በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የ2014 ዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

የአምላክ መንግሥት 100ኛ ዓመት!

የ2014 ዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

ጥቅምት 4 ቀን 2014 የተደረገውን የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ 130ኛ ዓመታዊ ስብሰባ 19,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተከታትለውት ነበር። ስብሰባው የተካሄደው በጀርሲ ሲቲ፣ ኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ሲሆን በሌሎች በርካታ ቦታዎች ያሉ ሰዎችም ፕሮግራሙን በቪዲዮ በቀጥታ ተመልክተውታል።

የበላይ አካል አባል የሆነው ማርክ ሳንደርሰን የስብሰባው ሊቀ መንበር ነበር። ወንድም ሳንደርሰን በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ በዚህ ዓመት የሚደረገው ስብሰባ መሲሐዊው መንግሥት መግዛት በጀመረበት 100ኛ ዓመት ላይ የሚካሄድ በመሆኑ ታሪካዊ ስብሰባ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገለጸ።

ወንድም ሳንደርሰን፣ የአምላክ መንግሥት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውን ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ሦስት ነገሮች ጠቀሰ፦

  • ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ። የይሖዋ ሕዝቦች በእሱ እርዳታ በመታገዝ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ በትጋት ሲሠሩ ቆይተዋል። በ1914 በጥቂት ሺዎች ይቆጠሩ የነበሩት አስፋፊዎች በ2014 የአገልግሎት ዓመት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሆነዋል። ይሖዋ በቃ እስኪል ድረስ በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥላለን።

  • ለመንግሥቱ ተገዢዎች በቡድን ደረጃ ጥበቃ ማድረግ። የሃይማኖት መሪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከባድ ስደት ያደረሱብን ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሞከሩበት ጊዜም ነበር። ይሁንና ይሖዋ አገልጋዮቹን በቡድን ደረጃ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እና በሌሎች ቦታዎች ያገኘናቸው ሕጋዊ ድሎች ይሖዋ አሁንም ድረስ ጥበቃ እያደረገልን እንደሆነ ያሳያሉ።

  • የተለያየ አስተዳደግና ሁኔታ ያላቸው ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ። የአምላክ መንግሥት የተለያየ አስተዳደግ፣ ብሔር እና ቋንቋ ያላቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመው በአንድነት አምላክን እንዲያገለግሉ አስችሏል። ወንድም ሳንደርሰን “ይህ ይሖዋ አምላክ ብቻ ሊያከናውነው የሚችል ተአምር ነው” በማለት ተናገረ። አክሎም በዚህ ታሪካዊ የሆነ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ መገኘት ትልቅ ክብር እንደሆነ በድጋሚ ገለጸ።

“የይሖዋ ወዳጅ ሁን” የተባለው ተከታታይ ቪዲዮ።

በዓመታዊ ስብሰባው ላይ ቀጥሎ የቀረበው ፕሮግራም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ ሲወጣ የቆየውን የልጆች ቪዲዮ የሚመለከት ነበር። በመጀመሪያ ወንድም ሳንደርሰን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሕፃናት የሰጡትን አስተያየት የሚያሳይ ቪዲዮ እንዲመለከቱ አድማጮችን ጋበዘ። ሕፃናቱ ከእነዚህ ተከታታይ ቪዲዮዎች ስላገኙት ትምህርት ያላቸውን አድናቆት ከልብ በመነጨ ስሜት ሲገልጹ መስማት ልብ የሚነካ ነበር።

ከዚያም የእነዚህ ተከታታይ ቪዲዮዎች ቀጣይ ክፍል የሆነ አዲስ ቪዲዮ ቀረበ። ይህ ቪዲዮ “ይሖዋ ደፋር እንድትሆን ይረዳሃል” የሚል ርዕስ አለው። የ12 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ይህ ቪዲዮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችውን ለንዕማን ሚስት ስለ ይሖዋ በድፍረት የተናገረችውን እስራኤላዊት ልጅ ታሪክ መሠረት ያደረገ ነው። (2 ነገሥት 5:1-14) ይህ ቪዲዮ ሰኞ ጥቅምት 6, 2014 በ​jw.org ላይ የወጣ ሲሆን ከ20 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል።

