መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“በጣም ብዙ ጥያቄ ነበረኝ”
የትውልድ ዘመን፦ 1976
የትውልድ አገር፦ ሆንዱራስ
የኋላ ታሪክ፦ የቤተ ክርስቲያን ፓስተር የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ
የተወለድኩት በላ ሴባ፣ ሆንዱራስ ውስጥ ሲሆን ከአምስት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ፤ በቤታችን ውስጥ ብቸኛው ወንድ ልጅ እኔ ነበርኩ። በቤተሰባችን ውስጥ መስማት የማልችለውም እኔ ብቻ ነበርኩ። የምንኖረው በአደገኝነቱ በሚታወቅ ሰፈር ውስጥ ነበር፤ ደግሞም በጣም ድሆች ነበርን። አራት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ አባቴ በሥራ ቦታው ባጋጠመው አደጋ የተነሳ ሞተ፤ ያኔ ደግሞ የቤተሰባችን ችግር ይበልጥ ተባባሰ።
እናቴ እኔንና እህቶቼን ለመንከባከብ የቻለችውን ሁሉ ታደርግ ነበር፤ ሆኖም ለእኔ ልብስ ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ እንኳ አልነበራትም። የሚሞቅ ልብስ ስላልነበረኝ ዝናብ ሲዘንብ በጣም ይበርደኝ ነበር።
ዕድሜዬ ከፍ ሲል የሆንዱራስ ምልክት ቋንቋ ተማርኩ፤ ይህም መስማት ከተሳናቸው ሌሎች ሰዎች ጋር ለመግባባት አስችሎኛል። እናቴና እህቶቼ ግን ምልክት ቋንቋ ስለማይችሉ ከእኔ ጋር የሚነጋገሩት የራሳቸውን ምልክቶችና አንዳንድ አካላዊ መግለጫዎችን በመጠቀም ነበር። እናቴ በጣም ትወደኝ ነበር፤ እኔን ከአደጋ ለመጠበቅም ብዙ ጥረት ታደርግ ነበር። በምታውቃቸው ጥቂት ምልክቶች በመጠቀም እንደ ሲጋራና መጠጥ ካሉ ሱሶች እንድርቅ ታስጠነቅቀኝ ነበር። በውጤቱም በምንም ዓይነት ሱስ ሳልጠላለፍ ማደግ ችያለሁ።
ልጅ እያለሁ እናቴ ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትወስደኝ ነበር፤ ሆኖም ወደ ምልክት ቋንቋ የሚተረጉምልኝ ሰው ስላልነበረ የሚሰጠው ትምህርት አይገባኝም ነበር። በጣም ስለተሰላቸሁ አሥር ዓመት ሲሆነኝ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆምኩ። ያም ቢሆን ስለ አምላክ ማወቅ እፈልግ ነበር።
በ1999 የ23 ዓመት ወጣት ሳለሁ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አባል ከሆነች አንዲት ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣች ሴት ጋር ተዋወቅኩ። እሷም መጽሐፍ ቅዱስንና የአሜሪካ ምልክት ቋንቋን አስተማረችኝ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር በጣም ስለወደድኩት ፓስተር ለመሆን ወሰንኩ። ስለዚህ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የተዘጋጀ የክርስትና ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ፖርቶ ሪኮ ሄድኩ። በ2002 ወደ ላ ሴባ ከተመለስኩ በኋላ በአንዳንድ ጓደኞቼ እርዳታ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚሆን ቤተ ክርስቲያን አቋቋምኩ። ከእነዚህ ጓደኞቼ አንዷ ከሆነችው ከፓትሪሲያ ጋር ከጊዜ በኋላ ተጋባን።
የቤተ ክርስቲያኑ ፓስተር እንደመሆኔ መጠን መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በሆንዱራስ ምልክት ቋንቋ ስብከት አቀርብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በሥዕል አሳይ እንዲሁም ታሪኮቹን በተውኔት መልክ አቀርብ ነበር። ከዚህም ሌላ በጎረቤት ከተሞች ያሉትን መስማት የተሳናቸው ሰዎች እየሄድኩ አበረታታቸውና እረዳቸው ነበር። እንዲያውም ወደ ዩናይትድ ስቴትስና ወደ ዛምቢያ ሚስዮናዊ ጉዞ አድርጌ ነበር። እውነቱን ለመናገር ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም የማውቀው ነገር አልነበረም። የማስተምረው የተነገረኝንና ሥዕሎችን በማየት የተረዳሁትን ነገር ብቻ ነበር። በጣም ብዙ ጥያቄ ነበረኝ።
በአንድ ወቅት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ስለ እኔ የውሸት ወሬ ማሰራጨት ጀመሩ። ሰካራም እንደሆንኩና በሚስቴ ላይ እንዳመነዘርኩ አስወሩብኝ። ይህም በጣም አበሳጨኝ። ብዙም ሳይቆይ እኔና ፓትሪሲያ ቤተ ክርስቲያኑን ለቀቅን።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን በተደጋጋሚ ይመጡ የነበረ ቢሆንም እኔና ፓትሪሲያ አንቀበላቸውም ነበር። ቤተ ክርስቲያናችንን ከለቀቅን በኋላ ግን ፓትሪሲያ ቶማስና ሊክሲ ከተባሉ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። ቶማስና ሊክሲ መስማት የተሳናቸው ባይሆኑም የምልክት ቋንቋ መቻላቸው አስገረመኝ። ስለዚህ ብዙም ሳይቆይ እኔም አብሬያቸው ማጥናት ጀመርኩ።
በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን በመጠቀም ለተወሰኑ ወራት አጠናን። ሆኖም አንዳንድ ጓደኞቻችን የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ተከታዮች እንደሆኑ ሲነግሩን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታችንን አቆምን። ቶማስ የይሖዋ ምሥክሮች መሪ አድርገው የሚቆጥሩት ሰው እንደሌለ ለማሳየት ብዙ ማስረጃዎችን ቢያቀርብልኝም አላመንኩትም።
