በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ወንጀለኞች በሚገደሉበት ጊዜ እግራቸው የሚሰበረው ለምን ነበር?

የመጽሐፍ ቅዱስ የወንጌል ዘገባ፣ በእንጨት ላይ የተሰቀሉት ኢየሱስና ሁለቱ ወንጀለኞች በተገደሉበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “አይሁዳውያን . . . አስከሬኖቹ በመከራ እንጨቶቹ ላይ ተሰቅለው እንዳይቆዩ ሲሉ እግራቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ጠየቁት” ይላል።—ዮሐንስ 19:31

የአይሁዳውያን ሕግ፣ ወንጀለኞች ከተገደሉ በኋላ በድናቸው ‘በእንጨት ላይ እንደተሰቀለ እንዳያድር’ ያዝዛል። (ዘዳግም 21:22, 23) ሮማውያን በሚሰቅሏቸው ሰዎች ላይም አይሁዳውያን ይህንኑ ሕግ ተግባራዊ ያደርጉ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ በሞተበት ቀን የሰዎቹ እግር መሰበሩ ሞታቸው እንዲፋጠንና ፀሐይ ጠልቃ ሰንበት ከመጀመሩ በፊት እንዲቀበሩ አስችሏል።

አንድ ሰው በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ከተፈረደበት አብዛኛውን ጊዜ እጆቹና እግሮቹ በእንጨት ላይ በምስማር ይቸነከራሉ። እንጨቱን ከተጋደመበት አንስተው ሲያቆሙት የግለሰቡ ክብደት በሙሉ በምስማሮቹ ላይ ስለሚያርፍ ከፍተኛ ሥቃይ ይሰማዋል። ግለሰቡ መተንፈስ እንዲችል እግሮቹን ወደ ታች በመግፋት ሰውነቱን መወጠር ይኖርበታል። የእግሮቹ አጥንቶች ከተሰበሩ ግን ይህን ማድረግ አይችልም። ግለሰቡ በዚህ ወቅት እግሮቹ ላይ በደረሰው ጉዳት የተነሳ ባይሞት እንኳ መተንፈስ ስለሚያቅተው ወዲያውኑ መሞቱ አይቀርም።

ወንጭፍ በጥንት ጊዜ ለጦርነት ጥቅም ላይ የዋለው እንዴት ነበር?

ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን የገደለው በወንጭፍ ተጠቅሞ ነበር። ዳዊት በወንጭፍ መጠቀምን የተማረው እረኛ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።—1 ሳሙኤል 17:40-50

አሦራውያን ወንጫፊዎች በአንድ የአይሁድ ከተማ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ የሚያሳይ ድንጋይ ላይ የተቀረጸ ምስል

ወንጭፍ በጥንቶቹ ግብፃውያንና አሦራውያን ሥነ ጥበብ ላይ ይታያል። ይህ መሣሪያ፣ መሃል ላይ ከቆዳ ወይም ከጨርቅ የተሠራ ማቀፊያ ያለው ሲሆን ማቀፊያው በሁለቱም አቅጣጫ ገመዶች አሉት። ወንጫፊው ከ5 እስከ 7.5 ሳንቲ ሜትር ዳያሜትር ያለውና 250 ግራም ያህል የሚመዝን ለስላሳ ወይም ድቡልቡል ድንጋይ በማቀፊያው ላይ ያስቀምጣል። ከዚያም ወንጭፉን ከአናቱ በላይ አሽከርክሮ አንዱን ገመድ ይለቀዋል፤ በዚህ ጊዜ ድንጋዩ ወደተፈለገበት አቅጣጫ በከፍተኛ ኃይል ይወነጨፋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ በተደረጉ ቁፋሮዎች በጥንት ዘመን በርካታ የወንጭፍ ድንጋዮች ተገኝተዋል። የሠለጠኑ ጦረኞች የሚያስወነጭፏቸው ድንጋዮች በሰዓት ከ160 እስከ 240 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ይጓዙ ነበር። ወንጭፍ አንድን ድንጋይ የሚያስወነጭፍበት ርቀት ቀስት ከሚያስፈነጥርበት ርቀት ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ምሁራን ስምምነት ላይ ባይደርሱም ወንጭፍም እንደ ቀስት ሰው ሊገድል ይችላል።—መሳፍንት 20:16