የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳልጠቀም ቢከለክሉኝስ?
ጓደኞችህ ሁሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ይጠቀማሉ፤ ደግሞም ሁልጊዜ የሚያወሩት ስለ እሱ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ አንተ ተጠቃሚ ባለመሆንህ ያሾፉብሃል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብሃል? ምን እርምጃስ ልትወስድ ትችላለህ?
ልታውቀው የሚገባ ነገር
አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ይከለክላሉ። ምናልባት እንዲህ የሚያደርጉት ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም የተለያዩ መዘዞችን እንደሚያመጣ ስለተገነዘቡ ይሆናል፤ ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
የመንፈስ ጭንቀትና ሌሎች የአእምሮ ጤና እክሎችን ሊያስከትል ይችላል።
ለፖርኖግራፊ፣ ለሴክስቲንግ እና በኢንተርኔት አማካኝነት ለሚሰነዘር ጥቃት ሊያጋልጥ ይችላል።
በጓደኞች መካከል አላስፈላጊ አለመግባባት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
ብዙ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀማቸውን ለማቆም መርጠዋል። እነዚህ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በመገንዘብ በራሳቸው ይህን ውሳኔ አድርገዋል። እስቲ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ወጣቶች ሁኔታ ተመልከት፦
ፕሪሲላ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀሟ ለተሻለ ዓላማ ልታውል የምትችለውን ጊዜ እየተሻማባት እንደሆነ ተገንዝባለች።
ጄረሚ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው የሚመጡትን መጥፎ ይዘት ያላቸው ነገሮች መቆጣጠር አለመቻሉ አላስደሰተውም።
ቤታኒ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀሟ ሌሎች ሰዎች ለሚያደርጉት ነገር ከልክ ያለፈ ትኩረት እንድትሰጥ እያደረጋት እንደሆነ አስተውላለች።
“ማኅበራዊ ሚዲያ የምቃኝበትን አፕሊኬሽን አጠፋሁት፤ እንዲህ በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በውሳኔዬ አልቆጭም፤ ደግሞም ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የማውለው ተጨማሪ ጊዜ ማግኘቴ አስደስቶኛል።”—ሲዬራ
“ማኅበራዊ ሚዲያ በጣም ሱስ የሚያስይዝ ነገር እንደሆነና ሰዎች ፖስት ለማደርጋቸው ነገሮች የሚሰጡት ምላሽ ከልክ በላይ እያሳሰበኝ እንደመጣ ተገነዘብኩ፤ ይህ ደግሞ አላስደሰተኝም። አካውንቴን ማጥፋት ከብዶኝ ነበር፤ ግን እንደዚያ ካደረግኩ በኋላ እፎይታ ተሰማኝ። አሁን ከቀድሞው የበለጠ ሰላም አግኝቻለሁ።”—ኬት
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ወላጆችህ ያወጡትን ሕግ ታዘዝ። ያወጧቸውን ሕጎች ሳትበሳጭ ወይም ሳታጉረመርም በመከተል ብስለትህን አሳያቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።”—ምሳሌ 29:11 የ1954 ትርጉም
አንዳንዶች ወላጆችህ ሳያውቁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንድትጠቀም ወይም የሚስጥር አካውንት እንድትከፍት ይመክሩህ ይሆናል። ይህ ስህተት ነው! እንዲህ ማድረግህ እንድትጨነቅና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። ወላጆችህ ጉዳዩን ከደረሱበት ደግሞ ለችግር ልትዳረግ ትችላለህ፤ እነሱም በአንተ ላይ ያላቸውን አመኔታ ማጣታቸው አይቀርም።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18
የራስህ ውሳኔ ይሁን። ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ወጣቶች አንተም ማኅበራዊ ሚዲያ ከመጠቀም እንድትቆጠብ ሊያደርጉህ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ለአንተ ጥሩ እንዳልሆነ ከተገነዘብክ ወላጆችህ ስላሉህ ብቻ ሳይሆን አንተ ራስህ አምነህበት ላለመጠቀም ውሳኔ አድርግ። ይህም እኩዮችህ ቢጠይቁህ እንኳ እንዳትሸማቀቅ ይረዳሃል፤ እኩዮችህም የራስህ ውሳኔ እንደሆነ ሲያውቁ አንተ ላይ ለማሾፍ ያን ያህል ላይነሳሱ ይችላሉ።
ዋናው ነጥብ፦ ወላጆችህ ያወጡትን ሕግ ታዘዝ፤ በተጨማሪም የእነሱ ውሳኔ የአንተም ውሳኔ እንዲሆን፣ የምትስማማባቸውን ነጥቦች ለማሰብ ሞክር። ቢያንስ ለጊዜው፣ ያለማኅበራዊ ሚዲያ መኖር ትችላለህ።