በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 6, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ2023 የፊፋ የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያን ለማየት ለመጡ ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል

የ2023 የፊፋ የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያን ለማየት ለመጡ ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል

ከሐምሌ 20 እስከ ነሐሴ 20, 2023 ባሉት ቀናት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በአውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ ባሉ የተለያዩ ከተሞች በተካሄደው የፊፋ የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ላይ ታድመዋል። ግጥሚያው በተካሄደባቸው ቀናት፣ በሁለቱ አገሮች ባሉ ዘጠኝ ከተሞች ውስጥ ልዩ የስብከት እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን 1,200 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በስብከት እንቅስቃሴው ተካፍለዋል። ቢያንስ 18 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ጠይቀዋል።

በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ሁለት ከሕንድ የመጡ ወጣት ሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በነፃ እንደምንሰጥ የሚገልጽ ምልክት የተለጠፈበት ጋሪ ተመለከቱ። ከዚያም ይህን ትምህርት መከታተል የሚችሉት የት እንደሆነ እህቶችን ጠየቁ። እህቶችም እንዲህ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በአብዛኛው የሚሰጠው በግለሰብ ደረጃ እንደሆነ ነገሯቸው። በተጨማሪም ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር ላይ ያለውን ኮድ በማስነበብ መጽሐፍ ቅዱስን በግል የሚያስተምራቸው ሰው እንዲመደብላቸው መጠየቅ እንደሚችሉ ገለጹላቸው። ሁለቱም ወዲያውኑ ኢንተርኔት ላይ ያለውን ፎርም ሞሉ፤ ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።

በብሪዝበን፣ አውስትራሊያ ያሉ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት መንገድ የጠፋባት የምትመስልን አንዲት ወጣት እርዳታ ያስፈልጋት እንደሆነ ጠየቋት። ይህች ወጣት ሆቴሏን ለማግኘት እንደተቸገረች ነገረቻቸው። ባልና ሚስቱም በደግነት ሊረዷት ተስማሙ። ሆቴሉን ለመፈለግ እየሄዱ ሳለ፣ ወጣቷ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ እንደመጣች ነገረቻቸው። ባልና ሚስቱም ከዚህ በፊት ፓፑዋ ጊኒ ይኖሩ እንደነበር ሲነግሯት ደስ አላት። ይህም ጥሩ ጭውውት እንዲያደርጉ በር የከፈተ ሲሆን በኋላም አድራሻ ተለዋወጡ። ሌላ ጊዜ ላይ ባልና ሚስቱ ለወጣቷ ከተማውን ሊያስጎበኟት ቀጠሮ ያዙ፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመውም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነገሯት። ወጣቷ ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች።

በኦክላንድ፣ ኒው ዚላንድ ያለች ቴሪና የተባለች እህት መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ጠባቂ ሆነው ከሚሠሩ ፑንጃብኛ ተናጋሪ ከሆኑ ሁለት ሰዎች ጋር ውይይት ጀመረች። ሌላ ጠባቂ ውይይታቸውን አቋርጦ ከሁለቱ ወንዶች ጋር በፑንጃብኛ ማውራት ጀመረ። እህታችን ሰውየው በሥራ ሰዓት ሲያወሩ ስላገኛቸው እየተቆጣቸው ያለ መስሏት ነበር። ሰውየው ግን እያስተረጎመላቸው እንደሆነ ሲነግራት ተገረመች። በተጨማሪም ሰውየው እህትን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሆነ ሲጠይቁኝ አምላክ የሰጠን መጽሐፍ እንደሆነ ነገርኳቸው። ልክ ነኝ?” አላት። እህት ልክ እንደሆነ ከነገረችው በኋላ jw.org​ን ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው ለማጥናት መጠየቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለእያንዳንዳቸው አሳየቻቸው።

ከኮሎምቢያ የመጣ ኒኮላስ የሚባል ሰው በብሪዝበን፣ አውስትራሊያ የጽሑፍ ጋሪው ወዳለበት ሄዶ ስለ ስብሰባዎቻችን ጠየቀ። እናቱና አያቶቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑና በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ እንደሚያበረታቱት ተናገረ። ጋሪው ጋ የቆሙት ወንድሞች በስፓንኛ ጉባኤ ያለ አንድ ወንድም እንዲያነጋግረው ዝግጅት አደረጉ። ከአንድ ሰዓት በኋላ ስፓንኛ የሚናገር ወንድም፣ ኒኮላስ ጋ ደወለለትና በዚያው ሳምንት መጨረሻ በሚካሄደው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተባለው የክልል ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ቀጠሮ ያዙ።

በአውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህ ዝግጅት ላይ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ‘እንደ ብርሃን አብሪዎች ለማብራት’ የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስተኞች ነን።—ፊልጵስዩስ 2:15