ጄደብሊው ላንግዌጅ።

ወንድም ሳንደርሰን፣ ለኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚያገለግል አዲስ አፕሊኬሽን እንደወጣ ገለጸ፤ ይህ አፕሊኬሽን አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ አዲስ ቋንቋ የሚማሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። አፕሊኬሽኑ በ18 ቋንቋዎች ከ4,000 የሚበልጡ ቃላትንና ሐረጎችን የያዘ ነው። ተጨማሪ ቃላትንና ሐረጎችን፣ ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ መግቢያዎችን እንዲሁም ሌሎች ገጽታዎችን በአፕሊኬሽኑ ላይ ለማካተት ጥረት እየተደረገ ነው።

ጄደብሊው ብሮድካስት።

በኢንተርኔት አማካኝነት የሚተላለፍ አዲስ የይሖዋ ምሥክሮች የቴሌቪዥን ጣቢያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ የሙከራ ስርጭት መጀመሩ አድማጮችን በጣም ያስደሰተ ዜና ነበር። በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለው ዋና መሥሪያ ቤታችን የሚገኘው ይህ ጣቢያ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን፣ ሙዚቃዎችንና በድራማ መልክ የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦችን ያስተላልፋል። በተጨማሪም የበላይ አካል አባል ወይም የአንዱ ኮሚቴ ረዳት በሆነ ወንድም የሚቀርብ ፕሮግራም በየወሩ ይወጣል።

ወንድም ሳንደርሰን፣ ከመጀመሪያው ፕሮግራም ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ ክፍል እንዲመለከቱ አድማጮችን ጋበዘ። ፕሮግራሙን የመራው የበላይ አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት ሲሆን አዲሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም የተከናወነውን ሥራ የሚያሳይ ቪዲዮ በፕሮግራሙ ላይ ተካትቶ ነበር። ጥቅምት 6 ቀን 2014 ጄደብሊው ብሮድካስት የቀጥታ ስርጭቱን የጀመረ ሲሆን ጣቢያው የሚገኘው tv.mr1310.com በተባለው ድረ ገጽ ላይ ነው።

ዘ ኪንግደም​—ዋን ሀንድረድ ይርስ ኤንድ ካውንቲንግ።”

የአምላክ መንግሥት በስብከቱ ሥራችን እድገት እንድናደርግና እየተሻሻልን እንድንሄድ ደረጃ በደረጃ ሲረዳን የቆየው እንዴት እንደሆነ የሚያወሳው የዚህ ቪዲዮ ተራኪ የበላይ አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ ነው። የቀድሞ ቪዲዮዎችን፣ በድራማ መልክ እንደገና የተተወኑ ታሪኮችንና ለረጅም ጊዜ በእውነት ውስጥ ከቆዩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን በማቀናጀት የተዘጋጀው ይህ ቪዲዮ የፍጥረት ፎቶ ድራማ የተዘጋጀውና ለሕዝብ የቀረበው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም በሸክላ ማጫወቻዎች፣ በምሥክርነት መስጫ ካርዶች፣ በሰልፎችና የድምፅ ማጉያ በተገጠመላቸው መኪኖች አማካኝነት ምሥክርነት ይሰጥ የነበረበትን መንገድ ያሳያል፤ በተጨማሪም ለአገልግሎት ሥልጠና ለመስጠት ስለተቋቋሙት ትምህርት ቤቶች ይተርካል።

የአምላክ መንግሥት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውን ነገሮች መለስ ብለን ማሰባችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? መንግሥቱ እውን እንዲሆንልን እንዲሁም ወደፊት የሚያከናውናቸውን ነገሮች በጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል።

ለአምልኮ የሚያገለግሉ መዝሙሮች።

የበላይ አካል አባል የሆነው ዴቪድ ስፕሌን ለይሖዋ ዘምሩ የተባለውን የመዝሙር መጽሐፍ እንደገና አሻሽሎ ለማውጣት እንደታሰበ ሲገልጽ ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ በጣም ተደስተው ነበር። የመዝሙር መጽሐፉ አዲስ ዓለም ትርጉም የተዘጋጀበት ዓይነት ሽፋንና ግራጫ ቀለም ያለው ጠርዝ ይኖረዋል። ለመዝሙር መጽሐፋችን እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥራት ያለው ሽፋን መጠቀማችን ሙዚቃ በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ያለውን ትልቅ ቦታ ያሳያል።

