የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ኢሳይያስ 41:10—“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ”
“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:10 አዲስ ዓለም ትርጉም
“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:10 የ1954 ትርጉም
የኢሳይያስ 41:10 ትርጉም
ይሖዋ a አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥማቸው እንደሚደግፋቸው ዋስትና ሰጥቷል።
“እኔ ከአንተ ጋር ነኝ።” ይሖዋ አገልጋዮቹ መፍራት የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ነግሯቸዋል፦ ብቻቸውን አይደሉም። እሱ ያሉበትን ሁኔታ ይመለከታል እንዲሁም ጸሎታቸውን ይሰማል፤ በመሆኑም ልክ ከጎናቸው ያለ ያህል ነው።—መዝሙር 34:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:12
“እኔ አምላክህ ነኝ።” ይሖዋ ሕዝቡን አሁንም ቢሆን አምላካቸው እንደሆነና እነሱም አገልጋዮቹ እንደሆኑ በመግለጽ አረጋግቷቸዋል። አምላክ ለእነሱ ሲል እርምጃ እንዳይወስድ ሊያግደው የሚችል ምንም ዓይነት ሁኔታ እንደሌለ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 118:6፤ ሮም 8:32፤ ዕብራውያን 13:6
“አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።” ይሖዋ ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ሦስት አገላለጾችን በመጠቀም አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ሕዝቡ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው የሚወስደውን እርምጃ በዓይነ ሕሊና ለመሣል የሚያስችል ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። አንድ ሰው ከወደቀ አምላክ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ያነሳዋል።—ኢሳይያስ 41:13
አምላክ አገልጋዮቹን የሚያበረታታበትና የሚደግፍበት ዋነኛው መንገድ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ኢያሱ 1:8፤ ዕብራውያን 4:12) ለምሳሌ የአምላክ ቃል እንደ ድህነት፣ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ሰዎች ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 2:6, 7) በተጨማሪም አምላክ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ስሜታዊና አእምሯዊ ጥንካሬ ለአገልጋዮቹ ለመስጠት መንፈስ ቅዱሱን ይጠቀማል።—ኢሳይያስ 40:29፤ ሉቃስ 11:13
የኢሳይያስ 41:10 አውድ
በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከጊዜ በኋላ በግዞት ወደ ባቢሎን የተወሰዱትን ታማኝ አይሁዳውያን አጽናንቷቸዋል። በግዞት ዘመናቸው ማብቂያ አካባቢ በባቢሎን ዙሪያ ባሉ ብሔራት ላይ ጥፋት የሚያመጣና ባቢሎንን ስጋት ላይ የሚጥል ድል አድራጊ እንደሚመጣ የሚገልጹ ወሬዎች እንደሚናፈሱ ይሖዋ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 41:2-4፤ 44:1-4) ይህ ዜና ባቢሎንንና በዙሪያዋ ያሉትን ብሔራት የሚያሸብር ቢሆንም አይሁዳውያኑ ግን በዚህ ሊጨነቁ አይገባም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ከአንዴም ሦስት ጊዜ ‘አትፍሩ’ በማለት አበረታቷቸዋል።—ኢሳይያስ 41:5, 6, 10, 13, 14
ይሖዋ አምላክ በኢሳይያስ 41:10 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው በባቢሎን በግዞት ለነበሩት ታማኝ አይሁዳውያን ቢሆንም ሁሉም አገልጋዮቹ ከዚህ ጥቅስ ማጽናኛ እንዲያገኙ ሲል በቃሉ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቀመጥ አድርጓል። (ኢሳይያስ 40:8፤ ሮም 15:4) በጥንት ጊዜ የነበሩ አገልጋዮቹን እንደረዳቸው ሁሉ ዛሬ ያሉ አገልጋዮቹንም ይረዳቸዋል።
ኢሳይያስ ምዕራፍ 41ን አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18