መርከቦችን ለማየት የመጡ ነፃነት አፍቃሪ የሆኑ ሰዎች
ከሰኔ 6 እስከ 16, 2013 ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች በሰሜናዊ ፈረንሳይ ወደምትገኘው ወደ ኡወን ወደብ ይጎርፉ ነበር፤ ጎብኚዎቹ የመጡት በዓለማችን ላይ ከሚካሄዱት ሁሉ ትልቅና እጅግ ማራኪ የሆነውን የመርከቦች ስብስብ ትዕይንት (አርማዳ) ለማየት ነበር።
በዓለማችን ላይ አሉ የተባሉ ውብና ረጃጅም መርከቦች ማራኪ በሆነው የኖርማንዲ አካባቢ በሚገኘው በጠመዝማዛው የሴይን ወንዝ ላይ 120 ኪሎ ሜትር ሽቅብ እየቀዘፉ ሄዱ፤ ከዚያም ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለውና ለዚህ ልዩ ዝግጅት ተስማሚ በሆነው የወንዙ ዳርቻ ላይ መልሕቃቸውን ጣሉ። አሥር ቀናት በፈጀው በዚህ ዝግጅት ላይ ጎብኚዎቹ 45 የሚሆኑ ረጃጅምና ዝነኛ መርከቦች ውስጥ ገብተው በነፃነት የመጎብኘት ልዩ አጋጣሚ አግኝተው ነበር።
በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙት እነዚህ በርካታ ሰዎች ይህን ትዕይንት ለማየት እንዲመጡ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? የዝግጅቱ መሥራችና አዘጋጅ እንደገለጹት ከሆነ ይህ የመርከቦች ትዕይንት ጎብኚዎቹ “በምኞት ዓለም እንዲከንፉ የሚያደርጓቸውን እነዚያን ግዙፍ መርከቦች በቅርበት እንዲያዩ ያስችላቸዋል።” በእርግጥም ልጆችንና አዋቂዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በነፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱትን ትላልቅ መርከቦች ሲመለከቱ ሩቅ ስለ መጓዝና ስለ ነፃነት ማሰባቸው አይቀርም።
ከዚህም በተጨማሪ በሺህ የሚቆጠሩ አገር ጎብኚዎች ስለ ሌላ ዓይነት ነፃነት ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለሚያስገኘው ነፃነት የመስማት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። (ዮሐንስ 8:31, 32) ጎብኚዎቹ በመካከለኛው ዘመን የተገነባችውን ውቧን የኡወን ከተማ ሲጎበኙና በሰው በተጨናነቁ ጠባብ ጎዳናዎቿ ላይ ሲዘዋወሩ ዓይናቸው በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ባስቀመጧቸው ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያዎች ላይ ማረፉ አልቀረም። ጎብኚዎች ወይም መርከበኞች ወደ ጽሑፍ መደርደሪያዎቹ ሲቀርቡ ደስ ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ያለ ምንም ክፍያ እንዲወስዱ የይሖዋ ምሥክሮቹ ይጋብዟቸዋል። በተለይም “ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም ይመጣ ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የብዙ አላፊ አግዳሚዎችን ትኩረት ስቦ ነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮቹ በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ቋንቋ በሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ላይ እንዲገኙ ለጎብኚዎቹ ግብዣ ያቀርቡ ነበር።
የአካባቢው ነዋሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ላደረጉት ለዚህ ዝግጅት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያቸውን ይዘው በአደባባይ የቆሙትን የይሖዋ ምሥክሮች መመልከቱ ያስደነቀው አንድ ግለሰብ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “መንገድ ላይ ስላየኋችሁ ደስ ብሎኛል። እምነታችሁን ባልጋራም ለሚያምኑበት ነገር በጽናት ለሚቆሙ ሰዎች አክብሮት አለኝ።” ሁለት አረጋውያን ደግሞ እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ሲካፈል ያገኙትን አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር “በማንነትህ ልትኮራ ይገባል!” ብለውታል።