በተጨማሪም በመዝሙር መጽሐፉ ላይ የተወሰኑ መዝሙሮች እንደሚጨመሩ ወንድም ስፕሌን ገለጸ። ይሁን እንጂ እነዚህን አዳዲስ መዝሙሮች ለመዘመር ተሻሽሎ የሚወጣው የመዝሙር መጽሐፍ እስኪታተም ድረስ መጠበቅ አያስፈልገንም። መዝሙሮቹ እንደተዘጋጁ jw.org ላይ ይወጣሉ።

ሦስቱ አዳዲስ መዝሙሮች በዓመታዊ ስብሰባው ላይ ተዘምረው ነበር፤ ስብሰባው በተካሄደበት ሳምንት መጀመሪያ ላይ የቤቴል ቤተሰብ አባላት መዝሙሮቹን ተለማምደዋቸው ነበር። የመዘምራን ቡድኑ በወንድም ስፕሌን መሪነት “በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!” የሚለውን አዲስ መዝሙር ዘመረ። ይህ መዝሙር የተዘጋጀው የአምላክ መንግሥት የተወለደበትን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ነው። የመዘምራን ቡድኑ መዝሙሩን ከዘመረ በኋላ ተሰብሳቢዎቹም አብረው ዘመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የመዘምራን ቡድኑና ተሰብሳቢዎቹ “ድፍረት ስጠን” የሚል ርዕስ ያለውን ሌላ አዲስ መዝሙር ዘመሩ።

ቃለ ምልልስ።

የበላይ አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ ለረጅም ዓመታት በቤቴል ላገለገሉ ሦስት ባልና ሚስቶች ያደረገው ቃለ ምልልስ በቪዲዮ ተቀድቶ ቀረበ። እነዚህ ቤቴላውያን ባለፉት ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ የተመለከቷቸውን ለውጦች በመናገር ይህ ሁኔታ የአምላክ ሕዝቦች እድገት እያደረጉ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ጎላ አድርገው ገለጹ። ወንድም ሎሽ፣ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ የሚጠቁመውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ከገለጸ በኋላ ሁላችንም ከይሖዋ ድርጅት እኩል መጓዝ እንዳለብን አሳሰበ።​—ኢሳይያስ 60:17

“ጥላ እና እውነተኛው ነገር።”

ይህን ንግግር ያቀረበው ወንድም ስፕሌን ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጽሑፎቻችን እንደ ቀድሞው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ባላቸው ትንቢታዊ ጥላ ላይ እምብዛም ትኩረት የማያደርጉት ለምን እንደሆነ አብራራ።

ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በዛሬው ጊዜ ላሉ ታማኝ ክርስቲያኖች ጥላዎች እንደሆኑ ይገልጹ ነበር። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዘገባዎች በዘመናችን ካሉ የአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ለሚፈጸሙ ክንውኖች ትንቢታዊ ጥላ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። እርግጥ ነው፣ እነዚህን ንጽጽሮች ማጥናት ትኩረት የሚስብና አስደሳች ሊሆን ይችላል። ታዲያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚወጡ ጽሑፎቻችን ጥላነት ያላቸውን ነገሮች እና እውነተኛዎቹን ነገሮች እምብዛም የማይጠቅሱት ለምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ወይም ክንውኖች ወደፊት ለሚፈጸሙ የላቁ ነገሮች ጥላ እንደሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት ራሳቸው የሚገልጹበት ጊዜ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ዘገባ ጥላ እንደሆነ በግልጽ የሚያመለክት ከሆነ በደስታ እንቀበላለን። “መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማይል ከሆነ ግን እኛም ምንም ማለት የለብንም” በማለት ወንድም ስፕሌን ተናገረ። የእያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ትርጉም ለማወቅ ጥረት ማድረግ አያስፈልገንም። ከዚህም በተጨማሪ ተስፋችን በሰማይም ይሁን በምድር፣ ጥላ የሆኑ ነገሮችን በመፈለግ እንዲሁም አፈጻጸማቸውን ለማወቅ ጥረት በማድረግ ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ልናገኝ የምንችለውን በዕለታዊ ሕይወታችን ሊጠቅመን የሚችል ትምህርት ሳናገኝ እንቀራለን።​—ሮም 15:4 a

“ነቅታችሁ ትጠብቃላችሁ?”

