ንድፍ አውጪ አለው?
ሴሎች ወደተለያየ የአካል ክፍል የሚያድጉበት መንገድ
በተጸነስክበት ወቅት በዓይን እንኳ የማይታይ አንድ ደቃቅ ሴል ነበርክ፤ ይህ ሴል ዛይጎት ተብሎ ይጠራል። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ሁሉም የአካል ክፍል ያለው ሕፃን ሆነህ ተወለድክ። ያ አንድ ሴል ተባዝቶ የተለያየ ቅርጽ፣ መጠንና አገልግሎት ያላቸውን ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ የሴል ዓይነቶች አስገኝቷል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድ ዛይጎት የDNAውን ግልባጭ ካዘጋጀ በኋላ ለሁለት ይከፈላል። ከዚያም አዲሶቹ ሴሎች ይህንኑ ሂደት ብዙ ጊዜ ይደጋግሙታል። መጀመሪያ ላይ ሁሉም አዳዲስ ሴሎች አንድ ዓይነት ናቸው። በውስጣቸው ያለው DNA ሁሉንም የሴል ዓይነቶች ለመሥራት የሚያስችል መመሪያ ይዟል።
ከተጸነስን ከአንድ ሳምንት በኋላ ሴሎቹ ወደ ሁለት ቡድኖች ይከፈላሉ። አንዳንዶቹ ሴሎች የጽንሱ አካል ክፍል ይሆናሉ፤ ሌሎቹ ሴሎች ደግሞ እንግዴ ልጅ እንዲሁም ጽንሱ እንዲያድግ የሚረዱ ሌሎች ሕብረ ሕዋሳት ይሆናሉ።
ሦስተኛው ሳምንት ላይ፣ የጽንሱ የአካል ክፍል የሚሆኑት ሴሎች ወደ ሦስት የተነባበሩ ቡድኖች ይከፈላሉ። በውጭ በኩል ያሉት ሴሎች በጊዜ ሂደት ነርቭ፣ አንጎል፣ አፍ፣ ቆዳና ሌሎች ሴሎች ይሆናሉ። መካከል ላይ ያሉት ሴሎች ደም፣ አጥንት፣ ኩላሊት፣ ጡንቻና ሌሎች ሕብረ ሕዋሳት ይሆናሉ። በውስጥ በኩል ያሉት ሴሎች ደግሞ ሳንባ፣ ፊኛ፣ የምግብ መፍጫ አካላት እና ሌሎች ውስጣዊ የአካል ክፍሎችን ይሠራሉ።
በእርግዝና ወቅት አንዳንዶቹ ሴሎች በተናጠልም ሆነ በቡድን ከጽንሱ አንድ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል ይጓዛሉ። ሌሎች ሴሎች ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ንጣፍ መሰል ነገር ይሠራሉ ወይም ታጥፈው ቱቦ መሰል ነገር ይፈጥራሉ። ይህ ሂደት ለየት ያለ ቅንጅት ይጠይቃል። ለምሳሌ በንጣፍ መልክ የተደራጁት ሴሎች ተጠቅልለው ትናንሽ ቱቦዎችን ይሠራሉ። በጽንሱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ይህ ሂደት በተመሳሳይ ጊዜ ይከናወናል። ከዚያም ቱቦዎቹ መርዘምና ቅርንጫፍ ማውጣት ይጀምራሉ፤ በስተ መጨረሻም ቱቦዎቹ ተቀጣጥለው የተሟላ የደም ዝውውር መስመር ይሠራሉ።
አንድ ጤናማ ሕፃን በሚወለድበት ወቅት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴሎቹ በተገቢው ቦታና ጊዜ በአግባቡ ተደራጅተው አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ይሆናሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሴሎች ያላቸው ወደተለያየ የአካል ክፍል የመለወጥ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?