ንድፍ አውጪ አለው?
የሊምፔት ጥርስ
ሊምፔት ባሕር ውስጥ የሚኖር ባለሾጣጣ ቅርጽ ዛጎል ያለው ቀንድ አውጣ ሲሆን በጣም ጠንካራ የሆነ ጥርስ አለው። ጥርሶቹ የተሠሩት ጎኢታይት ከሚባል ጠንካራ ማዕድንና ለስላሳ ከሆነ ፕሮቲን ነው። ቀጭን የሆኑትና ጥቅጥቅ ብለው የተቀመጡት የማዕድኑ ጭረቶች በፕሮቲኑ ተሸፍነዋል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የተቆለመመ ቅርጽ ያላቸው የሊምፔት ጥርሶች ምላስ መሰል በሆነው የአካል ክፍሉ ላይ ተደርድረዋል፤ እያንዳንዱ ጥርስ ቁመቱ ከአንድ ሚሊ ሜትር አይበልጥም። ሊምፔቱ ጥርሶቹን ለመፈቅፈቂያነት ይጠቀምባቸዋል። ሊምፔቱ የሚመገበውን አልጌ ከድንጋይ ላይ ፍቆ ማንሳት እንዲችል እያንዳንዱ ጥርስ በጣም ጠንካራ መሆን አለበት።
ተመራማሪዎች የተራቀቀ አጉሊ መነጽር በመጠቀም የሊምፔት ጥርስ ሳይሰበር ምን ያህል ጫና መቋቋም እንደሚችል ለማስላት ሞክረው ነበር። ተመራማሪዎቹ የሊምፔት ጥርስ የሸረሪት ድርን ጨምሮ እስካሁን ጥናት ከተደረገባቸው በተፈጥሮ የሚገኙ ቁሶች በሙሉ የላቀ ጥንካሬ እንዳለው አስተውለዋል። ምርምሩን ይመሩ የነበሩት ሳይንቲስት “እኛም ተመሳሳይ ንድፍ በመጠቀም አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት መሞከር አለብን” ብለዋል።
ተመራማሪዎች የሊምፔት ጥርስ ያለውን ንድፍ በመኮረጅ መኪና፣ ጀልባና አውሮፕላን አልፎ ተርፎም ሰው ሠራሽ ጥርስ መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሊምፔት ጥርስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?