የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች የሚደርሱባቸው ለምንድን ነው?
ክፋትን ለማስወገድ አምላክ ምን እርምጃ ይወስዳል?
ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ያመጣውን መከራ ለማስወገድ ምን እርምጃ እንደሚወስዱ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይነግረናል። “የአምላክ ልጅ [ኢየሱስ] እንዲገለጥ የተደረገው ለዚህ ዓላማ ይኸውም የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:8) በስግብግብነት፣ በጥላቻና በክፉ ድርጊቶች ላይ የተመሠረተው አሁን ያለው ሥርዓት ይጠፋል። ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ‘ወደ ውጭ እንደሚጣል’ ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 12:31) ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከተወገደ በኋላ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚቋቋም ሲሆን ይህች ምድር ሰላማዊ ስፍራ ትሆናለች።—2 ጴጥሮስ 3:13
የክፋት ጎዳናቸውን ለመለወጥ እምቢተኛ በመሆን መጥፎ ነገሮችን ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ” የሚለውን በግልጽ የተቀመጠ ተስፋ ልብ በል። (ምሳሌ 2:21, 22) ክፉ ሰዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከዚያ በኋላ አይኖርም። እንዲህ ባለው ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከወረሱት ኃጢአት ቀስ በቀስ ነፃ ይወጣሉ።—ሮም 6:17, 18፤ 8:21
በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ አምላክ ክፋትን የሚያስወግደው እንዴት ነው? እሱ የሰጠንን የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ስጦታ ነጥቆ እንደ ሮቦት እንድንሆን በማድረግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን የእሱን መንገድ በማስተማር እንዲሁም ጎጂ አስተሳሰብና ድርጊቶችን እንዲያስወግዱ በመርዳት ነው።
አምላክ የመከራ መንስኤዎችን በሙሉ ያስወግዳል
ካልተጠበቁ አደጋዎች ጋር በተያያዘስ አምላክ ምን ያደርጋል? መንግሥቱ በቅርቡ ምድርን እንደሚያስተዳድር ቃል ገብቷል። አምላክ የሾመው የዚያ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን እሱም የታመሙትን የመፈወስ ኃይል አለው። (ማቴዎስ 14:14) በተጨማሪም ኢየሱስ የተፈጥሮን ኃይሎች የመቆጣጠር ችሎታ አለው። (ማርቆስ 4:35-41) በመሆኑም “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” የሚያስከትሉት መከራ ከዚያ በኋላ አይኖርም። (መክብብ 9:11 NW) በክርስቶስ አገዛዝ ሥር በሰው ዘር ላይ ምንም ዓይነት አደጋ አይደርስም።—ምሳሌ 1:33
በአሳዛኝ ሁኔታ የሞቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከማስነሳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 11:25) በእርግጥም፣ ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ወይም ወደ ሕይወት ለመመለስ የሚያስችል ኃይል አለው!
በጥሩ ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር ፈጽሞ የማይደርስበት ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸው ተስፋ የሚያጓጓህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ ዓላማው ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? በአካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን እውቀት እንድታገኝ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።