በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 11, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ነሐሴ 2024 በዓለም ዙሪያ ሰባት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

ነሐሴ 2024 በዓለም ዙሪያ ሰባት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

ኢቢንዳ

የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ካርሎስ ሆርቴላኦ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም እንዲሁም የዘፍጥረት፣ የሩት፣ የአስቴር እና የዮናስ መጻሕፍት በኢቢንዳ ቋንቋ መውጣታቸውን ነሐሴ 2, 2024 አብስሯል። ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በካቢንዳ፣ አንጎላ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው። በስብሰባው ላይ 953 ሰዎች ተገኝተዋል። ተሰብሳቢዎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲሁም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተተረጎሙት ክፍሎች jw.org እና JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ስለተለቀቁ ማውረድ ተችሏል።

አንጎላ ውስጥ ከ716,000 በላይ ኢቢንዳ ተናጋሪዎች ይኖራሉ። በኢቢንዳ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። በአገሪቱ ባሉት በኢቢንዳ ቋንቋ የሚመሩ 13 ጉባኤዎችና አንድ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉት 335 ወንድሞችና እህቶች የአምላክን ቃል በገዛ ቋንቋቸው በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።

የዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኤነርጂ ማታንዳ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን ነሐሴ 9, 2024 አብስሯል። መጽሐፉ መውጣቱ የተገለጸው በሐራሬ፣ ዚምባብዌ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በአጠቃላይ 405 ተሰብሳቢዎች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል። መጽሐፉ እንደወጣ jw.org እና JW ላይብረሪ የምልክት ቋንቋ አፕሊኬሽን ላይም ተለቅቋል።

የማቴዎስ ወንጌል በ2021 በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ወጥቶ ነበር። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተጨማሪ መጻሕፍት በየጊዜው ሲወጡ ቆይተዋል። አንድ ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ እንደሚጠቀሙ ይገመታል፤ ከእነዚህም መካከል ዚምባብዌ ባሉ 11 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 11 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉት 377 ወንድሞችና እህቶች ይገኙበታል።

ቡልጋሪያኛ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ከተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌሎች በቡልጋሪያኛ መውጣታቸውን ነሐሴ 11, 2024 አብስሯል፤ የእነዚህ መጻሕፍት መውጣት የተነገረው በሶፊያ፣ ቡልጋሪያ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 ልዩ የክልል ስብሰባ የመደምደሚያ ንግግር ላይ ነው። በፕሮግራሙ ላይ 5,418 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። ሦስቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ወዲያውኑ jw.org እና JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ተለቅቀዋል።

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቡልጋሪያኛ መጀመሪያ የወጣው በ2009 ነው። በአሁኑ ወቅት ቡልጋሪያ በሚገኙት 57 ጉባኤዎች ውስጥ 3,000 ገደማ ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ።

አያ

የምዕራብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ቦይስ ሲልቬይን የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በአያ ቋንቋ መውጣታቸውን ነሐሴ 16, 2024 አብስሯል፤ ማስታወቂያው የተነገረው በጃኩቶሜይ፣ ቤኒን በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ለተገኙት 631 ተሰብሳቢዎች ነው። በአቡሜይ ከለቪ፣ ቤኒን የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ የተገኙ ሌሎች 435 ተሰብሳቢዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። ሁለቱም መጻሕፍት jw.org እና JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ስለተለቀቁ ማውረድ ተችሏል።

በቤኒን እና በቶጎ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአያ ቋንቋ ይናገራሉ። በዚህ ቋንቋ የተዘጋጁ ሌሎች ሁለት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉሞች አሉ። ሆኖም እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት መረዳት ለአብዛኞቹ አንባቢዎች አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ትርጉሞች፣ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም አውጥተውታል። በአሁኑ ወቅት በቤኒን በአያ ቋንቋ የሚመሩ 25 ጉባኤዎችና አንድ ቡድን፣ በቶጎ ደግሞ 12 ጉባኤዎችና 2 ቡድኖች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ውስጥ በአጠቃላይ ወደ 1,300 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ። መለኮታዊውን ስም በተገቢው ቦታ መልሶ ያስገባና ለመረዳት የማይከብድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው ሁሉም በጣም ተደስተዋል።