ወንድም ሌት ያቀረበው ይህ ንግግር ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል ከተናገረው ምሳሌ ጋር በተያያዘ ያለንን ግንዛቤ እንድናስተካክል ረድቶናል። (ማቴዎስ 25:1-13) አሁን ባገኘነው ግንዛቤ መሠረት በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሙሽራ ኢየሱስ ሲሆን ደናግሉ ደግሞ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ናቸው። (ሉቃስ 5:34, 35፤ 2 ቆሮንቶስ 11:2) ምሳሌው በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚከናወኑትን ነገሮች የሚያመለክት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚነቱን የሚያገኘው በታላቁ መከራ ወቅት ነው። ኢየሱስ ሞኞች ስለሆኑት አምስት ደናግል ሲናገር ከቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ብዙዎቹ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተው በሌሎች መተካት እንደሚያስፈልጋቸው መግለጹ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ልብ ሊባል የሚገባ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ነበር። አምስቱ ደናግል ልባሞች፣ አምስቱ ደግሞ ሞኞች እንደሆኑ ሁሉ እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ዝግጁና ንቁ ሆኖ የመጠበቅ አሊያም ከእውነት ጎዳና የመውጣት ምርጫ አለው።

በአንድ ዘገባ ውስጥ የተጠቀሰውን የእያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ትርጉም ለማወቅ ጥረት ማድረግ አላስፈላጊ እንደሆነ ቀደም ሲል ተገልጿል፤ በመሆኑም በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር ነገሮች በሙሉ ከምሳሌው ፍጻሜ ጋር በተያያዘ የሚያመለክቱት ነገር እንዳለ በማሰብ ምርምር ለማድረግ መሞከራችን ጥበብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከምሳሌው ልናገኘው በምንችለው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ትምህርት ላይ ማተኮራችን የተሻለ ነው። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል አባላት፣ ሁላችንም ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ የማድረግ እንዲሁም ‘ነቅተን የመጠበቅ’ ኃላፊነት አለብን። (ዮሐንስ 10:16፤ ማርቆስ 13:37፤ ማቴዎስ 5:16) ታማኝ ሆኖ መገኘት የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። እያንዳንዳችን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን በመኖርና በአገልግሎት ተሳትፎ በማድረግ ‘ሕይወትን መምረጥ’ ይኖርብናል።​—ዘዳግም 30:19

“የታላንቱ ምሳሌ።”

ይህን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ ሲሆን ስለ ታላንቱ ምሳሌ ካለን ግንዛቤ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ማስተካከያ አብራራ። (ማቴዎስ 25:14-30) አሁን ባገኘነው ግንዛቤ መሠረት በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ጌታ (ኢየሱስ) ወደፊት በሚመጣበት ጊዜ ባሪያዎቹን (በምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን ተከታዮቹን) ሰማያዊ ሕይወት እንዲያገኙ በማድረግ ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል። ኢየሱስ “ክፉና ሰነፍ” በሆነው ባሪያ ላይ የሚደርሰውን ነገር ሲናገር ከቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ብዙዎቹ ታማኝነታቸውን እንደሚያጓድሉ መተንበዩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቅቡዓን ተከታዮቹ ምንጊዜም በትጋት እንዲሠሩ እንዲሁም ክፉው ባሪያ ካሳየው ዝንባሌና ካደረገው ነገር እንዲርቁ ማስጠንቀቁ ነበር።

ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ጌታ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ለባሪያዎቹ ሰጥቷል። በተመሳሳይም ኢየሱስ እንደ ውድ የሚመለከተውን ነገር ይኸውም የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ ለተከታዮቹ በአደራ ሰጥቷል። እንዲሁም ሁላችንም አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል በስብከቱ ሥራ በትጋት እንድንካፈል ይጠብቅብናል። ወንድም ሞሪስ፣ ተሰብሳቢዎቹ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በቅንዓት የሚያከናውኑ በመሆናቸው ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ገለጸ።

“በቅርቡ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ማን ነው?”

በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ የቀረበውን ይህን ትኩረት የሚስብ ንግግር የሰጠው የበላይ አካል አባል የሆነው ጄፍሪ ጃክሰን ነው። ወንድም ጃክሰን፣ በማጎጉ ጎግ መሪነት ወደፊት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ማብራሪያ ሰጠ።​—ሕዝቅኤል 38:14-23

ቀደም ሲል የማጎጉ ጎግ የሚለው ስያሜ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ ከተባረረ በኋላ የተሰጠው ስም እንደሆነ እናስብ ነበር። ይሁንና ወንድም ጃክሰን ይህ ዓይነቱ ማብራሪያ የሚያስከትላቸውን አንዳንድ ጥያቄዎች አነሳ። ለምሳሌ ያህል፣ ጎግ ድል በሚደረግበት ጊዜ ይሖዋ “ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉና ለዱር አራዊት መብል” አድርጎ እንደሚሰጠው አስቀድሞ በትንቢት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 39:4) በተጨማሪም ‘ጎግና ስፍር ቁጥር የሌለው ሠራዊቱ’ በምድር ላይ እንደሚቀበሩ ይሖዋ ተናግሯል። ይሁን እንጂ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዴት ሊደርሱበት ይችላሉ? ሰይጣን ለ1,000 ዓመታት ወደ ጥልቁ ይጣላል እንጂ መብል እንዲሆን አይሰጥም ወይም አይቀበርም። (ራእይ 20:1, 2) ከዚህም ሌላ በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ሰይጣን ከጥልቁ ከተፈታ በኋላ “በአራቱም የምድር ማዕዘናት ያሉትን ብሔራት፣ ጎግንና ማጎግን ለማሳሳት . . . ይወጣል።” (ራእይ 20:7, 8) ሰይጣን ራሱ ጎግ ከሆነ ጎግን ማሳሳት እንደማይችል ግልጽ ነው።

በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሰው የማጎጉ ጎግ የሚያመለክተው ሰይጣንን ሳይሆን ወደፊት በአምላክ ሕዝብ ላይ የሚነሱትን ግንባር የፈጠሩ ብሔራትን እንደሆነ ወንድም ጃክሰን ገለጸ። የጎግ ጥቃት ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እንዲሁም “የምድር ነገሥታት” ከሚሰነዝሩት ጥቃት ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም።​—ዳንኤል 11:40, 44, 45፤ ራእይ 17:12-14፤ 19:19

ታዲያ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ የሚያመለክተው ማንን ነው? ይህ ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል። ያም ሆነ ይህ መጨረሻው እየቀረበ በመጣ ቁጥር ወደፊት ስለሚፈጠሩት ክስተቶች ያለን ግንዛቤ እየጠራ መሄዱ እምነት የሚያጠናክር ነው። ወደፊት በአምላክ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አንፈራም፤ ምክንያቱም የማጎጉ ጎግ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት እንደሚሸነፍና ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፋ፣ የአምላክ ሕዝቦች ግን ለዘላለም እንደሚኖሩ እናውቃለን። b

መደምደሚያ።

በመቀጠል ወንድም ሳንደርሰን አዲስ ዓለም ትርጉም በኪስ ሊያዝ በሚችል መጠን ታትሞ መውጣቱን ለተሰብሳቢዎቹ አሳወቀ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በድምፅ ለመቅዳት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነና በርካታ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን ወክለው እንደሚቀዱ ገለጸ። እነዚህ በድምፅ የተቀዱ ፋይሎች ከማቴዎስ መጽሐፍ አንስቶ በ​jw.org ላይ ተራ በተራ ይወጣሉ።

ወንድም ሳንደርሰን፣ የ2015 የዓመት ጥቅስ መዝሙር 106:1 እንደሆነ ተናገረ፤ ጥቅሱ “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት” ይላል። ሁላችንም በየዕለቱ ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉንን ምክንያቶች ቆም ብለን እንድናስብ አበረታታ።

ፕሮግራሙ የተደመደመው “ስምህ ይሖዋ ነው” የሚል ርዕስ ያለውን አዲስ መዝሙር በመዘመር ነው። ተሰብሳቢዎቹ ይህን ግሩም መዝሙር በሚዘምሩበት ወቅት ሰባቱ የበላይ አካል አባላት ከመዘምራን ቡድኑ ጋር ቆመው መዘመራቸው ይህ ታሪካዊ ስብሰባ ባማረ ሁኔታ እንዲደመደም አስችሏል!

a ይህ ንግግርና ቀጣዮቹ ሁለት ንግግሮች በመጋቢት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ በሚወጡ ርዕሶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

b ይህ ንግግር በግንቦት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ በሚወጣ ርዕስ ላይ የተመሠረተ ነው።