ነቅታችሁ ጠብቁ!
አውዳሚ ጎርፎች—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች አውዳሚ በሆኑ ጎርፎች ምክንያት ለችግር ተዳርገዋል። እስቲ የሚከተሉትን ሪፖርቶች ተመልከት፦
“በቻይና ዋና ከተማ ባለፉት ጥቂት ቀናት ማለትም ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ ባለው ጊዜ ውስጥ 744.8 ሚሊ ሜትር የደረሰ ኃይለኛ ዝናብ ጥሏል፤ . . . ባለፉት 140 ዓመታት ገደማ ውስጥ እንዲህ ያለ ከባድ ዝናብ ተመዝግቦ አያውቅም።”—ኤፒ ኒውስ፣ ነሐሴ 2, 2023
“ካኑን የተባለው አውሎ ነፋስ በደቡባዊ ጃፓን ከባድ ዝናብና ኃይለኛ ነፋስ ማስከተል ከጀመረ ዛሬ ሐሙስ ሁለተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፤ ቢያንስ ሁለት ሰዎች በዚህ የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል። . . . አውሎ ነፋሱ በማዕከላዊ ታይዋን ተራራማ አካባቢዎች እስከ 0.6 ሜትር የሚደርስ ዝናብ ያስከትላል ተብሎ ይጠበቃል።”—ዶቼ ቬሌ፣ ነሐሴ 3, 2023
“ባለፈው ቅዳሜና እሁድ [በኖቫ ስኮሻ] የጣለው ከባድ ጎርፍ ያስከተለ ዝናብ፣ በአትላንቲክ ዳርቻ ባሉት የካናዳ አካባቢዎች በ50 ዓመታት ውስጥ ከተመዘገበው ዝናብ ከፍተኛው ነው።”—ቢቢሲ ኒውስ፣ ሐምሌ 24, 2023
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ስላሉት ክስተቶች ምን ይላል?
‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ምልክት
መጽሐፍ ቅዱስ አሁን የምንኖረው ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በመባል በሚታወቅ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይጠቁማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ኢየሱስ በዘመናችን “የሚያስፈሩ ነገሮች” ወይም የሚያስደነግጡ ክስተቶች እንደሚኖሩ በትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) አስፈሪ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ይበልጥ ተደጋጋሚና ከባድ እንዲሁም ያልተጠበቁ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ነው።
የተሻለ ጊዜ ይመጣል
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ከሆነ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ እየተከሰቱ ያሉትን አስፈሪ ነገሮች ስናይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ተስፋችን ሊለመልም ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች ሁኑ።”—ሉቃስ 21:31፤ ማቴዎስ 24:3
አሁን እያየናቸው ያሉት ክስተቶች፣ የአምላክ መንግሥት የውኃ ዑደትን ጨምሮ የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች በሙሉ በቅርቡ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውል ይጠቁማሉ።—ኢዮብ 36:27, 28፤ መዝሙር 107:29
የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚያድሳት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “ምድርን የሚታደጋት ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።