ሥራህን አጥተሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ጠቃሚ ሐሳቦች ታገኛለህ?
ሥራ ማጣት የሚጎዳው ኪስህን ብቻ አይደለም፤ በቤተሰብ ሕይወትህ እንዲሁም በስሜታዊና በአእምሯዊ ደህንነትህ ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ምን ሊረዳህ ይችላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚገኙ ጊዜ የማያልፍባቸው መመሪያዎች ላይ የተመሠረቱ ጠቃሚ ምክሮችን እናካፍልህ።
ስሜትህን ለሌሎች ተናገር።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።”—ምሳሌ 17:17
ሥራ ማጣት የተለያዩ ስሜቶች ሊፈጥር ይችላል፤ እንድታዝን፣ እንድትበሳጭ፣ ግራ እንድትጋባ ወይም ዋጋ ቢስ እንደሆንክ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ስሜትህን ለቤተሰቦችህ ወይም ለቅርብ ጓደኞችህ አውጥተህ ከተናገርክ ሊያጽናኑህና ሊያበረታቱህ ይችላሉ። ምናልባትም በሁለት እግርህ እንድትቆም የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦች ያካፍሉሃል።
ከልክ በላይ አትጨነቅ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት።”—ማቴዎስ 6:34
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ነገ ዕቅድ እንድናወጣ ያበረታታናል። (ምሳሌ 21:5) ነገር ግን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለብንም ይመክራል። ብዙውን ጊዜ የምንጨነቅባቸው ነገሮች ፈጽሞ አይከሰቱም። እንግዲያው ከዛሬ አልፈን ስለ ነገ መጨነቅ ትርጉም የለውም።
መጽሐፍ ቅዱስ ውጥረት ሲሰማህ ቀለል እንዲልህ የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮች ይዟል። “ውጥረትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ማንበብ ትችላለህ።
የገንዘብ አወጣጥህ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:12
አሁን ያለህበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ማስተካከያ አድርግ። ለምሳሌ የገንዘብ አወጣጥህን ካላስተካከልክ እንደ አቅምህ መኖር አትችልም። አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥም አትግባ።—ምሳሌ 22:7
ያለህን ገንዘብ አብቃቅተህ ለመኖር የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦች ማግኘት ከፈለግህ “በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
ጊዜህን በጥበብ ተጠቀም።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ በመጠቀም . . . በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 4:5
አሁን ሥራ ስለሌለህ ‘በዚህ ሰዓት ግባ፣ በዚህ ሰዓት ውጣ’ የሚልህ አይኖር ይሆናል፤ ሆኖም ነገሮችን የምታከናውንበት ጥሩ ፕሮግራም ማውጣትህ አስፈላጊ ነው። ይህም ሕይወትህ የዘፈቀደ እንዳይሆን ያደርጋል፤ ለራስህ ያለህ አክብሮትም አይቀንስም።
አዳዲስ ሁኔታዎችን ለመላመድ ፈቃደኛ ሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:23
ቀደም ሲል ሠርተኸው የማታውቀውን ሥራ ለመሞከር ፈቃደኛ ሁን። ሥራው ያን ያህል ትልቅ ቦታ የማይሰጠው ቢመስልህ ወይም ከቀድሞው ያነሰ ደሞዝ የሚያስገኝልህ ቢሆንም እንኳ አይሆነኝም ብለህ ለመደምደም አትቸኩል።
ፍለጋህን አታቋርጥ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በማለዳ ዘርህን ዝራ፤ እስከ ምሽትም ድረስ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ የትኛው እንደሚያድግ . . . አታውቅምና።”—መክብብ 11:6
ሥራ መፈለግህን አታቁም። ሥራ እየፈለግህ እንዳለ ብዙ ሰዎች እንዲያውቁ አድርግ። ለምሳሌ ለዘመዶችህ፣ ለምታውቃቸው ሰዎች፣ ለቀድሞ የሥራ ባልደረቦችህና ለጎረቤቶችህ ንገራቸው። ሥራ የሚያስቀጥሩ ድርጅቶችን አነጋግር፤ የሥራ ማስታወቂያዎችን ተከታተል፤ እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች ድረ ገጽ ላይ ገብተህ ክፍት የሥራ ቦታ ይኖር እንደሆነ እይ። ሥራ ለማግኘት ብዙ ቃለ መጠይቆች ማድረግና ብዙ ቦታዎች የሥራ ማመልከቻ ማስገባት ሊያስፈልግህ ይችላል፤ ለዚህ አእምሮህን አዘጋጅ።