የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ምሳሌ 17:17—“ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው”
“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17 አዲስ ዓለም ትርጉም
“ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።”—ምሳሌ 17:17 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የምሳሌ 17:17 ትርጉም
እውነተኛ ወዳጆች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። እርስ በርስ እንደሚቀራረቡ ወንድማማቾች በተለይ በችግር ጊዜ አንዳቸው ለሌላው ታማኝነትና አሳቢነት ያሳያሉ።
“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።” ይህ አገላለጽ “ጓደኛሞች ሁሌም ፍቅራቸውን ያሳያሉ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እዚህ ላይ የገባው “ፍቅር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው ለአንድ ሰው የሚኖረንን ስሜት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በተግባር ጭምር የሚገለጽን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያመለክታል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-7) እንዲህ ባለ ፍቅር የተሳሰሩ ወዳጆች፣ በአለመግባባት ወይም በሕይወት ውጣ ውረዶች የተነሳ ወዳጅነታቸው በሚፈተንበት ጊዜም እንኳ እንደተቀራረቡ ይቀጥላሉ። በተጨማሪም በነፃ ይቅር ይባባላሉ። (ምሳሌ 10:12) ጥሩ ወዳጅ፣ በጓደኛው ስኬት አይቀናም። ይልቁንም ከጓደኛው ጋር አብሮ ይደሰታል።—ሮም 12:15
“እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” ይህ አገላለጽ በወንድማማቾች መካከል ያለውን ልዩ ቅርርብ እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። ስለዚህ ችግር ያጋጠመውን የቅርብ ወዳጃችንን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ ስናደርግ ለዚያ ግለሰብ እንደ እውነተኛ ወንድም ወይም እህት እንሆንለታለን ማለት ነው። በተጨማሪም እንዲህ ባሉ ጓደኛሞች መካከል ያለው ትስስር በፈተናዎች አይላላም። እንዲያውም አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እየጨመረ ስለሚሄድ ቅርርባቸው ይበልጥ ይጠናከራል።
የምሳሌ 17:17 አውድ
የምሳሌ መጽሐፍ፣ አንባቢዎቹ ቆም ብለው እንዲያስቡ በሚያደርጉ ቅልብጭ ያሉ አባባሎች አማካኝነት ጥልቅ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን ይሰጣል። የዚህን መጽሐፍ አብዛኛውን ክፍል የጻፈው ንጉሥ ሰለሞን ነው። የተጻፈው በዕብራይስጥ የግጥም አጻጻፍ ስልት ሲሆን ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ ንጽጽሮችን ይጠቀማል። በዚህ የአጻጻፍ ዘይቤ የስንኞቹ የመጨረሻ ቃላት ቤት አይመቱም። ከዚህ ይልቅ ወጥ የሆነ ምት ያላቸው ስንኞች አንዱን ሐሳብ የሚቃረን ወይም የሚደግፍ ሐሳብ ያስተላልፋሉ። ተመሳሳይ ንጽጽርን የሚጠቀም የግጥም አጻጻፍ ስልት የምናገኝበት አንዱ ቦታ ምሳሌ 17:17 ነው፤ የዚህ ጥቅስ ሁለተኛ ክፍል የመጀመሪያውን ክፍል የሚያጠናክር ሐሳብ ይዟል። ምሳሌ 18:24 ደግሞ የሚቃረኑ ሐሳቦች በንጽጽር የቀረቡበት ጥቅስ ነው። ጥቅሱ “እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች አሉ፤ ነገር ግን ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ” ይላል።
ሰለሞን ምሳሌ 17:17ን ሲጽፍ በአባቱ በዳዊትና የንጉሥ ሳኦል ልጅ በሆነው በዮናታን መካከል የነበረውን የጠበቀ ወዳጅነት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙኤል 13:16፤ 18:1፤ 19:1-3፤ 20:30-34, 41, 42፤ 23:16-18) ዳዊትና ዮናታን የሥጋ ዝምድና ባይኖራቸውም ከወንድማማቾች ይበልጥ ይቀራረቡ ነበር። ዮናታን ከእሱ በዕድሜ ብዙ ለሚያንሰው ወዳጁ ሲል ሕይወቱን ጭምር አደጋ ላይ ጥሏል። a
የምሳሌ 17:17 ሌሎች አተረጓጎሞች
“ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል።”—የ1954 ትርጉም
“ወዳጆች ዘወትር ፍቅራቸውን ያሳያሉ፤ ወንድማማቾች በችግር ጊዜ ካልተረዳዱ፥ የወንድማማችነታቸው ጥቅም ምንድን ነው?”—የ1980 ትርጉም
“ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወዳል፤ በመከራ ጊዜ ግን ወንድም ይወለዳል።”—የ1879 ትርጉም
የምሳሌ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a “የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።