በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?

እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?

 እውነቱን ከሐሰት መለየት ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም ከባድ እየሆነ እንደመጣ ይሰማሃል? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ከእውነታው ይልቅ በስሜት ወይም ራሳቸው በሚያምኑበት ነገር ለመመራት የመረጡ ይመስላል። ይህን ሁኔታ ለመግለጽ ተብሎ የተፈጠረው “ድህረ-እውነት (post-truth)” የሚለው ቃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ይህን ያሳያል። a ይህ ቃል ብዙዎች ‘እውነት የሚባል ነገር የለም’ ብለው የሚያምኑበትን የዛሬውን ጊዜ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።

 ይህ አመለካከት አዲስ አይደለም። ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስን በምጸት ጠይቆታል። (ዮሐንስ 18:38) ጲላጦስ፣ ኢየሱስ መልስ እስኪሰጠው ባይጠብቅም ያነሳው ጥያቄ ግን በጣም ወሳኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አጥጋቢ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች ግራ በተጋቡበት በዚህ ዓለም ውስጥ እውነቱን ከሐሰት መለየት እንድትችል ይረዳሃል።

በእርግጥ እውነት የሚባል ነገር አለ?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነት” የሚለውን ቃል ግልጽ በሆነ ማስረጃ የተደገፈን እንዲሁም ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክል የሆነን ነገር ለማመልከት ይጠቀምበታል። የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ b አምላክ የፍጹም እውነት ምንጭ እንደሆነ ያስተምራል፤ እንዲያውም “የእውነት አምላክ” በማለት ይጠራዋል። (መዝሙር 31:5) በተጨማሪም ቃሉ ከአምላክ የተገኘውን እውነት የያዘ ሲሆን ይህን እውነት ከብርሃን ጋር ያመሳስለዋል፤ ምክንያቱም ይህ እውነት፣ በዚህ ግራ የተጋባ ዓለም ውስጥ መንገድ ይመራናል።—መዝሙር 43:3፤ ዮሐንስ 17:17

እውነትን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

 አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት በጭፍን እንድንቀበል አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በስሜት ተመርተን ሳይሆን የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን እውነትን እንድንመረምር ግብዣ አቅርቦልናል። (ሮም 12:1) ‘ሙሉ አእምሯችንን’ ተጠቅመን እንድናውቀውና እንድንወደው ይፈልጋል፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ የምንማረው ነገር እውነት መሆኑን እንድናረጋግጥ ያበረታታናል።—ማቴዎስ 22:37, 38፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11

ውሸት የመጣው ከየት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል፤ የአምላክ ቃል ሰይጣንን “የውሸት አባት” በማለት ይጠራዋል። (ዮሐንስ 8:44) ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች አምላክን በተመለከተ ውሸት ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 3:1-6, 13, 17-19፤ 5:5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስለ አምላክ ውሸት ማናፈሱንና እውነቱን መደበቁን ቀጥሏል።—ራእይ 12:9

በዛሬው ጊዜ ውሸት እንዲህ የተስፋፋው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት በሚጠራው በዘመናችን፣ ሰይጣን ከምንጊዜውም ይበልጥ በዓለም ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ሰዎችን እያሳሳተ ይገኛል። ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማስተላለፍ ሌሎችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሃይማኖቶችም በውሸት የተሞሉ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለንበትን ጊዜ በተመለከተ አስቀድሞ እንደተናገረው፣ ሰዎች ‘ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው በዙሪያቸው አስተማሪዎችን በመሰብሰብ እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ለመመለስ’ መርጠዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

እውነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

 በሰዎች መካከል መተማመን እንዲኖር ዋናው መሠረት እውነት ነው። መተማመን ከሌለ ወዳጅነትም ሆነ ጠንካራ ማኅበረሰብ ሊኖር አይችልም። አምላክ፣ አምልኳችን በእውነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲህ ይላል፦ “[አምላክን የሚያመልኩ] በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።” (ዮሐንስ 4:24) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ለመለየትና ከዚያ ነፃ ለመውጣት የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች” በሚል ርዕስ የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

አምላክ እውነትን እንዳውቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

 አምላክ እንድትድን ይፈልጋል፤ ለመዳን ደግሞ ስለ እሱ እውነቱን ማወቅ ያስፈልግሃል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) አምላክ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣውን መሥፈርት ከተማርክና በዚያ ከተመራህ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ። (መዝሙር 15:1, 2) አምላክ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ለመርዳት ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ሲሆን ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች እንድንሰማ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 17:5፤ ዮሐንስ 18:37

አምላክ ውሸትን የሚያስወግድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

 አዎ። አምላክ፣ ሰዎች ሌሎችን በማታለል መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ሲያይ ያዝናል። በውሸት ጎዳና መመላለሳቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሁሉ ከምድር ገጽ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 5:6) በዚያን ጊዜ፣ አምላክ “እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ” በማለት የሰጠው ተስፋም ይፈጸማል።—ምሳሌ 12:19

a “ድህረ-እውነት (post-truth)” የሚለው ቃል በ2016 የዓመቱ ቃል እንዲሆን በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ተመርጧል።

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።