የካቲት 1, 2024
ደቡብ አፍሪካ
በዙሉ ቋንቋ ለ75 ዓመታት የይሖዋን መንግሥት ማስታወቅ
መጠበቂያ ግንብ በዙሉ ቋንቋ መታተም ከጀመረ 75ተኛ ዓመቱን ጥር 2024 አስቆጥሯል። የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ መጠበቂያ ግንብን በዙሉ ቋንቋ ማዘጋጀት የጀመረው በ1949 ነው፤ ሕትመቱ የሚከናወነውም በእጅ በሚሠራ ማባዣ ማሽን ነበር። ከጊዜ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው ይበልጥ ዘመናዊ ማተሚያ ማሽን ያገኘ ሲሆን ይህም ጽሑፎችን በተሻለ ጥራት እና በብዛት ለማተም አስችሏል።
መጀመሪያ አካባቢ ፈታኝ የነበረው ነገር፣ ለዙሉ ትርጉም ቡድን ተስማሚ መኖሪያ ማግኘት ነበር። በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ሕግ፣ ጥቁሮችና ነጮች በአንድ ሕንፃ ውስጥ አብረው እንዳይኖሩ ይከለክል ነበር። ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው የዙሉ ተርጓሚዎች ከቤቴል ውጭ ለመኖር ተገድደው ነበር። ይህም በጉዞ ጊዜ እንዲባክንና ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይፈጥር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ የሆስቴል ክፍል ውስጥ 20 ተርጓሚዎች የኖሩበት ጊዜ አለ። ከ1981 ጀምሮ በዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ለሁለት ዓመት ከኖሩት ወንድሞች አንዱ ወንድም አልፍሬድ ፓትጽዋና ነው። አሁን የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ነው፤ ያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “በሆስቴሉ ውስጥ የነበረው ሁኔታ አመቺ ያልነበረባቸው ጊዜያት ነበሩ። ያም ቢሆን የትርጉም ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለን ማረፊያ ማግኘት በመቻላችን ደስተኞች ነበርን። በተጨማሪም የመኖሪያ ቦታችንን በንጽሕና ለመያዝ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን ብዙ ጊዜ ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል።”
ደስ የሚለው በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ምቹ የርቀት የትርጉም ቢሮ አብረው ሥራቸውን ማከናወንና መኖር ችለዋል። በአሁኑ ወቅት በዙሉ ቋንቋ በሚመሩ 584 ጉባኤዎች ውስጥ ያሉት ከ28,000 በላይ አስፋፊዎች መጠበቂያ ግንብን እና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቋንቋቸው ማግኘት ችለዋል።
መጠበቂያ ግንብን እና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ዙሉ የመተርጎሙን ሥራ ይሖዋ መባረኩን በመቀጠሉ ደስተኞች ነን፤ ይህ የትርጉም ሥራ ብዙዎች “የሕይወትን ውኃ በነፃ [እንዲወስዱ]” አጋጣሚ ከፍቷል።—ራእይ 22:17