ሐቅ ተናግሮ ነበር፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:1, 2, 14) ሕዝቡ አምላክ የተናገራቸው ተስፋዎችና ትንቢቶች በትክክል የተፈጸሙ መሆናቸውን ማስተባበል አይችሉም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ትንቢቶች በትክክል እንዲፈጸሙ የሚያደርገው እንዴት ነው? አምላክ የሚጠቀምበት መንገድ ከሰዎች በጣም የተለየ ነው። ይህን ማወቅህ ይጠቅምሃል፤ ምክንያቱም አምላክ አንተንም ጭምር የሚነኩ ታሪካዊ ክስተቶች በቅርቡ እንደሚከናወኑ ተናግሯል።

የአምላክ ትንቢቶች ከሰዎች ትንበያዎች ጋር ሲነጻጸሩ

ሰብዓዊ ትንበያዎች ብዙውን ጊዜ የተመሠረቱት በሳይንሳዊ ጥናት፣ ነባራዊ ሁኔታዎችንና አዝማሚያዎችን በመገምገም አልፎ ተርፎም ነቢይ ነን ባዮች በሚናገሩት ሐሳብ ላይ ነው። ሰዎች ትንበያዎችን ከተናገሩ በኋላ የሚሆነውን ነገር ቁጭ ብለው ከመጠበቅ በስተቀር ምንም ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም።—ምሳሌ 27:1

ከሰዎች በተቃራኒ አምላክ ሁሉንም እውነታዎች ያውቃል። የሰዎችን ተፈጥሮና ዝንባሌ ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመሆኑም ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ ግለሰቦችም ሆኑ ብሔራት በሙሉ ምን እርምጃ እንደሚወስዱ አስቀድሞ በትክክል ማወቅ ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ከዚህም በላይ ማድረግ ይችላል። እሱ የፈለገው ውጤት እንዲገኝ ለማድረግ ሲል ሁኔታዎችን መቆጣጠርና መለወጥ ይችላል። እንዲህ ብሏል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ . . . የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።” (ኢሳይያስ 55:11) ከዚህ አንጻር አንዳንዶቹ የአምላክ ትንቢቶች መፈጸማቸው እርግጠኛ ስለሆነ በአዋጅ ወይም በማስታወቂያ መልክ መቀመጣቸው አያስገርምም። አምላክ፣ የተናገራቸው ትንቢቶች እንዲፈጸሙ ማድረግ መቻሉ ምንጊዜም ቃሉ በትክክል እንደሚፈጸም ዋስትና ይሆናል።

የወደፊት ሕይወትህ

ታዲያ አምላክ የአንተንም ሆነ የቤተሰብህን የወደፊት ሕይወት የሚመለከት አስተማማኝ ትንቢት ተናግሯል? አንድ ከባድ አውሎ ነፋስ እየመጣ እንደሆነ አስቀድመህ ብታውቅ ሕይወትህን ለማዳን አንዳንድ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ጥርጥር የለውም። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትም ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት ትችላለህ። አምላክ በቅርቡ ዓለም አቀፍ የሆነ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግሯል። ( “አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ብሏል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይህ ጊዜ ባለሙያ ተብዬዎች ከሚተነብዩት ፈጽሞ የተለየ ነው።

ጉዳዩን በሚከተለው መንገድ ልታስበው ትችላለህ፦ የዓለም ሁኔታ በጥቅሉ ሲታይ የራሱ የሆነ አንድ ታሪክ አለው። የዚህ ታሪክ መደምደሚያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጻፈ ልናውቀው እንችላለን። አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው . . . ተናግሬአለሁ፤ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።” (ኢሳይያስ 46:10) የአንተም ሆነ የቤተሰብህ የወደፊት ሕይወት አስደሳች ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚል ማወቅ ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮችን ጠይቃቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ያላቸው አይደሉም፤ ወይም ከመንፈሳዊ ዓለም የሚመጡ ድምፆችን እንደሚሰሙ አሊያም ልዩ የመተንበይ ችሎታ እንዳላቸው አይናገሩም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን አምላክ ወደፊት ያዘጋጀልህን ጥሩ ነገሮች ሊነግሩህ ይችላሉ።