በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ፎቶዎችን ከማውጣቴ በፊት የትኞቹን ጉዳዮች ማወቅ ይኖርብኛል?

ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ፎቶዎችን ከማውጣቴ በፊት የትኞቹን ጉዳዮች ማወቅ ይኖርብኛል?

 አስደሳች የእረፍት ጊዜ እያሳለፍሽ ነው፤ ይህንን ጓደኞችሽም እንዲያውቁልሽ ፈልገሻል። ግን እንዴት ብታሳውቂያቸው ይሻላል?

  1.  (ሀ) ለጓደኞችሽ በሙሉ ደብዳቤ መጻፍ

  2.  (ለ) ለሁሉም ጓደኞችሽ ኢ-ሜይል መጻፍ

  3.  (ሐ) ፎቶዎችሽን ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ማውጣት

 አያቶችሽ በአንቺ ዕድሜ ላይ እያሉ የነበራቸው ብቸኛ ምርጫ “ሀ” ነበር።

 ወላጆችሽ በአንቺ ዕድሜ እያሉ ምርጫ “ለ” እንኳ አልነበራቸው ይሆናል።

 በዛሬው ጊዜ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ፎቶግራፋቸውን ማውጣት የሚችሉ በርካታ ወጣቶች ግን ምርጫቸው “ሐ” ነው። የአንቺም ምርጫ ተመሳሳይ ነው? ከሆነ ይህ ርዕስ አንዳንድ ስህተቶችን ከመሥራት እንድትቆጠቢ ይረዳሻል።

 ምን ጥቅሞች አሉት?

 ፈጣን ነው። “በጣም አስደሳች ጉዞ ሳደርግ አሊያም ከጓደኞቼ ጋር በጣም ጥሩ ጊዜ ሳሳልፍ እዚያው እንዳለሁ ፎቶዎቼን ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ማውጣት እችላለሁ።”—ሜላኒ

 አመቺ ነው። “ጓደኞቼ ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ኢ-ሜይል ከመጻጻፍ ይልቅ በየጊዜው የሚያወጧቸውን ፎቶዎች መመልከት ይበልጥ ቀላል ነው።”—ጆርዳን

 ከጓደኞችሽ ጋር እንዳትራራቂ ይረዳሻል። “አንዳንድ ጓደኞቼና የቤተሰቦቼ አባላት የሚኖሩት እኔ ካለሁበት ርቀው ነው። በየጊዜው ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚያወጧቸውን ፎቶዎች መከታተሌ እነሱን በየቀኑ የማግኘት ያህል ሆኖልኛል!”—ካረን

 ምን አደጋዎች አሉት?

 ደህንነትሽ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ካሜራሽ ፎቶ የተነሳሽበትን ቦታ የሚጠቁም ቴክኖሎጂ ወይም ጂኦታጊንግ የሚጠቀም ከሆነ ካሰብሽው በላይ ብዙ መረጃ ልታስተላልፊ ትችያለሽ። ዲጂታል ትሬንድስ የተባለው ድረ ገጽ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል፦ “ጂኦታጊንግ ያላቸውን ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚያስቀምጥ ሰው፣ ይህን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው መጥፎ ዓላማቸውን ለማሳካት ለሚፈልጉ ሰዎች ሊጋለጥ ይችላል።”

 እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ወንጀለኞች ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉት የማትገኚበትን ቦታ ነው። ዲጂታል ትሬንድስ የተባለው ድረ ገጽ በአንድ ወቅት ሦስት ዘራፊዎች ማንም ሰው ወደሌለባቸው 18 ቤቶች በመግባት ዝርፊያ እንደፈጸሙ ዘግቧል። ዘራፊዎቹ ቤቶቹ ውስጥ ማንም ሰው እንደሌለ ማወቅ የቻሉት እንዴት ነው? ሳይበርኬዚንግ የተባለ ዘዴ በመጠቀም የቤቱን ባለቤቶች እንቅስቃሴ በማጥናት ነው፤ በዚህም ምክንያት ከ100,000 ዶላር በላይ የሚገመት ንብረት ዘርፈዋል።

 ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድታዪ ሊያደርግሽ ይችላል። አንዳንዶች ኅፍረት የሚባል ነገር ስለሌላቸው ሰው ሁሉ ሊያየው በሚችል ቦታ ማንኛውንም ነገር ያወጣሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “አደጋው የሚመጣው የማታውቋቸውን ሰዎች አካውንት መመልከት ስትጀምሩ ነው። ሁኔታው በማታውቁት ከተማ ውስጥ ያለካርታ ከመጓዝ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የማትፈልጉት ቦታ የመሄድ አጋጣሚያችሁ በጣም ሰፊ ነው።”

 ጊዜሽን ይሻማብሻል። ዮላንዳ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሳታውቁት፣ ሌሎች ሰዎች ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያወጧቸውን አዳዲስ ፎቶዎችና እያንዳንዱ ሰው የሰጠውን ሐሳብ በማንበብ ብዙ ጊዜ ልታጠፉ ትችላላችሁ። ይባስ ብሎ ደግሞ አዲስ ነገር እንዳለ ለማየት ስልካችሁን አሁንም አሁንም እስከ ማየት ልትደርሱ ትችላላችሁ።”

ፎቶዎችን የምታስቀምጡበት አካውንት ካላችሁ ራሱን መቆጣጠር የሚችል ሰው መሆን አለባችሁ

 ሳማንታ የተባለች ወጣት በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ድረ ገጾችን በመቃኘት በማሳልፈው ጊዜ ላይ ገደብ ማድረግ አስፈልጎኛል። ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ፎቶዎችን የምታስቀምጡበት አካውንት ካላችሁ ራሱን መቆጣጠር የሚችል ሰው መሆን አለባችሁ።”

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

  •   ተገቢ ያልሆነ ነገር ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርጊ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዓይኖቼ ፊት የማይረባ ነገር አላኖርም” የሚል ሐሳብ ይዟል።—መዝሙር 101:3

     “በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚያወጧቸውን ነገሮች የምከታተላቸው ሰዎች ምን እንዳወጡ በንቃት እከታተላለሁ፤ የሚያወጡት ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ከተሰማኝ ከዚያ በኋላ የሚያወጧቸውን ነገሮች ማየት አቆማለሁ።”—ስቲቨን

  •   የምትመሪባቸውን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ያለሽን ግንኙነት አቋርጪ፤ ምክንያቱም አቋምሽን እንድታላዪ ሊያደርጉሽ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል” በማለት ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 15:33 የግርጌ ማስታወሻ

     “ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚወጡ አንዳንድ ፎቶዎችን ብዙዎች ስለወደዷቸው ብቻ አንቺም መውደድ እንዳለብሽ አይሰማሽ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ፎቶዎችን የያዙ የኢንተርኔት ገጾች ጸያፍ ንግግሮች፣ እርቃንን የሚያሳዩ ምስሎችን እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ነገሮችን ያቀርባሉ።”—ጄሲካ

  •   ለምን ያህል ጊዜ ኢንተርኔት እንደምትጠቀሚና ፎቶዎችን የምታወጪው በየስንት ጊዜ ሊሆን እንደሚገባ ገደብ አብጂ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:15, 16

     “ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ‘በጣም ብዙ ፎቶዎችን ከሚያወጡ’ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጣለሁ። ወደ ባሕር ዳርቻ ሄዶ በዚያ የተነሳቸውን 20 ተመሳሳይ ፎቶዎች ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚያወጣ ሰው እንዳለ ታምናላችሁ? እነዚህን ሁሉ ፎቶዎች መመልከት በጣም ብዙ ጊዜ ይወስዳል!”—ሬቤካ

  •   የምታወጪያቸው ፎቶዎች የሰዎች ትኩረት ወደ አንቺ ብቻ እንዲሳብ የሚያደርግ አለመሆኑን እርግጠኛ ሁኚ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት” በማለት ጽፏል። (ሮም 12:3) ጓደኞችሽ የአንቺን ፎቶዎችና የምታደርጊያቸውን እንቅስቃሴዎች የመከታተል ግዴታ እንዳለባቸው አድርገሽ አታስቢ።

     “አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ያነሱትን በጣም ብዙ ፎቶ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ይለጥፋሉ። አንድ ሰው ጓደኛዬ ከሆነ መልኩ አይጠፋኝም፤ እሱን ለማስታወስ ፎቶዎቹን ማየት አያስፈልገኝም።—አሊሰን