ጥር 22, 2021
ቱርክሜኒስታን
ወንድም ኢህሎስቤክ ሮዝሜቶቭ በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናው ስላልፈቀደለት ለሁለተኛ ጊዜ ተፈረደበት
የፍርድ ውሳኔ
የቱርክሜኒስታን ፍትሐ ብሔር ፍርድ ቤት ጥር 19, 2021 ወንድም ኢህሎስቤክ ሮዝሜቶቭ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። ወንድም ኢህሎስቤክ በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናው ስላልፈቀደለት ብቻ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመት እንዲታሰር ተፈርዶበታል። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ በመሆኑ ምክንያት እንዲታሰር ሲፈረድበት ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
አጭር መግለጫ
ኢህሎስቤክ ሮዝሜቶቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1997 (አንዳሊብ)
ግለ ታሪክ፦ ሁለት ወንድሞች አሉት። ቤተሰቡን ለመደገፍ ሲል ከትምህርት ሰዓት በኋላ ሥራ መሥራት የጀመረው ገና በአሥር ዓመቱ ነው። ስፖርት፣ መጽሐፍ ማንበብና ሙዚቃ መስማት ይወዳል። እናቱ በ2010 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ እሱም ከአንድ ዓመት በኋላ ማጥናት ጀመረ
የክሱ ሂደት
ሐምሌ 11, 2018 ኢህሎስቤክ ሮዝሜቶቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በሴይዲ የጉልበት ሥራ ካምፕ ለአንድ ዓመት እንዲታሰር ተፈረደበት፤ በወቅቱ 20 ዓመቱ ነበር። የአንድ ዓመት የእስር ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ ተፈታ። በቱርክሜኒስታን ሕግ መሠረት አንድ ሰው በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ ለሁለተኛ ጊዜ ሊከሰስ ይችላል።
ኅዳር 25, 2020 ኢህሎስቤክ ለወታደራዊ አገልግሎት በድጋሚ ተጠራ። እሱም ክርስቲያናዊ አቋሙን በአክብሮት አስረዳ። ሆኖም ባለሥልጣናቱ የወንጀል ክስ መሠረቱበት። በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተከሰሰው ለሁለተኛ ጊዜ ስለሆነ ረዘም ያለ እስር ተፈረደበት።
ኢህሎስቤክ የመጀመሪያው የእስር ቆይታው “በጣም ከባድ” እንደነበር ገልጿል። ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳው እስር ቤት ከመግባቱ በፊት ያነበባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በቃሉ መያዙ ነው። ኢህሎስቤክ በተለይ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ ማሰላሰሉ በጣም እንደጠቀመው ገልጿል። ጥቅሱ ‘ስለ ምንም ነገር እንዳይጨነቅ፣’ ‘የአምላክን ሰላም’ ለማግኘት እንዲጸልይ እንዲሁም አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመው እንዲረጋጋ ረድቶታል። ኢህሎስቤክ “በእነዚያ የፈተና ወቅቶች ወደ ይሖዋ አዘውትሬ እጸልይ ነበር፤ እሱም ካጠገቤ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” ብሏል።
ይሖዋ፣ ወንድም ኢህሎስቤክን ጨምሮ እሱን ተስፋ የሚያደርጉትን ሁሉ ማበርታቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 40:29-31