ኪንያርዋንዳ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ዊንደር የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኪንያርዋንዳ ቋንቋ መውጣቱን ነሐሴ 16, 2024 አብስሯል። ወንድም ዊንደር ይህን ምሥራች የተናገረው በኪጋሊ፣ ሩዋንዳ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው። በፕሮግራሙ ላይ 9,908 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። የክልል ስብሰባ በተካሄደባቸው ሌሎች ሁለት ቦታዎች የተገኙ 1,141 ተሰብሳቢዎችም ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በሁሉም ቦታዎች የነበሩት ተሰብሳቢዎች የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። በኪንያርዋንዳ የተዘጋጀው የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም የኤሌክትሮኒክ ቅጂ እንዲሁም የድምፅ ቅጂ jw.org እና JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ተለቅቋል።

ሩዋንዳ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ኪንያርዋንዳ ተናጋሪዎች ይኖራሉ። ኪንያርዋንዳ እንደ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ባሉት አገራትም ይነገራል። ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኪንያርዋንዳ መጀመሪያ የወጣው በ2010 ነበር። በአሁኑ ወቅት በመላው ሩዋንዳ በሚገኙት 634 የኪንያርዋንዳ ጉባኤዎች ውስጥ ከ35,500 በላይ ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ።

ሲንሃላ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሲንሃላ ቋንቋ መውጣቱን ነሐሴ 16, 2024 አብስሯል፤ ይህ ምሥራች የተነገረው በኮሎምቦ፣ ስሪ ላንካ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተሰኘው የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ 4,273 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በቺሎው፣ ስሪ ላንካ በተካሄደ የክልል ስብሰባ ላይ የተገኙት 1,045 ተሰብሳቢዎችም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በሁለቱም ቦታዎች የነበሩት ተሰብሳቢዎች በሲንሃላ ቋንቋ የታተመው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። የኤሌክትሮኒክ ቅጂውንም ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ሲንሃላ ቋንቋ መተርጎም ከጀመሩ 75 ዓመታት አልፈዋል። በአሁኑ ወቅት በስሪ ላንካ ከ15 ሚሊዮን የሚበልጡ ሲንሃላ ተናጋሪዎች የሚኖሩ ሲሆን ይህ ቁጥር በአገሪቱ ባሉት 62 የሲንሃላ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉትን 4,808 ወንድሞችና እህቶችም ያካትታል።

ዋሊስኛ

የኒው ካሊዶኒያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማርቲን ዴኩዙ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በዋሊስኛ መውጣቱን ነሐሴ 30, 2024 አብስሯል፤ ይህ የምሥራች የተነገረው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ በተባለው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። ስብሰባው የተካሄደው በኒው ካሊዶኒያ በምትገኘው በኖመያ ከተማ እንዲሁም በዋሊስ እና ፉቱና በሚገኘው በማላኤ መንደር ነው። በሁለቱ ቦታዎች የተካሄዱት ስብሰባዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተገናኝተው ነበር። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት 317 ተሰብሳቢዎች በሙሉ የአዲስ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ የተሰጣቸው ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱን ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዋሊስኛ የወጣው በ2018 ነበር። በኒው ካሊዶኒያ እንዲሁም በዋሊስ እና ፉቱና ባሉት ሁለት ጉባኤዎች ውስጥ 153 ዋሊስኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም ተጠቅመው በእነዚህ ደሴቶች ለሚኖሩት ከ35,000 በላይ ዋሊስኛ ተናጋሪዎች ምሥራቹን ለማብሰር ጓጉተዋል።