ከተወሰኑ ወራት በኋላ ፓትሪሲያ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተዋጠች፤ በዚህ ጊዜ አምላክ የይሖዋ ምሥክሮች በድጋሚ ወደ ቤታችን እንዲልክልን ጸለየች። ብዙም ሳይቆይ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት ጎረቤታችን ፓትሪሲያን ልትጠይቃት መጣችና ‘ሊክሲ መጥታ እንድትጠይቅሽ ልነግርልሽ እችላለሁ’ አለቻት። ሊክሲ ለፓትሪሲያ እውነተኛ ጓደኛ ሆናላታለች። በየሳምንቱ ፓትሪሲያን ልታበረታታትና መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናት ትመጣ ነበር። እኔ ግን አሁንም የይሖዋ ምሥክሮችን ሙሉ በሙሉ አላመንኳቸውም።
በ2012 የይሖዋ ምሥክሮች እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? ለተባለው ትራክት በሆንዱራስ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን ቪዲዮ ለማሳየት ልዩ ዘመቻ አካሂደው ነበር። ሊክሲ ይህን ቪዲዮ አመጣችልን። ቪዲዮውን ስመለከት ስለ ገሃነመ እሳትና ስለ ነፍስ አለመሞት የሚገልጹትን ትምህርቶች ጨምሮ አስተምራቸው የነበሩት ብዙዎቹ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኙ ተገነዘብኩ፤ በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጥኩ።
በቀጣዩ ሳምንት ቶማስን ለማነጋገር ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ሄድኩ። መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር እንደምፈልግ ሆኖም የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማልፈልግ ለቶማስ ነገርኩት። መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ብቻ የሚሆን አዲስ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ፈልጌ ነበር። ቶማስ እንዲህ ያለ ቅንዓት በማሳየቴ ካመሰገነኝ በኋላ ኤፌሶን 4:5ን አሳየኝ፤ ጥቅሱ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ አንድነት ሊኖረው እንደሚገባ ይገልጻል።
በተጨማሪም ቶማስ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት በተግባር የተደገፈ እምነት፣ ክፍል 1፦ ከጨለማ መውጣት የተባለውን ቪዲዮ በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ ሰጠኝ። ቪዲዮው የተወሰኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች በተመለከተ እውነቱን ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ እንደመረመሩ ያሳያል። ቪዲዮውን ስመለከት የእነዚያ ሰዎች ስሜት ገባኝ። እኔም እንደ እነሱ እውነትን እየፈለግኩ ነበር። ቪዲዮው የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩ አሳመነኝ፤ ምክንያቱም እምነታቸው ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በድጋሚ ማጥናት ጀመርኩ፤ ከዚያም በ2014 እኔና ፓትሪሲያ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።
ያገኘሁት ጥቅም
የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤ የምወደው በሥነ ምግባር ንጹሕ ስለሆነ ነው። አምላክ ንጹሕ እንደሆነ ሁሉ አምላኪዎቹም በንግግራቸውና ሌሎችን በሚይዙበት መንገድ ረገድ ንጹሖች ናቸው። የአምላክ ሕዝቦች ሰላማዊ ከመሆናቸውም ሌላ እርስ በርስ ይበረታታሉ። የይሖዋ ምሥክሮች አንድነት አላቸው፤ እንዲሁም በየትኛውም አገር ቢኖሩ ወይም የትኛውንም ቋንቋ ቢናገሩ የሚያስተምሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተመሳሳይ ነው።
ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በማወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለምሳሌ ይሖዋ ሉዓላዊና ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ተምሬያለሁ። እሱ መስማት የተሳናቸውንም ሆነ መስማት የሚችሉ ሰዎችን ይወዳል። አምላክ ላሳየኝ ፍቅር በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከዚህም ሌላ ምድር ውብ ገነት እንደምትሆንና ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ሆነን ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለን ተምሬያለሁ። ይህን ቀን በጉጉት እጠባበቃለሁ!
እኔና ፓትሪሲያ መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስተናል። በአሁኑ ወቅት በቀድሞው ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን። ሆኖም ፓስተር ከነበርኩበት ጊዜ በተለየ መልኩ አሁን ስለማስተምረው ነገር ጥያቄ የለኝም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቴ ለጥያቄዎቼ መልስ ማግኘት ችያለሁ።