ሰኔ 20, 2024
ሩሲያ
ሪናት ኪራሞቭ በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ ለአራት ቀናት ጥቃት ተፈጸመበት
ወንድም ሪናት ኪራሞቭ ሚያዝያ 2023 የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶበት ማረሚያ ቤት ይገኛል። ፍርድ ከተላለፈበት ከአንድ ዓመት በኋላ ሚያዝያ 18, 2024 የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት በአቅራቢያው ወዳለ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ማረሚያ ቤት አዘዋወሩት። ባለሥልጣናቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደዚህ ቦታ ያዘዋወሩት በሳንባ ነቀርሳ ስለጠረጠሩት እንደሆነ ገልጸዋል። ሪናት ከተዘዋወረ ከሁለት ቀናት በኋላ የተወሰኑ እስረኞች ምርመራ ያደርጉበት ጀመር። በመኖሪያ ከተማው በአክቱቢንስክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከት መረጃ እንዲሰጣቸው አስገደዱት። ሪናት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ያሠቃዩት ጀመር። በቀጣዮቹ አራት ቀናት፣ የኤሌክትሪክ ንዘረት በሚፈጥር መሣሪያ ሳይቀር የተለያዩ ጥቃቶች ፈጽመውበታል። በዚህ ላይ ደግሞ በእነዚህ ቀናት እንዲተኛ፣ እንዲቀመጥ ወይም ሰውነቱን እንዲታጠብ አልፈቀዱለትም፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ቆሞ እንዲያሳልፍ አደረጉ። በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳይበላም ከለከሉት።
ጥቃቱ መፈጸም ከጀመረ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የሪናት ባለቤት ጋሊና ልትጠይቀው መጣች። ሪናት ፊቱ እንደበለዘ፣ መራመድ እንዳቃተውና እጆቹ እንደሚንቀጠቀጡ ስታይ ደነገጠች። ሪናት ስለ ሁኔታው ካስረዳት በኋላ ጋሊና ጉዳዩን ለጠበቃው አሳወቀችው፤ ጠበቃውም ወዲያውኑ ሪናት የደረሰበት ጉዳት በሕክምና እንዲመረመር እንዲሁም ጉዳዩ እንዲጣራ አቤቱታ አቀረበ።
የአቃቤ ሕግ ቢሮ ሪፖርቱ እንደደረሰው ሪናትን የጎበኘው ሲሆን የሕክምና ምርመራ እንዲደረግለትም ዝግጅት አደረገ። ጥቃት እንደተፈጸመበት በምርመራ ሲረጋገጥ ጉዳዩ ወደ አገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ተላለፈ። በተጨማሪም ሪናት ሳንባ ነቀርሳ እንደሌለበት በመረጋገጡ ግንቦት 17, 2024 ቀድሞ ወደነበረበት ማረሚያ ቤት እንዲመለስ ተደርጓል፤ አሁንም እዚያው ይገኛል።
ሪናት ለመጽናት የረዳው ምን እንደሆነ ለጋሊና እንዲህ ብሏታል፦ “ማድረግ የምችለው ነገር ቢኖር መጸለይና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስታወስ መሞከር ነው። ማንም እንዲህ እንዳላደርግ ሊከለክለኝ አይችልም። ይህ ነገር ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ብዙ ጥቅሶችን ማስታወስ የቻልኩት ለዚህ ነው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ላመኑበት ምክንያት ሲሉ የጭካኔ ድርጊት የተጋፈጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ይህን ሲያደርጉ ግን የይሖዋ መንፈስ እገዛ አልነበራቸውም። እኔ ግን ገደብ የለሽ የሆነው የይሖዋ ኃይል ብርታት ሆኖኛል። ራሴን እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘ለይሖዋ ያለኝን ታማኝነት ለማስመሥከር የሚያስችል እንዲህ የመሰለ አጋጣሚ ኖሮኝ አያውቅም። ተስፋ አልቆርጥም።’”
ሪናት የደረሰበት ኢሰብዓዊ ድርጊት ቢረብሸንም ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችለንን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” እንደሚሰጠን ማወቃችን ያጽናናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7