ጥቅምት 15, 2024
ብራዚል
የብራዚል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የታካሚዎችን የሕክምና ምርጫ የማድረግ መብት አስከበረ
ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን በሚመለከቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አስተላልፏል
መስከረም 25, 2024 የብራዚል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉልህ ውሳኔ አስተላልፏል፤ ይህ ውሳኔ ለአካለ መጠን የደረሱ ታካሚዎች ደም ያለመውሰድ እንዲሁም ደም የማይጠይቅ ሕክምና የመምረጥ መብት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት የጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በግል ወይም በሃይማኖት ምክንያት ደም መውሰድ ለማይፈልጉ ታካሚዎች ያለደም ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።
ይህ ውሳኔ ሊተላለፍ የቻለው በብራዚል ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮችን የፍርድ ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ነው። እህት ማልቪና ሲልቫ በ2018 የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ነበራት፤ ለሕክምና ደም እንዲሰጣት ፈቃደኛ መሆኗን በሚናገር ሰነድ ላይ እንድትፈርም ተጠየቀች። እህት ማልቪና ፈቃደኛ አለመሆኗን ስትገልጽ ሆስፒታሉ ቀዶ ሕክምናውን ሰረዘው። እህት ማልቪና ከአቋሟ ጋር የሚስማማ ሕክምና ማግኘት የቻለችው ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ጥረት ከተደረገ በኋላ ነው።
ወንድም ሔሊ ዴ ሶዛ በ2014 የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ነበረው። ሆኖም እሱ ባለበት አካባቢ የነበረው ሐኪም ቤት ያለደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የሚያስችል መሣሪያ አልነበረውም። ሔሊ ከእምነቱ ጋር የሚስማማ ሕክምና ሊያገኝ ወደሚችልበትና ሊያስተናግደው ፈቃደኛ ወደሆነ ሌላ ሐኪም ቤት እንዲዘዋወር ጥያቄ አቀረበ፤ ሆኖም የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ቢሮው ጥያቄውን ውድቅ አደረገው። ሔሊ እስካሁን ቀዶ ጥገና ለማድረግ እየተጠባበቀ ይገኛል። በብራዚል ያሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸዋል፤ ያለፈቃዳቸው ደም የተሰጣቸው ጊዜም አለ።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዳኛ ሉዊ ሮቤርቶ ባሮሶ ውሳኔውን ባሳወቁበት ጊዜ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “በሃይማኖት ምክንያት ደም ያለመውሰድ መብት በሕገ መንግሥቱ የሰብዓዊ ክብርና የሃይማኖት ነፃነት መርሕ ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም ሕይወትንና ጤናን በተመለከተ [የይሖዋ ምሥክሮች] አማራጭ ሕክምናዎችን የማግኘት [እንዲሁም] ደም መውሰድን የሚጠይቁ ሕክምናዎችን ላለመቀበል በግላቸው የመወሰን መብት አላቸው።”
ይህ አዲስ ውሳኔ በመላው ብራዚል ያሉ ፍርድ ቤቶች የታካሚዎችን የመምረጥ መብት እንዲያከብሩ ያስገድዳል። ውሳኔው እንደ አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ጃፓን ባሉ አገሮች ውስጥ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ካስተላለፏቸው ውሳኔዎች ጋር የሚመሳሰል ነው። እንዲሁም መስከረም 17, 2024 የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት ካስተላለፈውና የታካሚዎችን የመምረጥ መብት ማክበርን በ46 የአውሮፓ አገራት ውስጥ አስገዳጅ ካደረገው ውሳኔ ጋር አብሮ ይሄዳል።
የብራዚል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሁሉም ዜጎች የግል እምነትና የሕክምና ምርጫ እንዲከበር የሚያደርግ ውሳኔ በማሳለፉ አመስጋኞች ነን።